Get Mystery Box with random crypto!

ሳይንቲስት የመሆን ህልም ያላት ተማሪ ገሊላ ውጤቴ ባልረካም ወደ ዩንቨርሲቲ የሚያስገባኝ ስለሆነ አ | EBC(Ethiopian Brodcasting Corboration(EBC)

ሳይንቲስት የመሆን ህልም ያላት ተማሪ ገሊላ ውጤቴ ባልረካም ወደ ዩንቨርሲቲ የሚያስገባኝ ስለሆነ አይከፋኝም




ተማሪ ገሊላ አሰፋ ትባላለች፤ ከህጻንነቷ ጀምሮ ሳይንቲስት የመሆን ህልምን ይዛ ትምህርቷን ስትከታተል የነበረችው ገሊላ በአጣዬ ከተማ ተወልዳ ማደጓን ነግራናለች።
“የደረጃ ተማሪ መሆኔ ምኞቴ እንደሚሳካ የእርግጠኝነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርገኛል” የምትለው ተማሪ ገሊላ “በአካባቢያችን በተደጋጋሚ የተከሰቱት ጦርነቶች አስጨናቂ እና ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ” ብላለች።
“በተለይ ደግሞ 11ኛ ክፍል ተማሪ እያለች በ2013 ዓ.ም ላይ የተከሰቱት ሁለት ግጭቶች መኖሪያ ቤታችንን ጨምሮ ትምህርት ቤታችን እና ሌሎች ንብረቶቻችን ሲቃጠሉ መግለጽ የሚከብዱ ከባድ የተስፋ መቁረጥ ስሜቶች ተሰምተውኛል ብላናለች፡፡
በነዚህ ግጭቶች ምክንያት ህይወታችንን ለማትረፍ በተደጋጋሚ ለስደት ተዳርገናል የምትለው ተማሪ ገሊላ ሳይንቲስት የመሆን ምኞቴ ቀርቶ ፍላጎቴ በህይወት መኖር ብቻ እንደነበርም ተናግራለች፡።
ከአንድ ዓመት በፊት ህወሓት ወደ ሰሜን ሸዋ ጥቃት በመክፈቱ ምክንያትም እሷ እና ቤተሰቦቿ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ደብረብርሃን መሰደዳቸውን ነግራናለች።
አካባቢው መልሶ ሲረጋጋ ግን ትምህርቷን ለመቀጠል ስትል በአንድ ዘመዷ እና በሸዋሮቢት ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እርዳታ ምክንያት ከ11ኛ ክፍል ሁለተኛ መንፈቀ- ትምህርት ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን እንደወሰደችም ነግራናለች።
ቤተሰቦቼ እና መምህራኖቼ ያደረጉልኝ ድጋፍ በጦርነቱ ምክንያት ያየኋቸውን መጥፎ ሁኔታዎች ሁሉ እንድረሳ አድርጎኛል የምትለው ተማሪ ገሊላ ቤተሰቦቿን እና መምህራንን አመስግናለች።
የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተናን በሰላም በደብረብርሃን ዩንቨርሲቲ ተፈትና 569 ማምጣቷን ጠቅሳለች። “መፈናቀሉ እና ጦርነቶቹ ሁሉ ባይኖሩ ከዚህ የተሻለ ውጤት ላመጣ እችል ነበር፣ ይሁንና ይህ ውጤት ወደ ዩንቨርሲቲ የሚያስገባኝ በመሆኑ አይከፋኝም” ብላለች። ይህ ውጤት ከሰሜን ሸዋ እና አካባቢው ከሴቶች ከፍተኛው ውጤት እንደሆነ ሰምተናል።
ጦርነት የሰውን ልጅ ሲገድል እና ድሃ ሲያደርግ አይቻለሁ ያለችን ተማሪ ገሊላ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ሰላምን ተመኝታለች።
በቀጣይ በዩንቨርሲቲ በሚኖራት ጊዜ ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ማጥናት የመጀመሪያ ፍላጎቷ መሆኑን የነገረችን ተማሪ ገሊላ 12 ዓመት ሙሉ የለፉ የዘንድሮ ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤት በዚህ መልኩ መደምደሙ እንደሚያሳዝናትም ጠቁማለች።
Via አል ዓይን