Get Mystery Box with random crypto!

ዲያቆን ወልደ ሰንበት መጣጥፎች ፣ ትምህርቶች

የቴሌግራም ቻናል አርማ deacongirmayeshitla — ዲያቆን ወልደ ሰንበት መጣጥፎች ፣ ትምህርቶች
የቴሌግራም ቻናል አርማ deacongirmayeshitla — ዲያቆን ወልደ ሰንበት መጣጥፎች ፣ ትምህርቶች
የሰርጥ አድራሻ: @deacongirmayeshitla
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 1.39K
የሰርጥ መግለጫ

ይህ መንፈሳዊ ቻናል ትምህርቶች ፣መጣጥፎችን ፣ወጎች የሚተላለፉበት ነው። እንዲሁም የበአላት ወረቦች ፣ምስባክ ያገኙበታል

ይህ ቻናል በባለቤቱ የተከፈተ ቻናል ነው

Ratings & Reviews

2.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

2

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2022-08-31 21:50:01 ኢትዮጵያ እንደ ርብቃ በሆድዋ ያሉ ልጆችዋ እየተዋጉባት  "እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው?" ብላ እየጮኸች ነው:: ለእናት ልጆችዋ ቢጋደሉላት ምን ይጠቅማታል? ሟቹም ልጅዋ ገዳዩም ልጅዋ ነውና ከመቁሰል በቀር ምንም አታገኝም:: ዳዊት ልጁ አቤሴሎም ሌላ ልጁን አምኖንን በገደለ ጊዜ ያለቀሰውን ለቅሶ ኢትዮጵያ ታለቅሳለች:: በዚህ መካከል ምስኪኑ ወገናችን ይረግፋል:: እጅ እጁን ሲቆርጥ ደስታና ፉከራ የለም:: ብንችል በዚህ ሰዓት በጸጸት እንጸልይ:: ካልቻልን ደግሞ ቢያንስ ዝም እንበል:: የሀገርን ሰላም የምትፈልጉ ሁላችሁ ከሩቅ በለው በለው ማለት ትታችሁ ማረን ማረን በሉ::

በሩቅ ሆነን አይነካንም ብለን እየፎከርን በምስኪኑ ላይ እሳት የምናነድ አንሁን:: በወገን ሞት ተደስተን እንደባዕድ ሀገር ጦርነት የድል ዜማ ብናዜም እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ይፈርድብናል::

ከራሳችን በላይ ሌላ ጠላት የለንምና ጌታ ሆይ ከራሳችን አድነን:: ኢትዮጵያ እጅዋን ወደ እግዚአብሔር መዘርጋት ትታ ራስዋ ላይ ቃታ የሳበችበት ዘመን ላይ ደርሰናል:: ጌታ ሆይ በዓይነ ምሕረትህ ተመልክተህ እኛው ያነደድነውን እሳት አብርድልን:: በትግራይ በአማራ በኦሮሚያ ያሉ በዚህ እሳት ዙሪያ የሚማገዱ ወገኖቻችንን ከጥፋት ይጠብቅልን:: በግራም በቀኝም የተሰለፉት በድህነት የሚኖሩ አንድ ውኃ የጠጡ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው::  አባቶቻቸው ሳይለያዩ አብረው ከብዙ ጠላት ጋር ታግለው ባቆዩአት መሬት ላይ ወንድማማቾች ጦር እየተሳበቁ ነውና በቸርነትህ ልባቸውን አራራ:: ወንድምን ገድሎ እንደ ቃየን ከመቅበዝበዝ በቀር ትርፍ እንደሌለ አሳያቸው:: ጠግቦ በልቶ ሳያድር ተመስገን ማለትን ያልተወ ሕዝብህን ጌታ ሆይ በምሕረትህ አድነው::

(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
67 views , 18:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 08:23:09 #ኹሉንም_ነገር_ለእግዚአብሔር_እንስጠው

ወርቅን የሚያነጥር ሰው አንዲትን የወርቅ ቅንጣት ወደ እሳት ውስጥ ጨምሮ እጅግ ንጹህ እስክትኾን ድረስ ይጠብቃታል፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደዚሁ ሰዎች እስኪነጹ፣ እስኪለወጡና ባገኛቸው ነገር ጥቅም እስኪያገኙ ድረስ ፈተና ውስጥ እንዲቆዩ ይፈቅዳል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅምም እጅግ ከፍ ያለ ጥቅም ነው፡፡

