Get Mystery Box with random crypto!

አራቱ የተዛቡ የጊዜ አጠቃቀም ገጸ-ባህሪያት (“የጊዜ አጠቃቀም ጥበብ” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማ | Dr. Eyob Mamo

አራቱ የተዛቡ የጊዜ አጠቃቀም ገጸ-ባህሪያት

(“የጊዜ አጠቃቀም ጥበብ” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)

1. “አቶ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ”

ልክ የእሳት አደጋ መከላከያ ሰራተኞች ተግባራቸው በየቦታው እየበረሩ የተነሳን እሳት ማጥፋት እንደሆነ “አቶ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ” እዚህና እዚያ ብቅ ለሚሉ ሁኔታዎች ምላሽ በመስጠት ጊዜውን የሚያሳልፍሰው ነው፡፡ ለተለያዩ ችግሮች ምላሽ በመስጠት ከመሯሯጡ የተነሳ ቁጭ ብሎ ጊዜውን በሚገባ ለመጠቀም የሚረዳውን እቅድ ለማውጣት “ጊዜ” የለውም፡፡ ልክ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ከዚህኛው ወደዚያኛው እሳት እንደሚጣደፉ፣ እንዲህ አይነቱ ሰው ብዙውን ጊዜ ከስፍራ ወደ ስፍራ በፍጥነት ሲዘዋወርና በወቅቱ ሃሳቡን ለሳበው ችግር ምላሽ ለመስጠት ሲሯሯጥ ይታያል፡፡

ይህ አይነቱ ዝንባሌ አብዛኛውን ጊዜ ምንጩ የአስተዳደግ ሁኔታ ነው፡፡ አንድ ሰው ለተደወለው ስልክና ተከሰተ ለተባለው ችግር ሁሉ በድንገት ብድግ በማለት በሚሮጡ ቤተሰቦች መካከል ካደገ ያንንው ተምሮ ነው የሚያድገው፡፡

2. “አቶ አስደሳች”

የ“አቶ አስደሳች” ችግር “እምቢ” ለማለት ያለመቻል ችግር ነው፡፡ አንድ ሰው አንድን ነገር እንዲያደርግለት ከጠየቀው፣ ጊዜ ባይኖረው እንኳ “እሺ” በማለት ቃል ይገባል፡፡ ሰውን ሁሉ የመሸኘቱ፣ ለቸገረው ሁሉ ገንዘብ አበዳሪነቱ፣ ከአቅሙ በላይ ቢሆንም እንኳ የተጠየቀውን ስራ ሁሉ በእሺታ የመቀበሉ ዝንባሌ ጊዜ አጠቃሙን ከመስመር አውጥቶበታል፡፡

“አቶ አስደሳች” በተመሳሳይ ሰዓት ላይ ከሁለትና ከሶስት ሰዎች ጋር ቀጠሮ ሊይዝ ይችላል - በመዘንጋት ሳይሆን እምቢ የማለት የፈቃድ ጉልበት በማጣት፡፡ እንዲህ አይነት ሰው ከአምስትና ከስድስት ኮሚቴዎች በላይ አባል ሆኖ ራሱን ሊያገኘው ይችላል፡፡እንዲህ አይነቱ ዝንባሌ ከዝቅተኝነት ስሜትና ተቀባይነት ለማግኘት ከሚኖር የውስጥ ምኞት ወይም ደግሞ የሰውን ስሜት ላለመጉዳት ካለ ጽኑ ፍላጎት ሊመነጭ ይችላል፡፡ “አቶ አስደሳች” ብዙ ጊዜ ከሰዎች ሲደበቅ ይታያል - ይህንን አድርግልኝ ተብሎ ተጠይቆ እምቢ ከሚል መደበቁን ይመርጣል፡፡

3. “አቶ ጊዜ አለኝ”

