Get Mystery Box with random crypto!

የሐምሌ 11 የአንዋር መስጅድ ትዝታዬ(‹‹ጥቁር ሽብር››) አንድ ወንድማችን ሐምሌ 11/2006( | ከሁሉም ፈሰስ ፈሰስ ኢስላሚክ የእውቀት ግብይት ማግኛ

የሐምሌ 11 የአንዋር መስጅድ ትዝታዬ(‹‹ጥቁር ሽብር››)

አንድ ወንድማችን ሐምሌ 11/2006(ከ 7 አመት በፊት) በመንግስት የተፈፅመውን ‹‹ጥቁር ሽብር›› አስመልክቶ ትዝታውን በእንዲህ መልኩ አስቀምጦ ነበር። የተወሰኑ የቃላት ግድፈቶችን በማስወገድ እንደወረደ አቅርቤዋለው።

ዕለተ አርብ ሐምሌ 11/2006 እኔና ጓደኞቼ ሁሌ እንደምናደርገው በዕለቱ ለነበረው የተቃውሞ መረሀ ግብር
ተዘገጃጅተን በጊዜ ነበር ወደ አንዋር መስጅድ ያቀናነው፡፡
አንዋር መስጅድ በደረስንበት ወክት ከወትሮው በተለየ መልኩ የከተማ ፖሊሶችና የፌደራል ፖሊሶች የመስጂዱን
ዙሪያ ውርር አድርገውት ነበር፡፡ እኛም ጊዜው እስኪደርስ
ብለን በአንዋር ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ እየቃኘን ቆየን፡፡
ህዝቡ ከየ አቅጣጨው ወደ አንዋር መስጅድ እየጎረፈ ነበር፡፡

ሰዓቱ እየደረሰ ሲመጣ የአንዋር መስጅድ ጊቢው ሞላና
ህዝቡ ወደ ውጭ በመውጣት አስፓልት ላይ ማንጠፍ
ጀመረ፡፡ እኔና ጓደኞቼ ሁሌ የምንሰግደውና ተቃውሞም
ለማሰማት ምቹ የሆነውን ከአንዋር መስጅድ በዋናው
መግቢያ ዝቅ ብሎ ያለው መስቀለኛው መንገድ መሃል
አንጥፈን ቁጭ አልን፡፡ በዚያ ሰዓት ከተክላይማኖት ወደ ጎጃም በረንዳ ፣ ከአሜሪካን ጊቤ ወደ ጣና አቅጣጫ የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ አስፓልቶቹ በህዝብ ተሞልተው ነበር፡፡

በመሃል የህዝቡን ብዛት ለማየት ቆሜ ወደ ኃላዬ ማለትም
ወደ ተክላይማኖት አቅጣጭ ስመለከት መጨረሻው
አይታይም ነበር፡፡ ኮማንደር ጣሃ ኹጥባውን አንብቦ
አልጨረሰም ግና ኹጥባው ወደ መገባደዱ ነበር፡፡ በዚህ
ሰዓት የተለያየ መልዕክት የሰፈረባቸው ወረቀቶችና
ፖምፖሌቶች በየአቅጣጫው መበተን ጀመሩ፡፡ እኔና
ጓደኞቼም በጀርባችን ወሽቀነው የነበረውን ወረቀት
በማውጣት በትነን የየድርሻችንን ተወጣን፡፡ በዚህ ሰዓት
የከተማ ፖሊሶችና ፌደራሎች ደር ዳር ይዘው ሁኔታውን
በጥሞና ሲቃኙ ነበረ፡፡ እስከዚህ ሂደት ድረስ ከሞላ ጎደል
ሁሉም ነገር ሰላም ነበር፡፡