ስለዚህ ፈተና ሲገጥመን ውስጣችን ሊረበሽ ወይም ተስፋ ሊቈርጥ አይገባውም፡፡ ያ ወርቅን የሚያነጥር ሰው በእሳት ውስጥ የጨመራትን የወርቅ ቅንጣት እዚያ ውስጥ ምን ያኽል ጊዜ መቆየት እንዳለባት ያውቃል፤ መቼ ከእሳቱ ሊያወጣት እንደሚገባውም ያውቃል፡፡ እንዲሁ እስከ መጨረሻው በእሳቱ ውስጥ ተጥላ እንድትቀርና በዚያ እንድትቃጠል አይፈቅድም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ከወርቅ አንጣሪው በላይ ያውቃል፡፡ መቼ ከርኵሰታችን እንደምንነጻ ያውቃል፡፡ በመኾኑም ራሳችንን በመጣልና ተስፋ በመቁረጥ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመርን እንዳንሔድ ሽቶ መቼ ከዚያ ፈተና እንደሚያወጣን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ድንገት ያላሰብነው ነገር ቢገጥመን በፍጹም የምናማርር፣ ወይም ተስፋ የምንቈርጥ ልንኾን አይገባንም፡፡ ከዚህ ይልቅ የእነዚህ ነገሮች ምንነትን የሚያውቅ እግዚአብሔርን መጠበቅ፣ እርሱ እስከ ፈቀደው ጊዜ ድረስም ልቡናችንን በእሳት እንዲፈተን ማድረግ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ነገር በእኛ ላይ እንዲኾን የፈቀደው ለእኛ ጥቅምና በዚያ ውስጥ ኾነን በምናሳየው ጥረት ይበልጥ ሊያከብረን ስለሚወድ ነው፡፡

ይህን በማስመልከትም ጠቢቡ ሰው እንደዚህ ሲል መክሮናል፡- “ልጄ ሆይ! ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ብትሔድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ፤ ልብህን አቅና፤ ኹልጊዜ ታገሥ፤ አታወላውልም፤ በመከራ ብትጨነቅም አትጠራጠር” /ሲራ.2፥1-2/፡፡ “ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ስጠው፡፡” ለምን? እግዚአብሔር ከዚያ መከራ መቼ እኛን ማውጣት እንዳለበት ያውቃልና፡፡ ስለዚህ ኹሉንም ለእርሱ ልንሰጥ፣ ዘወትር እርሱን ልናመሰግን፣ ኹሉንም ነገር - ጥቅምም ይኹን ቅጣት - በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፤ ይህም ቢኾን ለእኛ ረብሕ የሚኾን ነውና፡፡ አንድ ሐኪም፥ ሐኪም የሚባለው ታካሚውን ገላዉን ሲያጥበውና ሲመግበው እንዲሁም ደስ ወደሚያሰኝ ስፍራ ሲወስደው ብቻ አይደለም፤ በእርሱ (በታማሚው) ሰውነት ላይ የቀዶ ጥገና ምላጭና ቢላ ሲያሳርፍም ጭምር ሐኪም ነው፡፡ አባትም አባት የሚባለው ልጁን ሲንከባከብ ብቻ አይደለም፤ የገዛ ልጁን ከቤት ሲያስወጣው፣ ሲገሥጸው፣ ሲገርፈውም ያው አባት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔር ከሐኪሞችም በላይ ሰውን ወዳጅ እንደ ኾነ በማወቅ፥ ምን ዓይነት የሕክምና ዓይነት እንደሚሰጠን በጥልቀት አንጠይቅ፤ ወይም ደግሞ ለደረሰብን መከራ እርሱን ተጠያቂ አናድርግ፡፡ ከዚህ ይልቅ እርሱ የወደደውን ነገር - ቅጣትም ይኹን ቅጣት የሌለው ነገር - ብቻ ምንም ይኹን ምን በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፡፡

