Get Mystery Box with random crypto!

+ መስቀል አደባባይና ቤተ ክርስቲያን + ከሁለት ወራት በፊት 'የጥምቀተ ባሕር ቦታዎችንና የአደባ | ዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ Henok Haile

+ መስቀል አደባባይና ቤተ ክርስቲያን +

ከሁለት ወራት በፊት "የጥምቀተ ባሕር ቦታዎችንና የአደባባይ በዓላትን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ልትጠቀምባቸው ትችላለች?" በሚል ርእስ የተለያዩ ባለሙያዎችን አስተያየት ያካተተ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ ነበርሁ፡ ጽሑፉ እንደ ተጠናቀቀ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በዝርዝር ውይይት አደረግን፡፡ ጉዳዩን ለብፁዓን አበው ለማቅረብና ወደ ይፋ ውይይት ለመግባትም ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ነበርን፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ነገሮችን የሚገለባብጥና ስሜት የሚነካ የሰሞኑ አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ::

በተለይ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በምእመናን ላይ የተደረገው አሳዛኝ ሁኔታ ፣ ከዚያ በፊትና በኋላ ሲደረጉ የነበሩት ልብ የሚያቆስሉ ስድድቦች እጅግ የሚያሳዝኑ ነበሩ:: አሁን በዚህ ዘመን ችግር ያነሰን ይመስል ሌላ ችግር መጨመር ነበረብን? ወይ የሚያሰኝ ሆነ፡፡

በስሜት የምንናገራቸውና የምናደርጋቸው ነገሮች ቁጣን ከማብረድና ሥራ የሠራን ያህል እርካታ እንዲሰማን ከማድረግ ያለፈ ውጤት እንደማያመጡ የታወቀ ነው:: በሌላው ተመልካች ዘንድም ‘ልማዳቸውን ነው ይጩኹ’ የሚል ንቀት ከማትረፍ ውጪ ምንም አያመጣም፡፡ ስለዚህ በየአቅጣጫው መፍትሔ የምንለውን ብንጠቁምና ቤተ ክርስቲያናችንን ብናግዝ የተሻለ ስለሚሆን እኔም በምክረ ሃሳቡ ላይ የተካተቱ አንዳንድ ሃሳቦችን ጨምሬ የተሻለ ነው የምለውን መፍትሔ ለመጻፍ ግድ ሆነብኝ፡፡

1. የመስቀል አደባባይ ሕጋዊ ይዞታ ጉዳይ

ቤተ ክርስቲያን ካሏት ነገሮች በተጨማሪ ብዙ ነገሮችን ከሀገሪቱ ልትጠይቅ የሚገባት ብዙ ሚሊዮኖችን የያዘች ሕጋዊ ማንነት ያላት ተቋም ናት፡፡ በዚህ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋን በአግባቡ ከተጠቀመች አንዱን የመስቀል አደባባይ ብቻ ሳይሆን ብዙ መስቀል አደባባዮችን ገንብታ አሁን የመወያያ ርእስ የሆነውን የመስቀል አደባባይ የትኩረት ማእከልነቱን እስከ ማሳጣት ድረስ አቅም ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ከከተማው ስፋትና ከምእመናን ብዛት አንጻር በየክፍለ ከተማው አንድ አንድ መስቀል አደባባዮች እንዲኖሩ ማድረግ የማትችልበትም ምክንያት የለም፡፡

ሆኖም አሁን እንኳን ሌላ ሊጨመር ያለውም የባለቤትነት ጥያቄው አደጋ ላይ ነው፡፡ አደባባዩ የብዙኃን ዓይን ያረፈበትም በከተማው ቦታ ጠፍቶ ሳይሆን ሥፍራው በኦርቶዶክሳውያን ልብ ውስጥ ያለውን የምልክትነት ሥፍራ በመረዳት መሆኑ ግልፅ ነው:: "ሜዳው ሰፊ ነው : ፈረሶቹ ሁለት ናቸው ግን አሳልፈኝ አሳልፈኝ ይባባላሉ" እንደሚባለው ብሂል ነው::

ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ላይ የምታቀርበው በቂ የሰነድ ማስረጃና ታሪካዊ እውነት እንዳላት ግልጽ ነው፡፡ ‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’ የሚል አምላክን እስካመነች ድረስም የተሻለውና ዋጋ ቢከፈልለትም የማያስቆጨው አካሔድ ይኼው ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን መብትዋን የምታስከብረውም ታሪካዊ ሰነዶችን ፎቶ እያነሱ በማኅበራዊ ድረገጽ በመለጠፍ ወይንም ጊዜያዊ ትኩሳትን ተንፈስ በሚያደርጉ መግለጫዎች ብቻ ሳይሆን የሕግ ሰዎችን ፣ የመሬት ሰነዶች ላይ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ፣ የዘርፉ ኤክስፐርቶች የሆኑ ልጆችዋን ያቀፈ አካልን እንዲወክላት በማድረግ ጉዳዩን በተገቢው ትኩረት እንዲፈታ በማድረግ ነው፡፡ ይህንን በማድረግ ችግሮችን ሌላ ተጨማሪ ችግር ሳይፈጥሩ መፍታት ይቻላል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ችግሩን ብቻ ማውሳት ምእመናን የተጠቂነት ስሜት ውስጥ እንዲገቡ ከማድረኛ ቤተ ክርስቲያንዋንም ክብር ከማሳጣት ያለፈ ጥቅም የለውም፡፡

2. መስቀል አደባባይን ‘የመስቀል አደባባይ’ ማድረግ

እንደሚታወቀው መስቀል የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ በዓልዋ መሆኑ የታመነ ነው፡፡ ሆኖም የመስቀል በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ይልቅ ፌስቲቫላዊ ቅርፁ በጣም የሚያይል አከባበር ያለው በዓል ነው፡፡

እንደሚታወቀው በበዓሉ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ከምትጠቀምበት ሰዓት ይልቅ የተለያዩ የፖለቲካ ሰዎችና ተጋባዥ እንግዶች ርዝመቱ የማይገመት ንግግር የሚያደርጉበት ሰዓት ይበዛል፡፡ የቤተ ክርስቲያንዋም አካላትም ከመንፈሳዊ ስብከት ይልቅ መንግሥትንና ተጋባዥ ዲፕሎማቶችን ማእከል ያደረገ ‘የተከበሩ አቶ እገሌ’ የሚበዛው ንግግር ሲያደርጉበት ይስተዋላል፡፡ በዓለ መስቀልም ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለመዳሰስ ሰበብ ሆኖ ያገለግላል እንጂ ወደ አደባባዩ መጥቶ ስለ ጌታችን መስቀል ምንም ዓይነት ነገር ሰምቶ የሚሔድ ምእመን የለም፡፡ በደርግ ዘመን እንኳን ከብዙ ችግር ጋር እነ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሰበኩት ‘ዮም መስቀል ተሰብሐ’ የሚል ስብከት ተጠቃሽ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን መስቀል አደባባይ ላይ የሚተላለፉ መልእክቶች እንዴት በዓሉን ከወቅታዊ ትኩሳት ጋር እናስተሳስረው በሚለው ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ መስቀል አደባባይ በአግባቡ ምሕላ እንኳን ደርሶበት አያውቅም፡፡ ሐቁን ለመናገር እንደ መስቀል በዓል አከባበርም መስቀሉን የሚቀብር ተራራ የለም፡፡

