Get Mystery Box with random crypto!

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመስከረም 30 ጀምሮ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተፈታኞች | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመስከረም 30 ጀምሮ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተፈታኞች መብትና ግዴታዎች
--------------
#የተፈታኝ_መብቶች፡
➭ ከፈተና ጥያቄ ውጪ ማንኛውንም ያልተረዳውን ነገር ጠይቆ የመረዳት መብት አላቸው።
➭ በየኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ምግብ፣ የህክምና አገልግሎት፣ የማደሪያ ክፍል፣ ፍራሽና ትራስ የማግኘት መብት አላቸው።
➭ ማንኛውም ተፈታኝ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያለውን የቤተ መጽሐፍት፣ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የሻወር፣ የካፍቴሪያዎች፣ የሚኒ ሱፐር ማርኬቶች፣ የተለያዩ ሱቆች፣ የመናፈሻና መዝናኛ አገልግሎቶችን የመጠቀም መብት አላቸው።
➭ የኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የጋራ የደህንነት ጥበቃ የማግኘት መብት አላቸው።
➭ በፈተና ሰዓት መፈተኛ ክፍል ገብቶ ብርሃናማ የመፈተኛ ቦታ፣ ወንበር፣ መጻፊያ ጠረጴዛ የማግኘት መብት አላቸው።
➭ ፈተና ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀድሞ ስለፈተናው ገለጻ (ኦሬንቴሽን) የማግኘት መብት አላቸው።
#የተፈታኝ_ግዴታዎች፡
➤ ማንኛውም ተፈታኝ በፈተና ማዕከልም ይሁን መፈተኛ ክፍል አድሚሽን ካርድ ይዞ የመገኘት ግዴታ አለበት።
➤ ማንኛውም ተፈታኝ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጣ የትምህርት ቤት #ወይም የነዋሪነት መታወቂያ ይዞ መገኘት አለበት።
➤ ማንኛውም ተፈታኝ ወደ ግቢ ከመግባቱ በፊትና ወደ መፈተኛ ክፍል ከመግባቱ በፊት ሙሉ አካላዊ ፍተሻ የመፈተሽ ግዴታ አለበት።
➤ ማንኛውም ተፈታኝ በዩኒቨርሲቲ ግቢና በመፈተኛ ክፍል የተከለከሉ ቁሳቁሶችን/ዕቃዎችን መያዝ የለበትም።
➤ ማንኛውም ተፈታኝ እርሳስ፣ ላጲስና የእርሳስ መቅረጫ ይዞ መገኘት አለበት።
➤ ማንኛውም ተፈታኝ የፈተና ደንብን የማክበር ግዴታ አለበት።
➤ ማንኛውም ተፈታኝ በፈተና ማዕከል ውስጥና በመፈተኛ ክፍል ውስጥ የፈተና አስፈጻሚዎች የፈተና አስተዳደር ሥራን ውጤታማ ለማድረግና ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚያደርጉትን ጥረት የመተባበር ግዴታ አለበት።
➤ ማንኛውም ተፈታኝ ፈተና ከመጀመሩ በፊት መፈተኛ ክፍል የመገኘት ግዴታ አለበት።
➤ ተፈታኙ ፈተናው ሳይጠናቀቅ ከፈተና ክፍል የሚወጣ ከሆነ የፈተና ጥያቄ የያዘውን ቡኩሌት ለፈታኙ የማሰረከብ ግዴታ አለበት።
➤ ማንኛውም ተፈታኝ ወደ ተመደበበት ዩኒቨርሲቲ ሲመጣ አንሶላ፣ ብርድልብስና የትራስ ጨርቅ ይዞ የመምጣት ግዴታ አለበት።
#ለተፈታኞች_የተፈቀዱ_ነገሮች፦
➣ አዲስ ወይም ቀድሞ ለመማር እና ለማጥናት ሲጠቀሙበት የነበሩ ማስተወሻ ደብተር ፣ የትምህርት መጽሐፍ፣ መንፈሳዊ/ኃይማኖታዊ መጽሐፍት፣ ባዶ ወረቀት
➣ እንደ አስፈላጊነቱ ደረቅ ምግቦች ወይም ሰንዱች ምግቦች (ጩኮ፣ በሶ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ቆሎ….)