በየትኛውም መንገድም ቢኾን የእርሱ ፈቃድ እኛ እንድንድንና ከእርሱ ጋር አንድ እንድንኾን ነውና፡፡ የትኛው መንገድ ለእኛ እንደሚጠቅምም እርሱ ያውቋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የትኛው መንገድ ወደ እርሱ እንደሚመልሰው ያውቃል፡፡ ኹላችንም እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ልንድን እንደምንችል ያውቃል፡፡ በመኾኑም የሚመራን በዚህ እኛ በምንድንበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ወደየትኛውም መንገድ ቢወስደንም - ልክ እንደ መጻጉዑ - እርሱ እንደሚያዘ’ን ተከትለን መሔድ እንጂ ትልቁ ጉዳያችን በለስላሳና በቀላል አልያም ደግሞ በከባድና በሸካራ ጎዳና እንድንሔድ የሚያዘ’ንን ትእዛዝ መኾን የለበትም (ልንሔድበት የሚገባው መንገድ እርሱ ስለሚያውቀው እንዲሁ መታዘዝ እንጂ የመንገዱን ከባድነት ወይም ቀላልነት የእኛ አጀንዳ ሊኾን አይገባውም፡፡)

(#በቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ - ወደ ኦሎምፒያስ የተላኩ መልእክታት - ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው )
112 views , 05:23
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 07:00:26 እዚህ ላይ የሚያስደንቀው የማርያም ዝምታ ነው፡፡ ማርታ ስትከስሳት ጌታችን መልስ ሠጠላት እንጂ ማርያም አንድም ቃል አልተነፈሰችም፡፡ ‹ቃሉን መስማት ይበልጣል ብዬ ነው!› ብላም አልተመጻደቀችም፡፡ ዝም አለች፡፡ በእርግጥ እኅትዋ ስትከስሳት ምን ተሰምቷት ይሆን? በአፍዋ ዝም ብላ በልብዋ እየተሳደበች ይሆን እንዴ? አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹የለም በውስጥዋም ክፉ ሃሳብ አልነበረም› ይላል፡፡ ‹እንግዲህ እንደ ማርያም አርምሞና ትዕግሥትን ገንዘብ እናድርግ› (ናጥሪ እንከ አርምሞ ወትዕግሥተ ከመ ማርያም) በማለት በአፍዋ አርምሞን (ዝምታን) ብቻ ሳይሆን በልብዋም ትዕግሥትን ገንዘብ አድርጋ እንደነበር ይመሰክራል፡፡

ያስደንቃል! እጅግ በምታከብረው ጌታ ፊት የገዛ እኅትዋ ስትከስሳት ማርያም እንዴት አልተበሳጨችም? ቢያንስ በልቧ እንኳን እንዴት አላጉረመረመችም? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ማርያም ሌላ ዓለም ውስጥ ስለነበረች ነው፡፡ ከጌታችን አንደበት የሚወጣውን አምላካዊ ቃል ሰምታ ልቧ ተሰውሯል ፤ አካልዋ በቤት ውስጥ ቢሆንም ኅሊናዋ ወደ ሰማያት ከፍ ብሏል፡፡ በጌታችን ቃል ልቡ የተሰበረ ሰው ደግሞ እንኳን ቢሰድቡት ቢደበድቡትም አይሰማውም፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ መወገሩ ገለባ የመሰለው ጌታችንን እያየ ስለነበር ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ የአፄ ገብረ መስቀል ጦር እግሩ ላይ ተሰክቶ ምንም ያልታወቀው በእግዚአብሔር ቃል ልቡ ስለተመሠጠ ነው፡፡ ማርያምም ልቧ በቃሉ ስለተመሰጠ በእኅቷ ንግግር ምንም አልተሰማትም፡፡

★ ★ ★

ከብዙ ወራት በኋላ ጌታችን ዳግመኛ ወደነማርታ ሀገር ወደ ቢታንያ ተመልሶ መጣ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን እንግዳ ሆኖ የሔደው ወደነማርታ ቤት ሳይሆን ወደ ለምጻሙ ስምዖን ቤት ነበር፡፡ የቢታንያው ስምዖን ለጌታችን የራት ግብዣ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ታዲያ የቢታንያ ነዋሪዎች እንደመሆናቸው ማርታ ፣ ማርያምና አልዓዛርም በስምዖን ቤት ተገኝተው ነበር፡፡

ማርያም ጌታችን ባስተማራት ትምህርት ልቧ ተሰብሮ ፣ የምትኖርበትን የኃጢአት ኑሮ ተጸይፋ ነበር፡፡ ስለዚህ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባስጥሮስ ሽቱ ገዝታ ወደ ስምዖን ቤት ገሰገሰች፡፡ ከጌታችን እግር ሥር ተደፍታም በዕንባዋ አጠበችው ፣ በፍጹም ጸጸት ወደ ፈጣሪዋ ተመለሰች፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ‹ይህ ጥፋት ምንድር ነው?› ብሎ ለሽቱው ብክነት ተቆጨ ‹ለድሆች ቢሠጥ ይጠቅም ነበር› የሚል የውሸት ምክንያትም አቀረበ፡፡

