Get Mystery Box with random crypto!

ለማንም እንዳትናገር! መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የአንድን ዲዳና ደንቆሮ አንደበት ‘ተከፈት’ ብሎ በአ | ዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ Henok Haile

ለማንም እንዳትናገር!
መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የአንድን ዲዳና ደንቆሮ አንደበት ‘ተከፈት’ ብሎ በአምላካዊ ኃይሉ ከፈተ፡፡ ይህንን ካደረገ በኋላ ግን ‘ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት’’ (ማር 7:36)
‘አትንገር ብዬ ብነግረው አትንገር ብሎ ነገረው’ ይሏል እንግዲህ ይኼንን ነው፡፡

የመልካም ሰውነት አንዱ መለኪያ ምሥጢር ጠባቂነት ነው፡፡ እውነተኛ ባልንጀርነትም ምሥጢርን መስማት ሳይሆን የሰሙትን ጠብቆ መያዝ ነው፡፡ ይህ የሚሆንላቸው ሰዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ይከበራሉ በፈጣሪም ዘንድ ዋጋቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ በምድርም ቢሆን ለከፍተኛ ሓላፊነት የሚታጩትና ከፍ ያለ ክብር የሚሰጣቸው ሰዎች በማሰቃያ ሥፍራ ሳይቀር እየተንገላቱ ምሥጢር የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው፡፡

አንዳንድ ሰው ግን የሰማውን ምሥጢር ለሌላ ሰው ለማዝረክረክ ማሰቃያ አያስፈልገውም፡፡ አትንገር የተባለውን እስኪናገር ድረስ ሆዱን ይቆርጠዋል፡፡ እግሩን እሾህ የወጋው ሰው እስኪነቀልለት ድረስ እንደሚንገበገብ ይህ ዓይነት ዓመል የተጠናወተውም ሰው ምሥጢሩን ለሌላ ሰው እስኪያሰማ ድረስ ይንቆራጠጣል፡፡ ‘ቀሊል ሰው’ ይለዋል ጠቢቡ ሲራክ
ምሥጢር ጠባቂነት ለወታደር የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፡፡ በኮድ ማውራት ግድ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ለሐኪም የሙያ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ለጠበቃ የጥብuቅና ፈቃድን ላለማጣት የሚጠበቅ ሕግ ነው፡፡ ለካህናት የንስሓ ልጆችን የመጠበቅ ሰማያዊ ቃልኪዳን ነው፡፡ ዓለም የምትናወጸው በዚህ መርሕ ኖረው ምሥጢር በማይጠብቁ ሰዎች ነው ማለት ይቀልላል፡፡

#Share
@diyakon_henok_haile

2. ጌታችን ያደረገው ፈውስ ቢሆንም ማስታወቂያ ሥሩልኝ ግን አላለም:: እንዳይናገሩ አዝዛቸው:: ከዚህም የምንማረው ብዙ ነው:: የሰውን መልካም ነገርም ቢሆን ምሥጢር መጠበቅ የግድ ነው፡፡ ለዚያ ሰው ሥራ እንቅፋት ላለመሆን ሲባል ዝም ማለት እርዳታ ነው:: የሰውን ኃጢአትና ነውር መደበቅ ደግሞ "ከባቴ አበሳ" (በደልን ሸፋኝ) አስብሎ በፈጣሪ ክብር ያስገኛል::

ሙሴን ወደ ስደት የዳረገው ምሥጢር መቋጠር የማይችል እስራኤላዊ ነበር፡፡ ሙሴ ለእርሱ አግዞ ግብጻዊውን ገድሎ ቢቀብርና ነጻ ቢያወጣው ‘አመስጋኝ አማሳኝ’ /አመስጋኝ አጥፊ/ እንዲሉ ሔዶ ወሬውን ነዛው፡፡ ወሬው በአጭር ጊዜ ተዳርሶ እስከ ፈር ኦን እልፍኝ ደረሰ፡፡ በአንድ መቋጠር በማይችል ወንፊት ሰው ምክኛት ሙሴ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ የዱር ስደተኛ ሆነ፡፡

