Get Mystery Box with random crypto!

እንሰትን በአማራ ክልል ለምግብነት ለማላመድ የተቀረፀ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደብረማር | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

እንሰትን በአማራ ክልል ለምግብነት ለማላመድ የተቀረፀ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ
===============
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፣ መስከረም 14/2015 ዓ.ም (የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት) ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር በአማራ ክልል እንሰትን ለምግብነት ለማላመድ የተቀረፀ ፕሮጀክት ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚደንትን ጨምሮ ከተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ስራ አስኪያጆችና ባለሙያዎች፣ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንቶች እንዲሁም የተለያዩ የስራ ክፍል ኃላፊዎችና መምህራን፣ ጥሪ የተደረገላቸው የዞንና የወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ ።

በዚህ መርሐ ግብር ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ በሀገራችን ሀሳብን ፋይናንስ ማድረግ ባልተለመደበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ግን ሃሳባችን ተቀብሎ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣለን በማለት በሙሉ ፍላጎት ከእኛ ጋር ለመስራት በመወሰናቸው አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

አክለውም ፕሮጀክቱ በዘርፉ ፋና ወጊ እንደሆነ ገልፀው እንሰት በክልላችን አብሮን የኖረ ተክል ቢሆንም ከዳቦ ከመጋገሪያነት ውጭ ሳንጠቀምበት ኑረናል ፤ በአንፃራዊነት በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ህዝብ የምግብ ዋስትና እንደሆነ ጠቁመዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን ተሞክሮ ወደ አማራ ክልል ጎጃም በማምጣት እንሰትን (ቆጮን) ለምግብነት በማላመድ የማህበረሰባችንን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አለብን በሚል ሃሳቡን በምርምር በማስደገፍ ወደ መሬት አውርደው ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ላደረጉት የፕሮጀክቱ አባላት ምስጋና አቅርበዋል። ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

በመጨረሻም ይህ ፕሮጀክት ለዞናችን ብሎም ለክልላችን ህዝብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ስለሆነ በተሻለ መንገድ እንዲጠናቀቅ የዩኒቨርሲቲያችንም ሆነ የውጪው ማህበረሰብ ፕሮጀክቱ የእኔ ነው በሚል የቅንነት መንፈስ ሃላፊነታቸውን በጋራ እንዲወጡም መልክታቸውን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) በዚህ መርሐ ግብር ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ፕሮጀክቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና በምትልበት ወቅት የተጀመረ በመሆኑ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን አንስተዋል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የክልሉን ስነ-ምህዳር ከመጠበቅ አንፃርም የሚኖረው ሚና ጉልህ እንደሚሆን ገልፀዋል።

የእንሰት ተክል በርካታ መልካም የተፈጥሮ ባህርያትን የታደለ በመሆኑ ከሌሎች ተክሎች ይልቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተመራጭ እንደሆነም ጠቅሰዋል ።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንሰት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ዋነኛ ምግብ ምንጭ ነው። በመሆኑም የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ በአማራ ክልል በተለይ ድርቅንና እርሃብን ለመቀነስ እንሰትን ለምግብነት የማላመድ ፕሮጀክት በመተግበር አርሶ አደሮች የደረቀ ቆጮን በብዛት እንዲያመርቱ እና ለምግብነት ከማዋል ጎን ለጎንም ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ማስቻል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሀገርን ለማልማትና በተለይም በምግብ ራስን ከማስቻል ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የግብርና ምርምሮች እና የፈጠራ ሀሳቦች እንደሚያበረታታ ገልፀዋል።

ከዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የመጡት መምህር እና በእንሰት ላይ መርምር ያደረጉት ተመራማሪ ዳንኤል መኖር "የእንሰት ምርታማነትና ማላመድ" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፉ አቅርበዋል።

ባቀረቡት ፅሑፍ እንደገለጹት እንሰት በቆላማውም በደጋማውም የአየር ንብረት ክልል ውስጥ መብቀል የሚችል ተክል መሆኑንና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችም እንዳሉት አስረድተዋል። ከጠቀሜታዎቹም ውስጥ እንስት ለባህላዊ መድሀኒትነት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት፣ ለምግብነት ፣ ለቃጫ መስሪያነት፣ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የሚሉት ጥቂቶቹ እንደሆኑ አብራርተዋል።

የእንሰት ተክል የአየር ንብረት ለዉጥን በተለያየ ሁኔታ በመቋቋም ያለዉሃ ለበርካታ ጊዜያት መቆየት በመቻሉ ከተመረተ በኋላ እስከ 7 አመት ሳይበላሽ መቆየት ስለሚችል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እንዳለው በማስገንዘብ ፅሑፋቸውን አጠቃለዋል።

በመርሃ ግብሩ "እንሰትን" በአማራ ክልል ለምግብነት ማላመድ በሚል ርዕስ የተቀረፀው ፕሮጀክ ንድፈ ሃሳብ በዝርዝር ቀርቧል።

የፕሮጀክቱ ሀሳብ አፍላቂ መምህርና ተመራማሪ አቶ ባወቀ ጥሩነህ ካቀረቡት ፅሑፍ እንደተረዳነው ፕሮጀክቱ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትነት በቀጣዮቹ 10 አመታት ውስጥ እንደሚተገበርና የኢትዮጵያ ልማት ባንክም የፕሮጀክቱን የአንድ አመት ትግበራ ማስጀመሪያ በጀት የ2 ሚሊዬን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ነው።

በቀረቡት ሁለት ጥናታዊ ፅሑፎች ላይም ውይይት የተደረገ ሲሆን ጥያቄዎችና ጠቃሚ አስተያየቶችም ከተሳታፊ እንግዶች ተሰጥተዋል።

በመርሐ ግብሩ የማጠቃሊያ ንግግር ያደረጉት የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ታፈረ መላኩን (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ሲሆኑ በንግግራቸው ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሮጀክቱን ሙያዊና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ወደ ሁለገብ የተቀናጀ ፕሮጀክትነት እንዲያድግ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።