Get Mystery Box with random crypto!

በክልሉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል በኢትዮጵያ | Ethiopian Electric Utility

በክልሉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በክልሉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ገ/መድህን ገለፁ፡፡

በክልሉ በተካሄደው ጦርነት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም ችግሮችን በመቋቋም አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ለማድረግ ክፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዚህ በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራትም ስድስት ሺ በላይ አዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ስራ አስፈፃሚው ገልፀው ከኃይል ሽያጭ ገቢ 230 ሚሊዮን 585 ሺ 358 ብር እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢ ደግሞ 102 ሚሊዮን 805 ሺ 811 ብር መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በነበረው ውስን ግብዓት ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ መስመሮች ለማሻሻል የኮንክሪት ምሰሶ ተከላ ማከናወን፣ የተቋረጠውን የሲስተም አሰራር ለማስቀጠል የዝግጅት ስራ ማከናወን፣ የማስፋፊያ ግንባታ ማከናወን፣ በሶስት የገጠር መንደሮች የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መገንባት የመሳሰሉ ስራዎች አቅም በፈቀደ መጠን ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ በሚቀጥለው ጊዜ ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን ክፍተት ሊያካክስ የሚችል ስራ ለማከናወን ጥረት ይደረጋል ያሉት አቶ መስፍን በአሁኑ ወቅት የክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያጠና በዋናው ቢሮ የተዋቀረ የቴክኒክ ቡድን ስራ መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡

አክለውም በቀጣይ የአገልግሎቱን ማዕከላት ሙሉ በሙሉ መልሶ በሲስተም ማስተሳሰር፣ ከሲስተም ውጪ ሲሰሩ የነበሩትን ስራዎች ወደ ሲስተም መመለስ፣ የሰው ሀይሉን ክፍተቶች መሙላት፣ የተቋሙን አዲስ መመሪያዎች፣ አደረጃጀት ወዘተ ተግባራዊ ማድረግ የመሳሰሉ ስራዎች የሚከናወኑ ይሆናል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ተቋርጠው የነበሩ የመልሶ ግንባታ፣ የገጠር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ከዋና መስመር ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች አነስተኛ የኃይል አማራጮች ግንባታ፣ ሶስት ሺ ቆጣሪዎችን በስማርት ቆጣሪዎች መቀየር፣ የተጎዱ ቢሮዎች ጥገናና ግንባታ፣ የመካከለኛ መስመር ማሻሻያ፣ አዲስ ደንበኛ የማገናኘት ወዘተ አንኳር ስራዎች ይከናወናሉ ሲሉ ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም በክልሉ ያለውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ለሚደረገው ጥረት ሁሉም አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት