Get Mystery Box with random crypto!

የሂሳብ መዝገብ አያያዝና የኦዲት ትምህርትን በተግባር ማስተማሪያ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችል አውደ | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

የሂሳብ መዝገብ አያያዝና የኦዲት ትምህርትን በተግባር ማስተማሪያ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችል አውደ ጥናት
ተካሄደ

=================

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ጥር 25/2015 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት)

ተማሪዎች በፅንሰ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር ለማየት ወደ ሌላ ቦታ ሳይሄዱ በዩንቨርስቲያቸው ውስጥ ተግባሩን እንዲማሩ ለማድረግ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የመጡ የሂሳብ አዋቂዎች፣የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት የተግባር ማስተማሪያ ማዕከሉን ለማቋቋም የሚያስችል ዐውደ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ይሄይስ አረጉ (ዶ.ር) በመክፈቻ ንግግራቸው የሳይንስ ትምህርት ዋና ተልዕኮው እውነትን በመፈለግ ችግርን መፍታት በመሆኑ የሚታይ፣የሚዳሰስ፣የሚኖር፣የሚሰራና የሚተገበር ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ፣ ንግድን ለማዘመንና የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት እንደነዚህ አይነት የተግባር ማዕከላት መቋቋማቸው አስፈላጊና የሚያስደስት ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአውደ ጥናቱ አቅራቢ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህር ደረጀ ብርሃኔ እንደገለፁት ይህ ማዕከል መቋቋሙ ተማሪዎች የፅንሰ ሀሳብ ዕውቀታቸውን ከተግባራዊ ዕውቀት ጋር አጣምረው ወደ ስራ ዓለም ሲገቡ ለተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ብቁ እንዲሆኑና ቀጣሪ ድርጅቶች፣ኢንቨስተሮች፣አበዳሪዎች፣መንግስት እና መሰል ተቋማት ከኪሳራና ከተሳሳተ ውሳኔ እንዲድኑ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

ዓላማውም ተማሪዎች ወሳኝ የሆኑ ሰነዶችን እንዲያውቁና እንዲለዩ፣ሰነዶችን መሰረት ያደረገ የሂሳብ መዝገብ እንዲይዙ፣በያዙት ሂሳብ መሰረት የፋይናንስ መግለጫዎችን እንዲያዘጋጁና ኦዲቶችን በትክክል እንዲሰሩ በማስቻል በቀጣሪ ድርጅቶች ተፈላጊና ተመራጭ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