Get Mystery Box with random crypto!

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን ለመቀበል እየተዘጋጀ መሆ | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን ለመቀበል እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለፀ

==============

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፦ መስከረም 12/2015 ዓ.ም ( ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት)
ትምህርት ሚኒስተር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ መመሪያ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችንም ይህንን መመሪያ በመቀበል ተፈታኝ ተማሪዎችን ለመቀበል ልዩ ልዩ ግብረ ኅይሎችን በማዋቀር በሙሉ አቅሙ እየሰራ ይገኛል፡፡

በዩኒቨርሲቲያችን የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ይኼይስ አረጉ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው በዋናው ግቢ፣ በቡሬ እና በጤና ካምፓስ ከ36 ሺህ በላይ ተፈታኝ ተማሪዎችን ለመቀበል ላለፉት ሁለት ሳምንታት ቅድመ ዝግጅት ሲያደረግ እንደቆዬ ገልፀው የሚመጡት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች እስካሁን ዩኒቨርሲቲው ከሚያስተናግዳቸው መደበኛ ተማሪዎች በሶስት እጥፍ የጨመረ በመሆኑ ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን ግቢዎቻችንን ለፈተና ምቹ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ፈተናው በሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ከ26 እስከ 28/01/2015 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ ሲሆን በ29 አጠቃላይ ገለፃና ማብራሪያ እንደሚሰጣቸውና ከ30 እስከ 02/02/2015 ዓ.ም ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልፀዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ ኤሌክትሮኒክስ ነክ መሳሪያዎችን ይዘው እንዳይገቡ የተከለከለ ሲሆን አስፈላጊ መረጃዎችንም ወደፊት በሁሉም ሚዲያዎች ስለሚገለፁ ተፈታኝ ተማሪዎች መረጃዎችን በቅርበት በመከታተል ማክበርና መጠበቅ ያለባቸውን ነገር በመከታተል ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ይሄይስ አረጉ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲያችን አካዳሚክ ጉዳዮች ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር በለጠ ያዕቆብ (ዶ/ር) ተፈታኝ ተማሪዎችን ያለ ምንም እንከን ለማስፈተን ትምህርት ሚኒስተር በላከው መመሪያ መሰረት አንድ ዋና የፈተና አስፈፃሚ ግብረ ኃይል በማቋቋም በአስተዳደርና በአካዳሚክ የተከፋፈሉ ኮሚቴዎች ተዋቅረው የመፈተኛ ክፍል፣ የምኝታ ክፍል፣ የምግብ አገልግሎት፣ ልዩ ልዩ ጥገናና የፅዳት ኮሚቴዎች ተቋቁመው በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ፈታኝ መምህራንን በተመለከተም ከዋናው እና ቡሬ ካምፓስ 539 ፈታኝ ፣ 36 አንባቢ እና 17 ቆጣሪ ተመልምለው የስም ዝርዝራቸው ለትምህርት ሚኒስቴር መላካቸውን ተናግረዋል፡፡

የፀጥታውን ዘርፍ በተመለከተም ተማሪዎች ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲፈተኑና ንብረቶች እንዳይበላሹ ለማድረግ እንደተዘጋጁና የደህንነት ካሜራዎችን በጥንቃቄ ለመጠቀም ባለሙያዎችን ከወትሮው በተለየ አደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውን በዩኒቨርሲቲያችን ፀጥታና ደህንነት ዳይሬክተር ኮማንደር እሱባለው አላምር ገልፀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምግብ ዝግጅትና መስተንግዶ አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ ይታየው አለም በበኩላቸው የምግብ ቤት ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ ቁሳቁሶች ከተለዩ በኋላ በግዥ፣ በጥገናና በውሰት የሚሟሉትን ለይተን በየዘርፋቸው እያሟላን ነው ብለዋል፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት የመኝታ ክፍል አስተባባሪ አበቡ ዋለ ተማሪዎች ብዛት ያላቸው በመሆኑ የመኝታ ክፍል እጥረት ቢያጋጥመንም ክፍሎችን አመቻችተን ጥገና የሚያስፈልጋቸውንና በግዥ የሚሟሉትን የመኝታ ቁሳቁሶች ማዘጋጀታቸውን ገልፀው ተማሪዎች ሲመጡ አንሶላ፣ ትራስ ልብስ፣ ብርድልብስና ሌሎች ልብሶች ይዘው መምጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