2022-07-11 16:14:14
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተማሪዎች ስነምግባር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጥናቶች ገለጹ፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ የትምህርት መረጃ ማዕከል ባወጣው ጥናት ከህዝብ ትምህርት ቤቶች 80 በመቶ በላይ የሆኑት የኮቪድ ወረርኝ በተማሪዎቻቸው ባህሪ ላይ በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ አምጥቷል የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተገልጿል፡፡
በህዝብ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ በተደረገው በዚህ ጥናት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ በተማሪዎች ላይ ከታየው አሉታዊ የባህሪ ለውጦች መሃል በትምህርት ገበታ ላይ አለመገኝት እና ሌሎች ከባድ የባህሪ ለውጦች ተጠቅሰዋል፡፡
በጥናቱ የተካተቱ 846 ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ 87 በመቶ ያህሉ ትምህርት ቤቶች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተማሪዎቻቸው ማህበራዊና ስነልቦናዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳመጣ ተናግረዋል፡፡
በጥናቱ ከተሳተፉ ትምህርት ቤቶች 56 በመቶ ያህሉ በክፍል ውስጥ የተማሪዎች የስነምግባር ግድፈት መጨመሩን ሲገልጹ 49 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከክፍል ውጪ ያሉ አለመግባባቶች መጨመራቸውን ተናግረዋል በማለት የዘገበው ዘ ክርስቲያን ፖስት ነው፡፡
በተጨማሪም 48% የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎቻቸው ለመምህራን እና ለሰራተኞች አክብሮት ያለመስጠት ድርጊት መጨመሩን ሲገልጹ 42 በመቶ ደግሞ በክፍል ውስጥ የተከለከሉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች መጠቀም ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሀገሮች ላይ ካስከተለው ዘርፈ ብዙ ቀውስ በቀጠለ ሁኔታ በተማሪዎች ላይ የፈጠረው ይህ የባህሪ ችግር የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሃገራትም እውነታ ሊሆን ይችላል፡፡ በሀገራችንም ወረርሽኙ የፈጠረው መሰል ተጽዕኖ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም ግልጽ በሆኑት ችግሮቹ ዙሪያ ግን ለመፍትሄ መስራት የሁሉም ሃላፊነት ነው፡፡
332 viewsMira Miracle, 13:14