Get Mystery Box with random crypto!

ዝንባሌያችንን የማወቅ አስፈላጊነት የስነ-ልቦና አዋቂዎች እንደሚነግሩን፣ ሰዎች የሚያልፉባቸው ጤ | Dr. Eyob Mamo

ዝንባሌያችንን የማወቅ አስፈላጊነት

የስነ-ልቦና አዋቂዎች እንደሚነግሩን፣ ሰዎች የሚያልፉባቸው ጤና ቢስ ልምምዶች በነገው ማንነታቸው ላይ ታላቅ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ አለው፡፡

አንዳንድ ሰዎች ካሳለፉት ልምምድ የተነሳ በመዛል ማንም እንዳሻው የሚያደርጋቸው “አጥር” የለሽ ሰው ይሆናሉ:: ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው ማንም እንደገና “እንዳይደፍራቸው” እና እንዳይነካቸው የተለያዩ “አጥሮችን” በዙሪያቸው ይሰራሉ፡፡ በእንደዚህ ሁኔታ ባለፈው ታሪካቸውና ልምምዳቸው ተጽእኖ ስር የወደቁ ሰዎችን በአራት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡

እነዚህ ዝንባሌዎች በአመራርም ሆነ በማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነታችን ተግባራዊነታቸው አይለወጥም::

1. ለሁሉም ነገር ተስማሚዎች (Compliants)

እንዲህ አይነት መሪዎች ሌሎች የግል ሕይወታቸውን መስመር ረግጠው እንዲያልፉና እደፈለጉ እንዲያደርጓቸው የሚፈቅዱ ሰዎች ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ የሚሆኑት የሰውን ስሜት የመጉዳት ፍርሃት ስላለባቸው ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች እምቢታ ከአንደበታቸው አይወጣም፡፡ መብታቸውን ካለአግባብ የሚጋፋና ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንኳ ቢሆን ለሰው ስሜት ለመጠንቀቅ ሲሉ ብቻ ያደርጉታል፡፡ ሰዎች ትተውን ይሄዳሉ ብለው ስለሚፈሩ መዘጋት ያለበትን የስሜት በራቸውን ይከፍታሉ፣ ሰዎች ሰተት ብለው ስለገቡ ደግሞ ተጎዳሁ ብለው ሲወቅሱ ይታያሉ፡፡

2. ገለልተኞች (Avoidants)

እንዲህ አይነት መሪዎች ለሰዎች ክፍት መሆን በሚገባቸው ጊዜና ሁኔታ የማንነት በራቸውን ጥርቅም አድርገው የሚዘጉ ናቸው፡፡ እንደዚህ አይነት መሪዎች ግፊት ያለበት ሁኔታ ሲከሰት ከመቋቋም ይልቅ ዘወር ማለት ይቀናቸዋል፡፡ የቀድሞ የአስተዳደግ ሁኔታ ወይም የኑሮ ልምምድ ካመጣው ተጽእኖ የተነሳ ደግመው ላለመጎዳት ራሳቸውን ዝግ የማድረግ ዝንባሌ አላቸው፡፡ እንዲህ አይነት መሪዎችን ለመርዳት እጅግ አስቸጋሪ ነው፣ ምክንያቱም ያለባቸው ዝግ የመሆን ዝንባሌ ለመርዳት የሚቀርቧቸውንም ሰዎች ጭምር ስለሚያርቅ ነው፡፡

3. ተቆጣጣሪዎች (Controllers)

እንዲህ አይነት መሪዎች የሌሎችን መስመር የማያከብሩና በሰዎች ስሜት፣ ሕይወት፣ ውሳኔና አመለካከት ላይ የሚረማመዱ መሪዎች ናቸው፡፡ ሰው ሊጣስበት የማይገባው መስመር እንዳለው የማያውቁ አይነት ተቆጣጣሪ መሪዎች ናቸው፡፡ ተቆጣጣሪዎች በሁለት ይከፈላሉ፡- “ጉልበተኞች” (aggressive) እና “ለስላሶች” (passive)፡፡

ጉልበተኛ ተቆጣጣሪዎች ኃይልን በመጠቀም መግባት የሌለባቸው ቦታና ሁኔታ ላይ ጥልቅ የሚሉ፣ እንደዚያ የማድረግም መብት እንዳላቸው የሚያስቡና የሚቆጣጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ለስላሳ ተቆጣጣሪዎች የጥፋተኝነት ስሜትን በመስጠትና በማታለል ሰዎቹ አንድን ማድረግ የማይፈልጉትን ነገር እንዲያደርጉ የሚገፋፉና በምርጫቸው እንዳደረጉት ስሜትን የሚያሳድሩባቸው አይነት መሪዎች ናቸው፡፡

4. ስሜት የለሾች (Non-responsives)

እንዲህ አይነት መሪዎች ለሰዎች ችግር፣ ጥያቄና ፍላጎት ምላሽን በመንፈግ አጥርን በዙሪያቸው የሚያበጁ ሰዎች ናቸው፡፡ ከማህበሩ ጋር እጅግ የተራራቁና በቀላሉ የማይገኙ ከመሆናቸውም በላይ ምንም አይነት ሁኔታ ቢከሰት ስሜት የማይሰጣቸውና ለመፍትሄ ራሳቸውን የማያቀርቡ አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ እንደዚህ አይነት መሪዎች አንዳንድ ጊዜ በዙሪያቸው በጣም ለህዝቡ የሚጠነቀቁ ሌሎች መሪዎች ከከበቧቸው ይህ ዝንባሌአቸው ብዙም ሳይታወቅ ለተወሰነ ጊዜ ሊጓዙ ቢችሉም የኋላ ኋላ ግን አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን ያገኙታል፡፡

እንግዲህ አንድ መሪ ራሱን በሚገባ በማወቅና ድካሙንና ብርታቱን በመገንዘብ ወደስኬታማ ጎዳና የሚገባበትን መንገድ መጥረግ ይጠበቅበታል፡፡ አንድ መሪ ራሱን በሚገባ በማያውቅበት ጊዜ ከሚከተሉት ሁለት ችግሮች ለአንዱ ሊጋለጥ ይችላል፡፡

ራሱን በማወቅ በሚገባ ያልበሰለ መሪ በሰዎች ሃሳብ በቀላሉ የሚነዳና ራሱ አቋም የሌለው ሰው ነው፤ እንደመጣው ሰውና እንደተነገረው ሃሳብ አቋሙን ይለዋውጣል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ አንድ መሪ ራሱን በሚገባ በማያውቅበት ጊዜ ስለ ሰዎች ፍላጎት ግድ የለሽ ወደ መሆንም ሊያዘነብል ይችላል፡፡ ራሱን በማወቅ ስላልተደላደለ የሚችለውን መንገድ ሁሉ ተጠቅሞ ራሱን በማግነን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ይታገላል፡፡

(አመራር A to Z ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ፡)

መጽሐፉ በአሁን ጊዜ በመደብሮች ሁሉ ይገኛል፡፡

https://t.me/Dreyob

https://m.youtube.com/user/naeleyob623

https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/