Get Mystery Box with random crypto!

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በክረምት ሲሰጥ የነበረዉ STEM Outrich መርሃ ግብር ተጠናቀቀ | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በክረምት ሲሰጥ የነበረዉ STEM Outrich መርሃ ግብር ተጠናቀቀ

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፡- ጳጉሜ 2/በ2014 ዓ.ም ( ደ.ማ .ዩ. ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት) የደብረ ማርቆስዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በ2014 ዓ.ም በክረምቱ ፕሮግራም (Summer Out rich) በተመረጡ ትምህርት አይነቶች ኬሚስትሪ፣ፊዚክስ ባዮሎጅ፣እንግሊዘኛ እና አይ.ሲቲ ከ13/10/2014 ዓ.ም አስከ 30/11/2014 ዓ.ም ሲሰጥ የነበረዉ የማጠናከሪያ ትምህርት የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪ ወ/ሮ ሳምራዊት ደሴ እንደገለጹት በክረምቱ መርሃ ግብር (Summer Out rich) ማጠናከሪያ ትምህርቱን የወሰዱት 44 ሴት፣ 163 ወንድ በአጠቃላይ 207 ተማሪዎች ሲሆኑ 14 መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርቱን ሰጠዋል፡፡

የዚህ መርሃ ግብር ዓላማ ክህሎትና አቅም ያላቸዉን ተማሪዎች በመለየት ያላቸዉን እዉቀትና ክህሎት አዉጥተዉ የሚጠቀሙበትን መንገድ በማመቻቸት እራሳቸዉንና ሀገራቸዉን እንዲጠቅሙ ለማድረግ ያለመ ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ልምድ ያላቸዉን ሰዎች ከተለያዩ የሙያ መስኮች በማምጣት ያላቸዉን ልምድ እንዲያካፉሏቸዉ ተደርጓል፡፡

የዚህ ዓመት STEM Outrich መርሃ ግብር ተጠቃሚዎች የ10ኛና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ የፈጠራ ስራዎቻቸዉን እንዲያዳብሩ የታገዙት አንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን ጭምር ነዉ፡፡ በተጨማሪም በበጋዉ ፕሮግራም በአይ ሲቲ ስልጠና ሲሰጣቸዉ የነበሩት ልጆች እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የታቀፉት ተማሪዎች ከምስ/ጎጃም ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች በሳይንስ ትምህርቶች ከፍተኛ ዉጤት ያላቸዉ ተማሪዎች ሲሆኑ የተሰጣቸዉ የማጠናከሪያ ትምህርት ተግባር ተኮር በመሆኑ የተለያዩ ፋብሪካዎችንና ወርክሾፖችን እንዲጎበኙ ተደርገዋል። በተሰጣቸዉ ተግባር ተኮር ትምህርት ክህሎቶቻቸውን በማዳበር የተለያዩ ድህረ ገጾችንና የፈጠራ ስራዎችን መስራት ችለዋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለመርሃ ግብሩ ያደረገዉ እገዛ ለ207 ተማሪዎች ዶርም እና ምግብ የቻለ ሲሆን በተጨማሪ ለመምህራን፣ የቤተ ሙከራ ባለሙያዎች ፣ ለአስተባባሪዎች ደግሞ የበጀትና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ለፕሮግራሙ መሳካት ከዩኒቨርስቲዉ በተጨማሪ STEM Synergy የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የበጀት ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድጋፍ አድርጓል፡፡

በመጨረሻም በመርሃ ግብሩ ላይ ተሳትፎ ለነበራቸዉ አካላት ሰርተፊኬት ከተሰጠ በኋላ ለተማሪዎች ምክርና የማጠቃለያ መልዕከት ተላልፎ የመርሃ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