Get Mystery Box with random crypto!

የኮርፖሬሽኑ ሴት ሠራተኞች ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች ታላቁ ሩጫ ላይ ተሳተፉ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽ | ECWC/ኢኮሥኮ/

የኮርፖሬሽኑ ሴት ሠራተኞች ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች ታላቁ ሩጫ ላይ ተሳተፉ
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢ.ኮ.ሥ.ኮ) ሴት ሠራተኞች በየዓመቱ እ.ኤ.አ አቆጣጠር ማርች 8 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመልከት በአገር አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ በተካሄደው ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች ታላቁ ሩጫ ላይ ተሳተፉ፡፡
መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው እና ከ15 ሺህ በላይ እንስቶች በተሳተፉበት በዚህ የ5 ኪ.ሜ የመካከለኛ ርቀት የሩጫ ውድድር ወደ 200 የሚጠጉ የኢ.ኮ.ሥ.ኮ ሴት ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የሩጫ ውድድሩ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የገለፁት በኢ.ኮ.ሥ.ኮ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፋጡማ ጀማል ውድድሩ በየዓመቱ መካሄዱ ሴቶች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ፣ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ፣ ራሳቸውን እንዲያዝናኑ እና በሥነ-ልቦና እንዲያንፁ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም እንደኮርፖሬሽን ተቋማቸውን እንዲወዱና እንዲያስተዋውቁ እንዲሁም የሥራ ፍቅር እና ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ያስችላል ያሉት ወ/ሮ ፋጡማ ኮርፖሬሽኑ ይህንን ተረድቶ የሥራው አንዱ አካል እንዲያደርግ፣ ለሥርዓተ-ፆታ ትኩረትና እውቅና በመስጠት የመንግስትን ፖሊሲ እንዲያስፈፅም መምሪያው ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡
መነሻውን ከቦሌ አትላስ ያደረገው የሩጫ ውድድሩ በቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን፣ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከዚያም በፍሬንድሺፕ አድርጎ መጨረሻውን ቦሌ አትላስ ላይ አድርጓል፡፡
የ2015 ዓ.ም ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የሩጫ ውድድር “ቦታዬ፤ መብቴ፤ ድምፄ” በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ ተካሂዷል፡፡
በውድድሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ-ሥላሴ፣ አትሌት መሰረት ደፋር፣ አትሌት ለተሰንበት ግደይን ጨምሮ ሌሎችም አትሌቶችና እንግዶች ተገኝተዋል።