ችግሮች መፈጠር የጀመሩት ከዚህ በኃላ ነበር፡፡ በድንገት
ከፊት ለፊታችን ግርግር ተነሳ፡፡ ከፊት ያሉት ወንድሞቻችን
ወደኃላቸው መገስገስ ጀመሩ፡፡ ባለሁበት ቦታ እንደቀሞኩኝ
የሆነውን ነገር በትክክል ባለውቅም የጩሃት የሲቃ ድምፅ
እየተሰማኝ ነበር፡፡ ህዝቡ ወደኃላው መፈግፈጉን ታያይዞታል፡፡ ፖሊሶችና ፌደራሎች ህዝቡን ያለ ርህራሄ በጭካኔ መደብደብ ጀምረዋል፡፡ ህዝቡ ድብደባውን ሽሽት ወደ ኃላው ይሮጣል፡፡

ፌደራል ፖሊሶች በርካቶችን ደብድበው አስፖልት ላይ
ዘረሯቸው፡፡ ህዝቡ ወዲያ ወዲህ ይሯሯጣል ፣ በዚህ መሃል
ፌደራሎቹ ድብደባቸውን ቀጥለዋል፡፡ በፌደራል ፖሊሶቹ
በኩል ያለተለመደ ነገርም ታየኝ ...ፌደራሎቹ በዱላ
ያልደረሱበትን ድንጋይ በመወርወር መፈነካከት ጀመሩ፡፡
በርካቶች አናታቸው ተተርክኮ ራሳቸውን ስተው አስፓልት ላይ
ወደቁ፡፡ የሚያናሳቸው በሌለበት የሚሮጠው ህዝቡም
ፌደራሉም ፖሊሱም እየረጋገጣቸው ማለፍ ጀመረ፡፡ አስፓልቱ በደም ጨቀየ፡፡ በድንገት ህዝቡ በተራው ፌደራሎቹን በመልሱ ማጥቃት አይነት እያሯሯጠ አባረራቸው፡፡ ፖሊሶቹ ወደ ጎጃም በረንዳ መስመር ፈረጠጡ፡፡ በሩጫው መሃል አንዱ የፖሊስ መኪና አንዱን ፖሊስ ገጨውና ፖሊሱ አስፓልት ወደቀ፡ ይሙት ይዳን አላውቅም፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች አስፖልቱ በህዝቡ ቁጥጥር ስር ሆነ፡፡

እኛ ለመስገድ ባንታደልም መስጅዱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የነበሩት ሶላት ሰግደው ጨርሰው ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዳለን አከባቢው በብረት ለበስ ፌደራል ፖሊሶች ተጥለቀለቀ፡፡ ሁኔታው ያላማረው ህዝብ ተበታተነ፡፡ ፌደራሎቹ አሁንም ያገኙትን ሁላ ህፃን፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳይለዩ መደብደብ ጀመሩ፡፡ በዚያ ሰዓት የአንዋር መስጅድ ሁለቱም በሮች ተከርችመው ወደ ውስጥ መግባትም ሆነ መውጣት አይቻልም ነበር፡፡ በርካቶች አስፓልት ላይ ራሳቸውን ስተው እንደወደቁ፣ አስፓልቱ በደም እንደጨቀየ ሁሉም ወደ አንዋር መስጅድ የሚወስዱ መንገዶች በፌደራል ፖሊሶች ተዘጋጉ።

በወቅቱ እኔ የአሜሪካን ጊቢ ልጅ ባልሆንም ከዚያው ሰፈር
ልጆች ጋር በአካባቢ ነበርኩኝ፡፡ ወደ ጓደኞች ስልክ ስደውል ከመደብደብ ውጭ እንዳልተያዙ ነገሩኝ፡፡ ፌደራሎች አስፓልት ላይ የወደቁት ጎትተው እየጫኑ ወደ ህክምና ጣቢያ ሳይሆን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው፡፡