ማርያም ፈተናዋ ብዙ ነው ፤ ቃሉን ስትማር እኅትዋ ተቸቻት ፤ ንስሓ ስትገባ ደግሞ ይሁዳ ተነሣባት፡፡ ማርታ ቃሉን ከመስማት ይልቅ ‹ለምግብ ሥራ ቅድሚያ እንሥጥ› ብላ እንደነበር ይሁዳም ‹ለነዳያን አገልግሎት ቅድሚያ ይሠጥ› አለ፡፡ (ይሁዳ ጌታችን ሲያስተምር ‹እናትህና ወንድሞችህ መጥተዋል እያለ ትምህርት እንዲቋረጥ የሚታገል ሰው እንደነበር ልብ ይሏል› ማቴ.12፡46 ትርጓሜ)

ይሁዳ ሲናገር ማርያም እንደ ልማዷ ዝም አለች ፤ ጌታችንም እንደ ልማዱ መልስ ሠጠላት፡፡ እርስዋንም ‹ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል› ብሎም አሰናበታት፡፡ ማርያም በተማረችው ቃል የንስሓ ፍሬ አፈራች ፤ የኃጥኡን መመለስ ለሚወደው ጌታ ዕንባዋ አቀርባ ከማርታ በላይ አስተናገደችው፡፡ መስተንግዶዋም ከማርታ ብቻ ሳይሆን ታላቅ ግብዣ ካደረገለት ከለምጻሙ ስምዖንም የበለጠ ሆነ፡፡ ጌታችንም ለለምጻሙ ስምዖን ከእርሱ መስተንግዶ የእርስዋ መስተንግዶ ምን ያህል የበለጠ እንደሆነ አነጻጽሮ ነግሮታል፡፡ (ሉቃ. 7፡44-46)

ከላይ እንደተገለጸው ማርያም እንዲህ ስትጸጸትና ኃጢአትዋ ሲሰረይላት ማርታ በለምጻሙ ስምዖን ቤት ውስጥ በእንግድነት ተገኝታ ነበር፡፡ ምን እያደረገች ይሆን? የእኅትዋን መመለስ በመገረም እያየች ይሆን? ወይስ በቤትዋ ያመለጣትን ትምህርት ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብላ እየሰማች ይሆን? ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ መልሱን እንዲህ ሲል ጽፎልናል፡፡ ‹‹በዚያም እራት አደረጉለት፤ ማርታም ታገለግል ነበር›› (ዮሐ. 12፡2)

ለማመን ያስቸግር ይሆናል፡፡ አዎን ማርታ በሰው ቤትም እንኳን አላረፈችም፡፡ በቤትዋ እንዳደረገችው በስምኦን ቤትም በአገልግሎት ላይ ነበረች፡፡ እኅትዋ ስትማር ጓዳ የነበረችው የዋኋ ማርታ ምንም እንኳን ጌታችን አገልግሎቷን ሳይነቅፍ የሚበልጠው ከእግሩ ሥር መገኘት እንደሆነ የነገራት ቢሆንምም አሁንም መልካሙን ዕድል አልመረጠችም፡፡ እኅትዋ ስትማር ታገለግል እንደነበረች ፣ የእኅትዋ ኃጢአት ሲሰረይም እስዋ አገልግሎት ላይ ናት፡፡ ማገልገል መልካም ነው ፤ እኛ በአገልግሎት ስንባክን ፣ ሌሎች ወደ እግዚአብሔር ሲቀርቡ ኖረዋል፡፡

ንስሓ ገብተው ወደ ሥጋ ወደሙ ሲቀርቡም እኛ አገልግሎት ላይ ከሆንን እንደ ማርታ ዕድላችንን ያልተጠቀምን ምስኪኖች ነን፡፡ የሚያሳዝነው ማርታ አላወቀችም እንጂ የስምዖን ቤት ግብዣ ከጌታ እግር ስር ለመቀመጥ የመጨረሻ ዕድሏ ነበር፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ከዚያች ቀን በኋላ በጥቂት ቀናት ልዩነት ተሰቅሎ ሞቶአል፡፡ ከዚያም ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶ በአርባኛው ቀን አርጓል፡፡ ማርያም የመጀመሪያ ዕድሏን ለመማር ፣ የመጨረሻ ዕድሏን ደግሞ ለንስሓ ተጠቀመችበት፡፡ ማርታ ግን ‹ታገለግል ነበር›፡፡

"ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ"
68 views , 04:00
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 07:00:26 +++ ማርታም ታገለግል ነበር+++

ማርያምና ማርታ እኅትማማቾች ናቸው፡፡ ‹ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን ፣ አልዓዛርንም ይወድ ነበር› (ዮሐ. 11፡5) ስለዚህም በቢታንያ በሚገኘው ቤታቸው እንግዳ ሆኖ ተገኘ፡፡ እጅግ ለሚወዱት ጌታ ፍቅራቸውን ለመግለጽ እኅትማማቾቹ ይሻላል ብለው ያሰቡትን ሁለት የተለያየ ዓይነት አቀባበል አድርገውለት ነበር፡፡ ማርታ ለምትወደው እንግዳዋ ምግብ ለማቅረብ ብዙ ተጨንቃ በጓዳ ሥራ ላይ ተወጠረች፡፡ ‹ለታላቁ ጌታ ምን ላቅርብለት ይሆን?› ብላ ተጠበበች፡፡
መቼም የምናከብረው ሰው እንግዳ ሆኖ ሲመጣ ሙያውም ሊጠፋብን ይችላል፡፡

ማርታም የገጠማት ይኼው ነው ፣ ምኑን ከምኑ አድርጋ እንደምታቀርብ ግራ ገባት ፤ ጌታችን እንዳለው ‹በብዙ ነገር ተጨነቀች ታወከች›፡፡

እኅትዋ ማርያም ግን ሃሳቧን ጥላ ቃሉን ልትሰማ ከጌታ እግር ሥር ቁጭ አለች፡፡
ማርያምን በማርታ ዓይን ሆነን ስናያት እንግዳ ሲመጣ ሥራ ላለመሥራት ከእንግዳ ጋር ከሚቀመጡ ሥራ ጠል እኅቶች አንድዋን ትመስለናለች፡፡

እኅትዋ ከጭስ ጋር ስትታገል ፣ ምን ልሥራ ብላ ስትርበተበት እስዋ በቤትዋ እንደ እንግዳ መቀመጥዋን ስናይ ‹ምን ዓይነቷ ግፍ የማትፈራ ናት› ብለን መታዘባችን አይቀርም፡፡

ማርታ ግን ታዝባ ዝም አላለችም፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው። ጌታችንም ኢየሱስም መልሶ፦ ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት።››

ሉቃ. 10፡38-42 በእኛ ግምገማ ማርታ የበለጠ ለጌታ ፍቅር ያላት ቢመስለንም ጌታችን ግን የማርታን በፍቅር ለሥራ መድከም ሳይነቅፍባት የማርያም ምርጫ ግን ‹የማይቀማ በጎ ዕድል› መሆኑን ተናገረ፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል?

በእኅትማማቾቹ ቤት የተገኘው ሌላ እንግዳ ቢሆን ኖሮ ማርያም ያደረገችው የሚያስወቅስ ይሆን ነበር፡፡ በእነርሱ ቤት የተገኘው ግን የሰማይና የምድር ፈጣሪ ነው፡፡

እርሱ ደግሞ የሚቀበሉት እንጂ የሚሠጡት እንግዳ አይደለም፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እንዳለው ‹‹ማርታ ጌታ ራሱ የፈጠረውን ምግብ በገበታ ልታቀርብለት›› ተጨነቀች፡፡(Martha gave him to eat: viands which He had created she placed before Him)
@deaqonhanok
የዋኋ ማርታ ያላወቀችው ነገር እርሱ ደስ ብሎት የሚበላው ምግብ እርስዋ የምትሠራው ዓይነት ምግብ እንዳልሆነ ነው፡፡

እንደ ሐዋርያቱ ቀርባ ብትጠይቀው ኖሮ ፡- ‹‹አንቺ የማታውቂው የምበላው መብል ለእኔ አለኝ›› ይላት ነበር፡፡

(ዮሐ. 4፡32) ምን ትጠጣለህ? ብትለው ለሙሴ እንደነገረው ‹ኃጢአተኛ ሲጸጸት ዕንባውን እጠጣለሁ› (ኃጥእ አመ ይኔስሕ ዕንባሁ እሰቲ) ብሎ ይመልስላት ነበር፡፡