የምእመናን በዓል እንደመሆኑ ከውጪ የሚመጡ እንግዶች ሕዝቡ በዓሉን ሲያከብር መመልከት ሲገባቸው በመስቀል አደባባይ ግን ሕዝቡ የውጪ እንግዶች በዓሉን ሲያከብሩ ከሩቅ ሆኖ ይመለከታል፡፡ ነፋስ የሚያማታውን የስፒከር ድምፅ እየተከተለ ጭብጨባ ሲሰማ ያጨበጭባል፡፡ የአደባባዩ መርሐ ግብር አስተዋዋቂ አሁን እንዲህ እየተከናወነ ነው ሲል እየሰማ ሥፍራው ላይ ያለው ሕዝብ በቤቱ በቴሌቪዥን ከሚመለከተው ሰው ያነሰ መረጃ ኖሮት ተደናብሮ ይመለሳል፡፡ አንዳንዴም ደመራው ቶሎ አልበራ ሲለው በፉጨትና በጭብጨባ ፍጠኑ ይልና ሕዝቡ ራሱ ጧፍ በመለኮስ በዓሉን ያስጀምራል፡፡
አንድ ስብከት ሳይሰበክ ፣ አንድ መዝሙር በወጉ ሳይሰማ ሊቃውንቱ ፣ መዘምራኑ የኦሎምፒክ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት እንደሚታዩት አትሌቶች ምንም ሰዓት ሳያገኙ በጥድፊያ አልፈው እንዲያልፉ ይደረጋል፡፡ አብዛኛው የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣትና የማኅበራት መዘምራን መስቀል ሲመጣ እንደ ትልቅ አገልግሎት የሚያዩት ከበዓሉ ዕለት ይልቅ ለበዓሉ ሲዘጋጁ የሚያቀርቡትን ዝማሬና ወደ አደባባዩ እስከሚደርሱ ድረስ በመንገድ ላይ የሚዘምሩትን ዝማሬ ነው፡፡ የልዩ ልዩ ሚዲያ ጋዜጠኞችም መስቀሉን መቅበራቸው የተለመደ ነው፡፡ ‘የዘንድሮን የመስቀል በዓል ካለፈው ዓመት የተለየ የሚያደርገው ግድቡ በተገባደደበት ማግስት ላይ በመሆናችን ሲሆን’ የሚል ዘገባ ያቀርባሉ፡፡

አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ለቃለ መጠይቅ ያቀርቡና ‘መስቀል ከሃይማኖታዊነቱ ባሻገር ለሀገር የሚያበረክታቸው እሴቶች ምን ምን ናቸው?’ ‘የመስቀል በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ያለው ጠቀሜታ ምንድን ነው?’ የሚሉ በየዓመቱ እንደ ችቦው የማይቀሩ ችክ ምንችክ ያሉ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ በማግስቱም የመንግሥት ሚዲያዎች ስለ ክትፎ አሠራርና ስለ ቆጮ አዘገጃጀት ቀኑን ሙሉ ሲያብራሩና ዘፈን ሲጋብዙ ይውላሉ፡፡ ታሪኩን የማያውቅ ሰው ንግሥት እሌኒን የጉራጌ ንግሥት ፣ መስቀሉም ከክትፎ ውስጥ ተቆፍሮ የተገኘ ሊመስለው ይችላል፡፡

ብቻ በአጭሩ መስቀልን ሲያስታውስ አንድ ነገር ጨበጥሁ የሚል ሰው ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ደመራው የሚለኮስበት ውብ ሰዓት ላይ ብቻ ሕዝቡ በእልልታና በጧፍ እያጀበ ሰውነትን የሚነዝር ዝማሬ ያቀርባል፡፡ አሁን አሁን ቀረ እንጂ ደመራው የወደቀበትን አቅጣጫ እንደ ሀገሪቱ ፖለቲካ ኮምፓስ ቆጥሮ ወዴት ወደቀ ብሎ በጭንቀት የሚጠይቅም ብዙ ሰው አለ፡፡ ከዚያ በኋላ መስቀል አደባባይ ለሰዓታት ብቻ መስቀሉን አክብሮ አገልግሎቱ ያበቃል፡፡