Get Mystery Box with random crypto!

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና የአካባቢው ማህበረሰብ ኤፍ ኤም 97.7 ሬዲዮ ጣቢያ የተመሰረተበትን 6 | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና የአካባቢው ማህበረሰብ ኤፍ ኤም 97.7 ሬዲዮ ጣቢያ የተመሰረተበትን 6ኛ አመት ክብረ በዓል አከበረ
=================
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፣ ነሐሴ 28/2014 ዓ.ም (ደ.ማ.ዩ. ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት) "የጥበብና_ማህበረሰብ_ድምፅ" በሚል መሪ ቃል የሚመራው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና የአካባቢው ማህበረሰብ ኤፍ ኤም 97.7 ሬዲዮ ጣቢያ ጥሪ የተደረገላቸው የፌደራል፣ የክልል ፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ሬዲዮ ጣቢያው ተደራሽ ከሆነባቸው አካባቢዎች የተጋበዙ የሀይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ከፍሎች በተገኙበት 6ኛ አመት የምስረታ ክብረ በዓሉን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ዓለማየሁ የጉባዔ አዳራሽ አከበረ።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና የአካባቢው ማህበረሰብ ኤፍ ኤም 97.7 ሬዲዮ ጣቢያ የቦርድ ሰብሳቢና የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚደንት ዶር. ታፈረ መላኩ በመግቢያ ንግግራቸው ይህ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ በሌሎች ዋና ዋና የመገናኛ አውታሮች ሽፋን የማይሰጣቸውና ትኩረት የተነፈጉ የማህበረሰብ ጉዳዮችን ሽፋን በመስጠት በጉልህ የሚጠቀስ ሬዲዮ መሆኑን ጠቅሰው አሁን እያከናወነ ካለው ይበልጥ ለማህበረሰባችን ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ስራዎች እንደሚጠበቁ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የሬዲዮ ጣቢያው ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት ሞላ በበኩላቸው የሬዲዮ ጣቢያውን አጠቃላይ የስራ ክንውን አጭር ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርታቸውም ሬዲዮው ተመርቆ ስራ የጀመረው ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱም በ 1 ዳይሬክተር ፣ በ 1 የይዘት ማናጀር፣ በ 5 ሪፖርተሮች እና በ 1 የቴክኒክ ባለሙያ እንዲሁም በ 1 ድጋፍ ሰጭ ቋሚ ቅጥር ሰራተኞች ሰራ መጀመሩን ገልፀዋል።

የሬዲዮ ጣቢያው ተደራሽነቱን ለማስፋትና የፕሮግራሞቹንም ጥራት ለማስጠበቅ ከሰው ሀይል አንፃር አሁን ላይ 15 ሪፖርተሮች፣ 3 ኤዲተሮች ፣ 4 የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ 1 የድጋፍ ሰጭ ሰራተኛ እና 1 ስራ አስኪያጅ በአጠቃላይ 24 ቋሚ ቅጥር ሰራተኞች እና 10 የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ያሉ ሲሆን የአየር ስዓታቸውንም በፊት ከነበረው በቀን የ6 ስዓታት የአር ጊዜ ወደ 11 ስዓት ከፍ ማድረጋቸውን ዳይሬክተሯ አክለው ገልፀዋል።
የስርጭት አድማስ ከማስፋት አንፃርም ከባለ 1 ኪሎ ዋት ወደ ባለ 2 ኪሎ ዋት ለማሳደግ በሂደት ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።

በቀረበው የስራ ክንውን ሪፖርት ላይ ከታዳሚዎች ሀሳብና አሰተያየት የተሰነዘሩ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችና ሀሳብችም ተገቢ ምላሽና ማብራሪያዎችም ተሰጥተዋል።

በመጨረሻም ለሬዲዮ ጣቢያው ስራ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ልዩ ልዩ አካላት የእውቅናና ምስጋና ስነ ስርዓት ተደርጓል።