ጌታችን በዚህች ምድር ሲመላለስ ተአምራቱን እንዳይናገሩ ያደርግ የነበረው ተአምራቱ ቢነገሩ የሚጎዱ ሆነው አልነበረም፡፡ በአንድ ወገን መከራ ከፊቱ አስቀምጦ ክብርን መፈላለግ እንደማይገባ ሲያስተምረን ሲሆን በሌላ በኩል ግን ከጊዜው በፊት መከራን ሊያደርሱበት እንዳይነሳሱና የመጣበትን ዓላማ ቅድሚያ መፈጸም እንደሚገባው ሲያስረዳ ነበር፡፡
ምሥጢር መጠበቅ በጎ ዕቅድንም ይጨምራል፡፡ ያለ ጊዜው የወጣ በጎ ዜናም ሆነ ዕቅድ በአፍ ይቀራል፡፡ ሳይሠራ ፈተና ይበዛበታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳይሠሩ ቀድሞ ‘እሠራለሁ’’ ብሎ ነጋሪት መጎሰም ለጠላት ማንቂያ ደወል ነው፡፡ አበው ‘የሰይጣን ጆሮ አይስማ’ የሚሉት ለሰይጣን ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንድ ነገር ሳይሠራ ተወርቶ ይዳረሳል፡፡ ክፋቱ በጣም ያወራከው ነገር የሰራኸው የሚመስልህ ነገር ነው፡፡ ብዙ ካወራህ በኋላ ያወራኸውን ከሰራኸው ለመለየት መቸገርህ አይቀርም፡፡ ዝም ብሎ መሥራትን የመሰለ ደግሞ ምንም ነገር የለም፡፡ ችግሩ ‘አሣ ሳትይዝ አሣ እጠብሳለሁ አትበል’ እንደሚባለው ከሥራ ማኒፌስቶው መቅደም የለበትም::

#Share
@diyakon_henok_haile

3. አንዳንዴ ደግሞ "በምሥጢር እየሥራ" መሆኑን የሚያወራም ሰው አለ:: ጳውሎስ ኞኞ በጻፈው አሁን የማላስታውሰው ጽሑፍ ላይ በድሮ ዘመን ደረታቸው ላይ "የምሥጢር ፖሊስ" የሚል ጽሑፍ የተለጠፈባቸው ሰላዮች ነበሩ ይባላል:: ምሥጢሩም እንዳይቀር ጉራውም እንዳይቀር ነው ነገሩ:: እንዲህ ያለ ነገር ስንት ሥራ አበላሽቶአል መሰላችሁ?!
ዝም ማለት የቻለ ተቋም ወይም ግለሰብ ባይሠራ እንኳን ዝምታው ግርማ ይሆነዋል፡፡ ‘ሬሳ የሚፈራው ለምንድር ነው? ቢሉ ዝም ስለሚል’’ ይባላል፡፡ ዝም የሚል ወገን ባይሠራ እንኳን ‘ዝም ያለው ምን እየሠራ ነው?’’ ያሰኛል፡፡ መረዳት ከቻልን ውስጥ ውስጡን የልባቸውን እየሠሩ ፣ በፈለጉት ቦታ የፈለጉትን እያስቀመጡ ፣ ንብረት እያፈሩ ፣ እየተደራጁ ጸጥ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ላይ ላዩን ደግሞ እያወሩ ምንም የማይሠሩ ዓለምን ሞልተዋታል፡፡
ሥጋትንህንም ሁሉ መደበቅ አንድ ብልህነት ነው፡፡ አንዱን ሰውዬ ዘራፊዎች አግኝተው ቅጥቅጥ አደረጉት ይባላል፡፡ ኪሱን ሲፈትሹ ግን ያገኙት አምስት ብር ብቻ ነው፡፡ ብስጭት ብለው ‘’አንተ ለ አምስት ብር ብለህ ልትሞት ነበር እንዴ?’’ ሲሉት ‘አይ እኔማ ካልሲዬ ውስጥ የደበቅኩትን አምስት መቶ ብር ትወስዱብኛላችሁ ብዬ ፈርቼ ነው’ ብሎ አረፈው፡፡
በዚህ ዘመን አንደበትን ያለመሰብሰብ ችግር እንደዚህ ሰውዬ እየጎዳንም ነው፡፡ እንዲህ ሊያደርጉ ነው ፣ እንዲህ ሊሠሩ ነው ወዘተ በሚል ጥቆማ ተበረታትተው ብዙ ክፉ የሠሩና የሚሠሩ ዘራፊዎች አሉ፡፡ አንዳንዴም እንደ ባለ አምስት መቶ ብሩ ሰውዬ ያላሰቡትን ያሳሰብናቸው ቀማኞች አሉ፡፡ የማይተዋወቁትን ሰዎች ሳናውቅ አብረን ሰድበን አንድ ያደረግናቸው ፣ የማይታወቁትን ሰዎች በነቀፋ ጀግና ያደረግናቸው ብዙ ናቸው፡፡
የዚህ ዘመን መሻገሪያ ወርቃማ ሕግ አንደበትን መቆጠብ ፤ የቻለ ድምጽ አጥፍቶ በጎ መሥራት ፣ ያልቻለም የሚሠሩ ሥራዎችን በአንዳንድ ነጋሪቶች አለማደናቀፍ ነው፡፡

‘ኢየሱስም ያዩትን እንዳይናገሩ አዘዛቸው’’

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
#Share
@diyakon_henok_haile