ከዚያ በኃላ ሀሳቤን መስጅዱ ውስጥ ወዳሉት ሁለት እህቶቼ
በማዞር ስልክ ደወልኩኝ ግን አይነሳም፡፡ ከዚያ አንደኛዋ እህቴ የኔን ሰላም መሆን ከጠየቀችኝ በኃላ በሩ እንደተዘጋና
በፌደራሎች እንደተከበቡ ነገረችኝ፡፡ እኔ ወደ ቤት ሳልመለስ
ከስፍራው ራቅ ብዬ ሁኔታውን መቃኘት ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ
ሰዓቱ እየመሸ ነበር፡፡ በመጨረሻ ጥቂቶች በዕድሜ የገፉ
አባት እናቶች ብቻ ተለቀው በመስጅዱ በሴቶችም
በወንዶችም በኩል የነበረው ሁሉ ታፍሶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ
ተወሰደ፡፡ ልጆቻቸው የተያዙባቸው አባቶችና እናቶች አንዋርና ዙሪያው ሆነው እየተጨነቁ ነበር፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኃላ የነበረውን ሁኔታ ማየት ስላልቻልኩኝ ያወኩት እህቴ ከተፈታች በኃላ ነበር፡፡

ፖሊስ ጣቢያ ከደረሷቸው በኃላ ሂጃባቸውን አስወልቀው
ፀጉራቸውን እየነጩ፣ ልብሳቸውን ሰብስበው ኮሮኮንች ላይ
በጉልበታቸው እንዲሄዱ እንዳደረጓቸው፣ በቦርሳቸው ቁርዓን
የያዙትን እየቀሙ ቁርዓኑን ከነቦርሳው እንዳቃጠሉት
እያለቀሰች ነበር የነገረችኝ፡፡ በርካቶች ፖሊስ ጣቢያው
ውስጥ በዚያ ምሽት በዚያ ብርድ ከድብደባ ብዛት ተጎድተው ራሳቸውን ስተው ቢወድቁም ወደ ህክምና ቦታ
የሚወስዳቸው ግን አልነበረም፡፡

በዚህ ስቃይ ውስጥ ሆነው የሌሊቱን አብዛኛውን ክፍል ካሳለፉ በኃላ ግማሹን አስቀርተው ግማሹን ደግሞ ከሌሊቱ 9፡30 አከባቢ ከፖሊስ ጣቢያ እየደበደቡ እውጥተው አባረሯቸው፡፡ በዚያ ውድቀተ ሌሊት-ትሪንስፖርት በማይገኝበት ፣ ማደሪያ በማይገኝበት ሊያውም
ሴትን ልጅ ለዘራፊ ለደፋሪ መደሰቻ ሆኚ ብለው አውጥተው
አበረሯቸው፡፡ ደግነቱ በፖሊስ ጣቢያው አካባቢ የነበሩ
ሙስሊሞችና የሌላ እምነት ተከታይ የሆነ ሰዎች ሴቶቹን ወደ ቤታቸው በማስገባት አሳደሯቸው፣ ምግብ ሰጣቸው፡፡

እህቶች ቤት የደረሱት ጠዋት ነበር፡፡ የስጋ እህቶቼ ቤት ቢደርሱም ሌሎች በርካታ ሙስሊም እህቶቼና ወንድሞቼ ግን በየማጎሪያው ታጎሩ፡፡ ያለምንም ክስ ለበርካታ ቀናትና ወራት በእስር አሳለፉ፡፡ የተወሰኑት በጊዜ ሂደት ቢፈቱም በዚያ ቀን ተይዘው ጥፋተኛ ናችሁ ተብለው ተፈርዶባቸው እስካሁንም እስር ቤት ያሉ በርካቶች ናቸው፡፡

ታዲያ ያንን በአንባገነኑ የህወሃት መንግስት የተፈፀመ የቡዙዎች እንባና ደም የፈሰሰበት፣ የቡዙዎች አካል የጎደለበት በእትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ጥቀር የስቃይ ጠባሳ ጥሎ ያለፈን ይህ ቀን መቼም ቢሆን ከአእምሮዬ አይጠፋም፡፡
ስለፍትህ እንጮሀለን፣ ሠላምን እንሰብካለን፣ አንድነትንና መከባበርን እንሻለን!