Get Mystery Box with random crypto!

የመውጫ ፈተና (Exit Exam ) የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር ከመጡ | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

የመውጫ ፈተና (Exit Exam ) የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር ከመጡ የስራ ኃላፊዎች ጋር ወይይት ተካሄደ ተካሄደ

===================

ደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ | የካቲት 28/2015 ዓ.ም |ህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ዳይሬክቶሬት | በ2015 ዓ.ም የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና ውጤታማ ለማድረግ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለተመራቂ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ግብዓቶችን እስከማሟላት ድረስ ሰፊ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡ የስራ ኃላፊዎች አጠቃላይ ዝግጅቱ ምን እንደሚመስል ግምገማ አካሂደዋል፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር የዩንቨርሲቲ ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ዳንኤል የመውጫ ፈተና የትምህርት ጥራት የሚለካበት ተማሪዎች ብቁና ተወዳዳሪ መሆናቸው የሚለይበት ዋነኛው መንገድ እንደሆነ በመግለፅ በዚህ ዓመት በዩንቨርሲቲዎችገልፀው የአይሲቲ መዋቅር ፣ ኤሌክትሪክሲቲ አቅርቦት ፣ ኢንተርኔት ፣ የሰው ኃይልና የተማሪዎች ዝግጅት በስፋት የሚሰራባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ አንስተዋል፡፡

አያይዘውም በትምህርት ሚኒስትር በኩል በተለያዩ የመንግስትና የግል ሚዲያዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ፣የህግ ማዕቀፍ (የአሰራር ስርዓት መመሪያ የማዘጋጀትና ለተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች የፈተና ንድፍ አዘጋጅቶ ለዩንቨርሲቲዎች ተደራሽ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል። በዩንቨርሲቲዎች የተደረጉ ዝግጅቶችን በመገምገም አስፈላጊ ድጋፎችን ለማድረግ በተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች እየተዘዋወሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) የመውጫ ፈተና የእውቀትና የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላትና በተቋማት በኩልም የተወዳዳሪነት መንፈስን ለመፍጠር በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ከግብዓት መሟላት አንፃር አንዳንድ ጉድለቶች እንዳሉ የገለፁት ፕሬዚደንቱ ተማሪዎችን ከማዘጋጀት አንፃር ከሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በስነ ልቦናና በእውቀት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ለፈተናው መሟላት የሚገባቸው ቁሳቁሶች ተሟልተው በጥራት ለመስራት ትልቅ ወጭ ስለሚጠይቅ ትምህርት ሚኒስቴር የበጀት ሁኔታንም ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡

አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ይሄይስ ሐረጉ (ዶ/ር/ በበኩላቸው መውጫ ፈተና እንደሚሰጥ አቅጣጫ ከተቀመጠ ጀምሮ ተማሪዎችን በማነቃቃትና በማዘጋጀት ረገድ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑንና መምህራን ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ቲቶሪያል እየሰጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

የዕውቀት አውድማ ከጮቄ ማማ

=============

ለተጨማሪ እና አዳዲስ መረጃዎች



#ፌስቡክ https://www.facebook.com/dmu.edu

#ቴሌግራም https://t.me/Debre_Markos_University

#ዩቱዩብ https://www.youtube.com/channel/UCqQDHEyYDen3aybySpYsF_Q

#ዌብሳይት www.dmu.edu.et