አልጠየቀችውም እንጂ መራራ ሐሞት እስኪጠጣ ድረስ በሰው ልጅ ፍቅር ስለተጠማው ጕሮሮው ይነግራት ነበር፡፡

(‹ሰላም ለጕርዔከ በጽምአ ፍቅረ ሰብእ ሐማሚ፡፡ እስከ ስቴ ሐሞት ጥዕመ ወዘወይነ ትፍስሕት ከራሚ› እንዲል) የእርሱ ምግብና መጠጥ የሰው ልጅ ልቡን ሠጥቶ ወደ እርሱ መመለሱ ነው፡፡

ማርያም ግን የማይቀሟትን በጎ ዕድል መረጠች፡፡ ከራሱ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብሎ ከመማር በላይ ምን ዕድል አለ? ፈጣሪ ሲናገር መስማትስ እንዴት መታደል ነው? እርሱ የሚናገረው ቃል እኮ መለኮታዊ ቃል ነው! ከጌታ የሚወጣው ቃል የሚሠራና ሕያው የሆነው የራሱ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ

‹ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል› (ዕብ. 4፡12) እርሱ የሚናገረው ቃል ሙቱን አፈፍ አድርጎ ያስነሣል ፣ ለምጻሙን ያነጻል፡፡

አስረው እንዲያመጡት ከአይሁድ የተላኩት የሮም ወታደሮች እንኳን ከትምህርቱ ጣዕም የተነሣ ተደንቀው ‹‹እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም›› ብለው ባዶ እጃቸውን ተመልሰዋል፡፡

(ዮሐ.7፡46) የኤማሁስ መንገደኞችም ‹በመንገድ ሲናገረን ልባችን ይቃጠል አልነበረምን?› ብለዋል፡፡(ሉቃ. 24፡32) ይህ የጌታችን ድንቅ ትምህርት ማርታ ማድቤት ሆና አመለጣት፡፡

‹ብዙ ነቢያት ሊሰሙት ወድደው ያልሰሙትን› ቃል የመስማት ዕድል ቤቷ ድረስ መጥቶላት እርስዋ ግን ሥራ ላይ ነበረች፡፡ እንደ ሙሴ ወደ ተራራ ሳትወጣ ፣ በደመና ሳትከበብ ቤቷ ድረስ እግዚአብሔር መጥቶ ሊያናግራት ሲል እስዋ ግን ምግብ እየሠራለች ነው፡፡

‹ማርታ ግን አገልግሎት ስለበዛባት ባከነች› ይላል፡፡ ይህ ቃል በእግዚአብሔር ቤት ለምናገለግል ፣ የማርታ ችግር ላለብን ሰዎች ምንኛ ከባድ ቃል ነው? ለመቅደሱ ቀርበን ከፈጣሪ ለራቅን ፣ ጠዋት ማታ በሥራ ፣ በዕቅድ ፣ በስብሰባ ተወጥረን እንደ ማርታ ብዙ ድስት ለጣድን ለእኛ ምንኛ ከባድ ቃል ይሆን? አቡነ ሺኖዳ ‹‹እስከ ዛሬ የእግዚአብሔርን ቤት አገለገልሁ ፤ የቤቱን ጌታ የማገለግለው መቼ ይሆን?›› ብለው ነበር፡፡

ቤቱን እያገለገልን የቤቱን ጌታ ማገልገል ያቃተን ፣ በአገልግሎት ተወጥረን ከጸሎት ፣ ከንስሓ ፣ ከሥጋ ወደሙና ቃሉን ለራስ ብሎ ከመስማት ለተለየን ሰዎች እጅግ ከባድ ቃል ነው፡፡

