Get Mystery Box with random crypto!

ወርቅ፣ ብርና ነሃስ! አንዳንድ የስነ-ልቦና ጥናቶችን አገላለጽ ወደ እኛ ቋንቋ ስንመልሳቸው ቢያታ | Dr. Eyob Mamo

ወርቅ፣ ብርና ነሃስ!

አንዳንድ የስነ-ልቦና ጥናቶችን አገላለጽ ወደ እኛ ቋንቋ ስንመልሳቸው ቢያታግለንም ለትርጉሙ ቀረብ በሚል አገላለጽ ስንገልጻቸው፣ “ከእውነታው ወደላይ የወጣ አመለካከት” (Upward counter factual thinking) እና “ከእውነታው ወደታች የወረደ አመለካከት” (Downward counter factual thinking) የሚባሉ ሁለት አመለካከቶች አሉ፡፡ ይህንን ሃሳብ ለማብራራት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2020 ዓ/ም የተደረገ አንድ ጥናት፣ “በኦሎምፒክ ውድድር ወቅት አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሽልማትን ከተረከበው ሰው ቀጥሎ ደስተኛው ተሸላሚ ማን ነው? ሁለተኛው የወጣው የብር ተሸላሚ ነው? ወይስ ሶስተኛ የወጣው የነሃስ ተሸላሚ?” ለሚለው ጥያቄ መልስን ይሰጣል፡፡

በጥናቱ ውጤት መሰረት ሁለተኛ በመውጣት ብር ከሚሸለሙ ተወዳዳሪዎች ይልቅ ሶስተኛ በመውጣት ነሃስ የሚሸለሙ ተወዳዳሪዎች የበለጠ ደስተኛ ናቸው፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ካለን ራሳችንን ከግባችን አንጻር ሳይሆን ከሌላው ሰው አንጻር የመመልከት ዝንባሌ የተነሳ ነው፡፡

ጥናቱ እንደሚነግረን፣ ሁለተኛ የሚወጡ ሰዎች ከእውነታው ወደላይ በመመልከት (Upward counter factual thinking) አንደኛ ከወጣው ሰው ጋር ራሳቸውን በማነጻጸር፣ “አንደኛ ብወጣ ኖሮ” የሚልን የጸጸት ስሜት ያስተናግዳሉ፡፡ ምንም እንኳን ከአንድ ሰው በስተቀር ሁሉንም የቀደሙ ቢሆንም “ያጡት” ላይ በማተኮር ያዝናሉ፡፡

በተቃራኒ፣ ሶስተኛ የወጡት ሰዎች ከእውነታው ወደታች በመመልከት (Downward counter factual thinking) ምንም ሽልማት ካላገኙት ሰዎች ጋር ራሳቸውን በማነጻጸር፣ “ሶስተኛ ባልወጣ ኖሮ” የሚልን “የእንኳን አልሆነብኝ” ስሜት ያስተናግዳሉ፡፡ ምንም እንኳን በሁለት ሰዎች ቢቀደሙም ሁኔታው ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ “ያገኙት” ላይ በማተኮር ይደሰታሉ፡፡

በማንኛውም የሕይወታችን ስምሪትና ጥረት ውስጥ ለትንሽ ያመለጠንን ጥሩ “ውጤት” ለነገ ትምህርት፣ ለትንሽ ያመለጥነውን መጥፎ “ውጤት” ደግሞ ፈጣሪን ለማመስገንና ለደስተኛነት ብንጠቀምበት ጥሩ የስነ-ልቦና ሁኔታ ውስጥ ራሳችንን እንደምናገኘው ጥርጥር የለውም፡፡

በትጋት ከሰራች በኋላ ያመለጣችሁ ነገር ላይ ሳይሆን በልፋታችሁ ያገኛችሁት ውጤት ላይ አተኩሩ!

https://t.me/Dreyob

https://m.youtube.com/user/naeleyob623

https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/