Get Mystery Box with random crypto!

የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ፍቅር እና ሰላምን መስበክ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል - የኢትዮጵያ | የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውስንል ECGBC

የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ፍቅር እና ሰላምን መስበክ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን
********
የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ፍቅር እና ሰላምን መስበክ እንዲሁም የአብሮነት እሴቶችን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር "የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ለአብሮነት እሴቶች መጠናከር" በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃኑ ትውልድን በሃይማኖት መርሆዎች በመቅረጽ ለሰላም ግንባታ ሚናቸው የላቀ ነው ያሉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ፣ የችግሮች መንስኤ ከመሆን መቆጠብ ይኖርባቸዋልም ብለዋል።
በአንዳንድ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን የሌሎችን ሃይማኖት አለማክበር እና ማንቋሸሽ ይስተዋላል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህ አካሄድ ሊታረም እንደሚገባ ገልፀዋል።
በዘላቂነት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሃይማኖት ሚዲያ ካውንስልን ለማቋቋም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መደረሱንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፣  በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተሸረሸሩ የመጡ እሴቶች መበራከት እና በየቦታው የሚፈጠሩ ችግሮች የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን የቤት ስራዎቻቸውን ላለመስራታቸው ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
በርካታ አማኞች ያሉባት አገሪቱ የሚገዳደል እና መንገድ የሚዘጋ ትውልድ ተበራክቶባታል ያሉት ዋና ፀሐፊው መገናኛ ብዙሃኑ ከመነቃቀፍ ይልቅ መደጋጋፍን እኛ እና እነሱ ከሚል የጥላቻ ትርክት በላይ  አብሮነትን መስበክ አለባቸው ብለዋል።
ተገቢ ባልሆነ አካሄድ ውስጥ እየተጓዙ ለሚገኙ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃንም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና ሰላምን እንዲሰብኩ እንመክራለን ያሉት ዋና ፀሐፊው፣ ይህ ካልሆነ ግን በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታ መኖሩን አብራርተዋል።
@Ethiopian Broadcasting Corporation