Get Mystery Box with random crypto!

የገሊላ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትን በዘመናዊ መልክ ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ዉል ስምምነትና የመሰ | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

የገሊላ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትን በዘመናዊ መልክ ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ዉል ስምምነትና የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓት ተከናወነ

=====================

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፡- ነሐሴ 23/2014 ዓ.ም (ደ.ማ.ዩ. ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት) ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጀርመን አገር ከሚገኘዉ ከምፕተን ማዘጋጃቤትና ከበጎ አድራጊዎች ጋር በመሆን በምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ሰዴ ወረዳ ሰረቀ ብርሀን ቀበሌ ገሊላ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትን በዘመናዊ መልክ ለመገንባት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የመግባቢያ የዉል ስምምነትና የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓት በ22/12/2014ዓ.ም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተከናዉኗል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሳቸዉ ሽታዉ የገሊላ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትን በዘመናዊ መንገድ ለመገንባት የተከናወነዉን የመግባቢያ የዉል ስምምነትና የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓቱንና አጠቃላይ ስለሚገነባዉ ት/ቤት በተመለከተ እንደሚከተለዉ ገልጸዋል፡፡

የገሊላ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትን በዘመናዊ መንገድ የሚገነባዉ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ከምፕተን ማዘጋጃ ቤት እና የምስ/ጎጃም ዞን አስተዳደርና የሰዴ ወረዳ አስተዳደር አራቱ አካላት በጋራ በመቀናጀት ሲሆን የገንዘብ ድጋፍ የሚያደረርጉትም ጀርመን ሀገር የሚገኘው ከምፕተን ማዘጋጀቤትና ሌሎች በጎ አድራጊ ድርጅቶች ናቸዉ፡፡

ይህ ት/ቤት በዘመናዊ መንገድ ደረጃዉን በጠበቀ መልኩ እንዲገነባ መነሻ የሆኑት አካባቢዉ ተወላጅና በአሁን ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ተወልኝ ከበደ ይባላሉ፡፡ እኒህ ግለሰብ ጀርመን ሀገር ሶስተኛ ድግሪያቸዉን በሚሰሩበት ወቅት ከምፕተን ማዘጋጃ ቤት ጋር በመነጋገር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የከምፕተን ማዘጋጃ ቤት እስካሁን የገሊላ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትን ጨምሮ 10 ት/ቤቶችን በዘመናዊ መንገድ በመገንባት ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ የሚገነባዉ ት/ቤት ጥራቱን በጠበቀ ደረጃ እንዲገነባ የመህንዲሶችን ቡድን በማዋቅር ፕላኑን በማዘጋጀትና የግንባታ ስራው እስከሚጠናቀቅ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ የዉል ስምምነት ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተፈራርመዋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከምፕተን ማዘጋጃ ቤትንና የአካባቢዉን ማህበረሰብ በማገናኝት ይህ 1ኛ ት/ቤት ደረጃዉን ጠብቆ እንዲገነባ እና ግንባታዉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ክትትል የማድረግ ሃላፊነት የሚወስድ መሆኑም ተነግሯል፡፡

የከምፕተን ማዘጋጃቤት ተወካይ የተከበሩ ፕሮፈሰር ዩሃንስ ሽታይንብሩን በበኩላቸዉ ት/ቤቱን የከምፕተን ማዘጋጃ ቤትና ህዝብ የመገንባት ዕድል በማግኘታቸዉ ደስተኛ እንደሆኑና ግንባታዉን ደረጃዉን በተጠበቀ መልኩ በማጠናቀቅ ለአካባቢዉ ማህበረሰብ እንደሚያስረክቡ ቃል ግብተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዘዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ በበኩላቸዉ የገሊላ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ደረጃዉን የጠበቀ ሆኖ መገንባቱ ለአካባቢዉ ማህበረሰብ ትልቅ ዕድል ነዉ ብለዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ስያሜም የሰዴ ወረዳና የከምፕተን ከተማን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ እጨጌ ገሌላ ከምፕተን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት በሚል መጠሪያ እንዲጠራ አስተያየታቸዉን ሰጠዋል፡፡

በመጨረሻም ይህ ት/ቤት እንዲገባ አስተዋጾ ላደረጉት ለከምፕተን ማዘጋጃቤትና ዶ/ር ተዉልኝ ከበደ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የት/ቤቱ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ 20 ህንፃዎች የሚኖሩት ሲሆን ከእነዚህም ዉስጥ የመማሪያ፣የመምህራን መኖሪያ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ለልዩ ልዩ የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች፣የግብርናና ስፖርት ማዝወተሪያ ቦታዎችን አካትቷል፡፡ ት/ቤቱ በአንድ ፈረቃ ከ680 ተማሪዎች በላይ የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረዉ ተገልጠዋል፡፡