 ገንዘብ (ብር)
➣ የልብስ ወይም የእጅ ቦርሳ፣ የግል ልብስ፣ ጫማ
➣ የግል ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ (ሳሙና፣ ሞዴስ፣ የጥርስ ብሩሽ፣ የጥርስ ሳሙና፣ የገላ ማድረቂያ ፎጣ፣ ሶፍት፣ ሻምፖ፣ ኮንዲሽነር፣ ሎሽን፣ ቻፕስቲክ፣ የጸጉር ቅባት፣ የፊት ቅባት)
#ለተፈታኞች_የተከለከሉ_ነገሮች፦
⮕ ማንኛውንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው፡፡
⮕ ማንኛውንም ዓይነት ስለት እና ሹልነት ያላቸውን ብረታ ብረቶችና ጠንካራ ፕላስትኮች ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው።
⮕ ማንኛውም ድምጽ የሚቀዳ፣ ፎቶ የሚያነሳ፣ ቪዲዮ የሚቀርጽ፣ ከቴሌ መስመርም ሆነ ከቴሌ መስመር ውጭ መልዕክት በዲጂታል መንገድ የሚሰጥ ወይም የሚቀበል የግል ዕቃ/መሳሪያ /ቴክኖሎጂ ውጤት፣ ስልክ፣ አይ-ፓድ፣ ታብሌት፣ ኮምፕዩተር፣ ላፕቶፕ፣ ስማርት ሰዓት፣ ማጂክ ብዕር/እስክሪብቶ፣ ማጂክ ኮት/ጃኬት እና ሌሎች ማንኛቸውም ፎቶ፣ ምስል እና ድምጽ የሚቀርጹ የኤሌክትሮኖክስ መሣሪያዎችን በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥም ሆነ ግቢ ዙሪያ ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡
⮕ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት የግል ፍላሽ ዲስክ፣ ሃርድ ዲስክ፣ ሲዲ፣ ሚሞሪ፣ ሚሞሪ ሪደር፣ ኦ-ቲጂ ኮንቨርተርና መሰል ዕቃዎችን ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡
⮕ ማንኛውም አደንዛዥ እጾች (ጫት፣ ሲጋራ፣ በሓኪም ማዘዣ የሌለው መድኃኒት (በሽሮፕም ይሁን በታብሌት፣ ህክምና መስጫ መርፌ) መያዝ ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡
⮕ ማንኛውም ዓይነት የአልኮል መጠጥ ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡
⮕ ማንኛውም ዓይነት የአንገት ሐብል፣ የጸጉር ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ የጣት ቀለበት፣ የእጅ አንባር፣ አድርጎ ወይም ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው፡፡ (ከልሙጥ የጋብቻ ቀለበት በስተቀር)
⮕ ፈተና ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ወደ ፈተና ክፍል መግባት እና ፈተናው ተጀምሮ 45 ደቂቃ ሳይሞላ ከፈተና ክፍል መውጣት የተከለከለ ነው፡፡ ⮕ ተፈታኙ ፈተናው ሳይጠናቀቅ ከፈተና ክፍል የሚወጣ ከሆነ የፈተና ጥያቄ የያዘውን ቡኩሌት ይዞ መውጣት ተከለከለ ነው፡፡
⮕ በፈተና ሰዓት በመፈተኛ ክፍል ውስጥ ማስቲካ መያዝም ሆነ መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡
⮕ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በግልም ሆነ በቡድን መጮህ ወይም በጣም ከፍተኛ ድምጽ ማሰማት የተከለከለ መሆኑን እያሳስብን በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢና ጤና ሳይንስ ካምፓስ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዲወስዱ የተመደቡልንን ወረዳዎችና ትምህርት ቤቶችንም ከታች አስቀምጠናል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