“አቶ ጊዜ አለኝ” አንድን ነገር የሚተገብረው ሲመቸው ወይም “ሙዱን” ሲያገኝ ነው፡፡ ዘና ያለ፣ መጨናነቅ የማይወድና ብዙውን ጊዜ እግሩን ጠረጴዛ ላይ ሰቅሎ የሚታይ ሰው ነው፡፡ ተግባሮቹን ቅደም ተከተል የማስያዝ ልማድ ባይኖረውም በውስጥ ታዋቂነት ግን ማድረግ ደስ ከሚለው ተግባር መጀመር እንደሚወድ እውቅ ነው፡፡ አንድ ነገር ደስ የሚለው ከሆነ ጊዜ አያጣለትም፡፡ በመቀጠልም ለማድረግ ቀለል ያለውን የመምረጥ ዝንባሌ አለው፡፡ አንድ የጀመረውን ነገር ለማስተላለፍ ወይም ለማቆም ትንሽ “እንቅፋት” በቂ ነው፡፡

“አቶ ጊዜ አለኝ” የኑሮው መፈክር፣ “ስደርስ እደርስበታለሁ” ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በጊዜው ያልተከናወነ ተግባር ሊያደርስ የሚችለውን መዘዝም ሆነ ሊጎዳ የሚችለውን ሰው የማየት ብቃት የለውም፡፡ እንዲሁ በመላ-ምት ስለሚኖር ከራሱ አልፎ ቤተሰቡንም ሆነ መስሪያ ቤቱን የሚጎትት ታላቅ የስኬት ጠንቅ ነው፡፡

4. “ወ/ሪት ማሕበረሰብ”

“ወ/ሪት ማሕበረሰብ” የተወለደችው ከሰዎች ጋር ለመሰባሰብ እንደሆነ የሚያስመስልባት ማንነት አላት፡፡ የንግግር ችሎታዋና የመግባባት ፍጥነቷ አስገራሚ ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ለመገናኘትና ለማሳለፍ ከምታገኘው አጋጣሚ አንዱም አያመልጣትም፡፡ የሚያስደንቀው ነገር ለማሕበራዊ ሕይወት በምታደርገው የዚህና የዚያ ሩጫ በፍጹም አለመድከሟ ነው፡፡ “ወ/ሪት ማሕበረሰብ” “ጓደኞቼ” ብላ የምትጠራቸው ሰዎች ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ አብዛኛዎቹን በቀን ውስጥ በአካል ካላገኘቻቸው በስልክ ረዘም ላለ ጊዜ ታነጋግራቸዋለች፡፡ ለመስራት ያልፈለገችው ስራ ካለ ያንን ስራ የምታስተላልፈው ከሰዎች ጋር በመገናኘትና ይህና ያንን በማድረግ ነው፡፡

“ወ/ሪት ማሕበረሰብ” ከስራዋ አካባቢ በፍጹም ሰው አይጠፋም፡፡ ከአንድ ቦታ ወደሌላኛው፣ ወይም ደግሞ ከስራ ቦታ ወደቤቷ ስትሄድ በመንገድ ላይ ሰዎችን ቀጥሮ ሻይ መጠጣትም ሆነ መጨዋወት የተለመደ ተግባሯ ነው፡፡ የአንድን ስራ የቀን ገደብ ከሰዎች ጋር ለማሳለፍ ስትል ማስተላለፍ እንደ ችግር አይታያትም፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት ዝንባሌዎች መካከል ራስህን በየትኛው አገኘኸው? ካላገኘኸውስ ራስህን በምን አይነት ሁኔታ ያየኸው ይመስልሃል? ጊዜ አጠቃቀምህ ሙሉና ስኬታማ ነው ብለህ ታስባለህ?

ጊዜያችሁን በሚገባና በስኬታማነት ለመጠቀም የሚረዳችሁን “የጊዜ አጠቃቀም ጥበብ” የተሰኘው መጽሐፌን ማንበብ አትዘንጉ፡፡ በገበያ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

https://t.me/Dreyob

https://m.youtube.com/user/naeleyob623

https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/