Get Mystery Box with random crypto!

ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማስፋት በህግ ተማሪዎች መካከል ትምህርታዊ ክርክር ተካሄደ = | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማስፋት በህግ ተማሪዎች መካከል ትምህርታዊ ክርክር ተካሄደ

==================

ደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ | መጋቢት 09/2015 ዓ.ም | ህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ዳይሬክቶሬት |
| ደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ ህግ ት/ቤት ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል፣ ከምስራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ፣ ከከፍተኛ ፍ/ቤት የመጡ የስራ ኃላፊዎች ፣ የዩንቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና መምህራን እንዲሁም ተማሪዎች በተገኙበት የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ የበይነ መረብ መዘጋት ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? በሚል በተማሪዎች መካከል ትምህርታዊ ክርክር ተካሂዷል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ይሄይስ አረጉ(ዶ/ር) ህግ ት/ቤት ትውልድን ከማነፅ አንፃር በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ እና አሁንም ለተማሪዎች የነፃ ሀሳብ መግለጫ መድረክ መመቻቸቱ ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ወቅታዊ፣ ወሳኝና በሳል ሀሳብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዩንቨርሲቲው የህግ ት/ቤት ዲን መምህር አማረ ስጦታው በበኩላቸው ህግ ት/ቤት በትምህርት ጥራት፣በማህበረሰብ አገልግሎትና በምርምሩ ዘርፍ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚጠቀሙባቸውና ልምድ ከሚለዋወጡባቸው ፕሮግራሞች መካከልም ትምህርታዊ የክርክር መድረክ አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም የሰብአዊ መብቶች ክበብ ከተቋቋመ ጀምሮ ስልጠናዎችን በማመቻቸት፣ ማህበረሰቡ ለሰብአዊ መብቶች ያለው ግንዛቤ እንዲዳብርና ለሰብአዊ መብቶች መከበር የድርሻውን እንዲወጣ በትጋት እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል የሰብአዊ መብት ጥበቃና ምርምር ኦፊሰር አቶ ኖህ የሱፍ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የሰው ልጅ መብቶች የማክበር ባህል እንዲዳብር በተለይም ወጣቶች የሌሎችን ሰብአዊ መብቶች በማክበር እንዲታነፁ ለማድረግ ስልጠና በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ እስካሁን ከ10 በላይ በሚሆኑ ዩንቨርሲቲዎች ክበባትን በማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ለተማሪዎች የክርክር መድረክ መፈጠሩም በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ ክህሎታቸውን አዳብረው ፣ መብታቸውን አክብረው የሌሎችን መብት እንዲያስከብሩ እና በሀሳብ የበላይነት እንዲያምኑ ያስችላል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ክበቡን ከማቋቋም ጀምሮ ለፕሮግራሙ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የዩንቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ለህግ ት/ቤት ዲንና መምህራን እንዲሁም ተማሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ክርክሩን ካካሄዱት ተማሪዎች መካከል የ4ኛ ዓመት የህግ ት/ቤት ተማሪ ያሬድ ሙሌ በዚህ ክርክር ላይ ስንሳተፍ በንድፈ ሃሳብ የምናውቀውን ትምህርት በተግባር ለማሳየት፣ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር፣በራስ መተማመንን ለማዳበርና በትምህርት ህይወታችን በደንብ ታንፀን ስለምንወጣ ህጉን በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል ሲል ተናግሯል፡፡

ተማሪ ሀይማኖት ይበልጣል በበኩሏ ሀሳባችንን በታዳሚዎች ፊት በነፃነት ስንገልፅ የንግግር ክህሎታችንን ለማዳበርና የተለያዩ ጉዳዮችን ከተለያዩ ሀሳቦች አንፃር የመተንተን ክህሎታችንን እንድናዳብር ይረዳናል ብላለች፡፡

በክርክሩ የተሳተፉ ተማሪዎች ለወደፊት ቀጣይነት እንዲኖረዉና ሁሉንም ተማሪዎች ያሳተፈ ሊሆን እንደሚገባው አሳስበው ይህን መድረክ ላዘጋጁላቸው አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ክበቡ ከተቋቋመ ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ 2 የህግ ት/ቤት መምህራን የክበቡ አባላት የሰዓት ሽልማት አበርክተዋል፡፡እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ለፕሮግራሙ መሳካት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንድሁም ክርክሩን ለተሳተፉ 4 ተማሪዎች በአጠቃላይ የ10,000ብር የገንዘብ ሽልማት በማበርከት ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

የዕውቀት አውድማ ከጮቄ ማማ

==========

ለተጨማሪና አዳዲስ መረጃዎች


#ቴሌግራም
https://t.me/Debre_Markos_University

#ፌስቡክ
https://www.facebook.com/dmu.edu

#ዩቱዩብ https://www.youtube.com/channel/UCqQDHEyYDen3aybySpYsF_Q