Get Mystery Box with random crypto!

“አላ ቢዚክሪላሂ ተጥመኢኑል ቁሉብ!!” በቅርቡ በግምት የስምንት ሰዐት መንገድ ከአንድ ሾፌር ጋር | ዶር ዛኪር ናይክ # [ Dr zakir nike amharic ] [ ዶ/ር ዛኪር ናይክ] [ dr zakir nike ] DR zakir amharic

“አላ ቢዚክሪላሂ ተጥመኢኑል ቁሉብ!!”
በቅርቡ በግምት የስምንት ሰዐት መንገድ ከአንድ ሾፌር ጋር ተጓዝኩ፡፡ ጉዞው ለኔ በህይወቴ ካሳለፍኳቸው ጉዞዎች እጅግ ልዩ ሆኖብኛል፡፡ ሾፌሩ ከኔ ጋር ከተለዋወጣቸው ጥቂት ቃላት ውጭ ይሄን ሁሉ ሰዐት ስንጓዝ ዚክር ላይ ነበር፡፡ ወላሂ እጅግ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ እሱን አይቼ እኔም ዚክር እጀምርና ብዙም ሳልቆይ እራሴን ከሆነ የሀሳብ ባህር ውስጥ ስንቦጫረቅ አገኘዋለሁ፡፡ እመለሳለሁ፡፡ ዳግም እራሴን ከሌላ ቦታ አገኘዋለሁ፡፡ ሱብሃነላህ!!! እራሴን ታዘብኩት አልላችሁም፡፡ ነገሩ ከዚያም በላይ ነው የሆነብኝ፡፡ እራሴን ተጠየፍኩት፡፡ በወንድሜ በጣም ቀናሁኝ፡፡ አላህ በተውሂድና በሱና ላይ ያፅናው ብያለሁ፡፡
ግን ወንድሞችና እህቶች ስራችን ብለን ቁጭ ብለን ዚክር ላለማረጋችን አዋጣም አላዋጣም ምክኒያት ይኖረን ይሆናል፡፡ አሰልቺ ረጃጂም ጉዞዎችን ስናደርግ አሁንም አሁንም ከማዛጋት፣ አስቀያሚ ማስታወቂዎች ላይ ከማፍጠጥ፣ … ዚክር ብናረግ ምን ነበረበት? ሱብሃለህ!!! አንዴ ሱብሃለህ ሳንል ስንት መቶ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠናል?! ስንት ረጃጅም ሰአቶችን በከንቱ አሳልፈናል? አራት መቶ አምስት መቶ ኪሎ ሜትሩ ይቅር:: የአራትና አምስት ሰዐት መንገዱም ይቅር:: ኧረ ሌላው ቀርቶ የፒያሳ መገናኛ፣ የመርካቶ አየር ጤና መንገድም ይቅር እሩቅ ነው እንበል:: በአንዲት አጭር ፌርማታ ስንትና ስንት ዚክር ማረግ ስንት አጅር ማፈስ አይቻልም? እውነት በዚክሩ የሚገኘው አጅር በገንዘብ ቢቀየር እንዲህ እንዘናጋ ነበር? አቤት የኛ ነገር!!!
እስኪ አንድ ደቂቃ በማይፈጁ ዚክሮች የሚገኘውን አጅር ያስቡ
- “ሱብሐነላሂ ወቢሐምዲሂ ሱብሐነላሂል ዐዚም” በሐዲስ እንደተነገረው እነኚህ ለምላስ የሚቀሉ፣ ሚዛን ላይ የሚከብዱ፣ አረሕማን ዘንድ የተወደዱ ቃላት ናቸው፡፡ በደቂቃ ስንቴ ማለት ይቻላል?
- “ላሐውለ ወላ ቁወተ ኢላ ቢላህ” ከጀነት ድልብ ሀብቶች ውስጥ አንዷ ነች፡፡ በደቂቃ ስንቴ ማለት ይቻላል?
- የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ባለቤት ጁወይሪያ ከፈጅር ሶላት እስከ ረፋድ ዚክር ስታደርግ ቆይታ “እኔ ካንቺ በኋላ አራት ከሊማዎችን ሶስት ጊዜ ደጋግሜ ብያለሁ፡፡ ብትመዘን እስካሁን አንቺ ካልሺው ትበልጣለች አሏት፡፡(ሱብሐነላሂ ወቢሐምዲሂ ዐደደ ኸልቂሂ፣ ወሪዷ ነፍሲሂ፣ ወዚነተ ዐርሺሂ፣ ወሚዳደ ከሊማቲሂ)
- አንዴ በነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ ሶላት ያወረደ አላህ በሱ ላይ 10 ሶለዋት ያወርድበታል፡፡ በደቂቃ ስንቴ ማድረግ ይቻላል? … እነኚህ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ውድ የኢስላም ወንድሞችና እህቶች ኢስላም እኮ ሂወት ነው፡፡ አይደል እንዴ? ጁሙዐ ወይም ረመዳን ብቻ ተጠብቆ ሽር ጉድ የሚባልበት ድግስ አይደለም፡፡ “የኢስላም ድንጋጌዎች በዙቡኝ” ያላቸውን ሰው “ምላስህ አላህን በማውሳት ከመርጠብ አይወገድ” ብለው አይደል ያመላከቱት ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም? ጌታችን እንዲህ ይላል፡ ((… እነዚያ ያመኑት ልቦቻቸውም አላህን በማስታወስ የሚረኩ ናቸው፡፡ አዋጅ! አላህን በማስታወስ (የአማኞች) ልቦች ይረካሉ)) (አረዕድ፡ 28) ነብያችን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡ ((ጌታውን የሚያስታውስና እና የማያስታውስ ምሳሌ የህያው እና የሙት ምሳሌ ነው)) ቡኻሪና ሙስሊም፡፡ አሁን እኛ ህያዋን ነን ወይስ የቁም ሙት?
የአላህ ሰዎች ሀይላቸውም፣ ምግባቸውም፣ እስትንፋሳቸውም፣… ዚክር ነው፡፡ በአንድ ወቅት ያነበብኩት የኢብኑል ቀይም ረሒመሁላህ ንግግር ትዝ አለኝ፡፡ ካየሁት ቆየሁና ምናልባት በትክክል ላላሰፍረው እችላለሁ፡፡ በግርድፉ ይሄን ይመስላል፡፡ “እንደ ኢብኑ ተይሚያ ዚክር የሚያበዛ አላየሁም፡፡ በአንድ ወቅት ፈጅር ከሰገደ ጀምሮ ዚክር ያረጋል፡፡ ባለበት ሁኔታ ላይ እያለ ሰዐቱ በጣም ሄደ፣ ረፈደ፡፡ በሁኔታው ተገርሜ እያየሁት ነው፡፡ እንደተገረምኩ ገብቶታል፡፡ ዘወር ብሎ እንዲህ አለኝ፡- “ይሄ ምግቤ ነው፡፡ እሱን ካላገኘሁ ብርታት አይኖረኝም”
“ጌታችን ሆይ! አንተን ለማስታወስ፣ አንተን ለማመስገን እንዲሁም አንተን ባማረ መልኩ ለመገዛት አግዘን፡፡”

ibnu munewer