እያገለገሉ ከፈጣሪ መራቅ እጅግ ከባድ ነው፡፡ እንደ ማርታ ፈጣሪ ባለበት ቤት እየኖሩ ከፈጣሪ መለየትም እጅግ የከፋ ነው፡፡

ማርያም የምትማርበትን ክፍል አጽድተን ፣ በኋላም ገበታውን አቅራቢ ሆነን የምንወደውን ፈጣሪ ሳንሰማው መቅረት እንዴት ያሳዝናል? ለሰብአ ሰገል ወደ ቤተልሔም ሔደው እንዲሰግዱ የጠቆሟቸው አይሁድ ነበሩ ፤ እነርሱ ግን ሔደው አልሰገዱለትም፡፡ ቅዱስ አምብሮስ እንዳለው ኖኅ መርከብ ሲሠራ የረዱት የቀን ሠራተኞች ነበሩ ፤ እነርሱ ግን ከጥፋት ውኃ አልዳኑም፡፡ ለፍቶ ደክሞ አገልግሎ ፣ ሌላውን አስተምሮ ፣ ቤተ እግዚአብሔርን ሠርቶ መኮነን እንዴት ያሳዝናል? እንደ መርፌ የሌላውን ቀዳዳ እየሠፋን የራሳችንን መስፋት ያቃተን ፣ እንደ መቋሚያ ለሌላው ድጋፍ እየሆንን ራሳችንን ማቆም ያቃተን ‹አገልግሎት ስለበዛብን የባከንን› ብዙዎች ነን፡፡

ማርታ ከቃሉ በመራቋ ምክንያት አገልግሎትዋን እንኳን በጸጥታ ማገልገል አልቻለችም፡፡ ብቻዋን መሥራትዋም አስቆጫት፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው።›› ይህ ንግግርዋ ብዙ ጉድለት እንዳለባት ያሳያል፡፡ እኅትዋ እስከሆነች ድረስ ቀስ ብላ ጠርታ ‹ምን ማድረግሽ ነው? ነይና አግዢኝ እንጂ› ልትላት ትችል ነበር፡፡ አልዓዛር በሞተ ጊዜ በለቅሶ ቤት ‹ማርያምን በስውር ጠርታ፦ መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል› ብላ እንደተናገረችው አሁንም በስውር ጠርታ ልትወቅሳት ትችል ነበር፡፡

(ዮሐ. 11፡28) እርስዋ ግን በቀጥታ ለእኅትዋ ከመናገር ይልቅ እኅትዋን በጌታ ፊት አሳጣቻት ፣ ከእኅትዋ ይልቅ እርስዋ ለጌታ የበለጠ ፍቅር ያላት እንደሆነች የሚያሳይ ንግግር ተናረች፡፡ ሰው ቃለ እግዚአብሔር ሲጎድለው ጠበኛ ይሆናል፡፡ እርሱ እየሠራ የሌሎች አለመሥራት ያበሳጨዋል ፣ በቀጥታ ሔዶ ለሰው ችግሩን ከመናገር ይልቅ በተዘዋዋሪ መናገር ይቀልለዋል፡፡ የዋኋ ማርታ ለአገልግሎት ስትባክን የገጠማት ፈተናም ይኼው ነው፡፡
55 views , 04:00
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-24 23:23:05 ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ ማንም እንዳይቀር
169 viewsGery, 20:23
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-24 23:22:36
159 viewsGery, 20:22
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-23 13:57:08 “በምድር ላይ የምንቆየው የዕድሜ ልክ ቆይታ በዘላለማዊው ሕይወት ካለው የዓይን ጥቅሻ አፍታ ጋር እንክዋን እኩል አይሆንም:: የዚህ ምድር ቆይታ እንግዲህ ለዚያኛው የሚያበቃን ነው" አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ



"እመቤቴ ሆይ በአንቺ ጸሎት በልጅሽ ቸርነት ከታመንሁ ሰማይ ወፍጮ ምድር መጅ ቢሆኑ ሁለቱም ሊያጠፉኝ ቢፈልጉ አንዳች ሊያደርጉኝ አይችሉም" ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ



"ሰዎች የተራሮችን ከፍታ የባሕርን ሞገድ የወንዞችን ረዥም ፍሰት : ለማድነቅ ወደ ብዙ ሀገራት ይጉዋዛሉ : የከዋክብትን ውበትም ያደንቃሉ:: አንድን አስደናቂ ፍጥረት ግን ቸል ብለው ያልፉታል : ይህ ድንቅ ፍጥረት የሰው ልጅ ነው::" ቅዱስ አውግስጢኖስ



አንድን አባት ሰዎች መጡና "ዘወትር ጸሎት በማድረግህ በሕይወትህ ላይ የጨመረልህን ነገር ንገረን?" አሉት:: እርሱ ግን "ጸሎት በማድረጌ ከጨመርሁት ይልቅ የቀነስሁት ይበዛልና እርሱን ልንገራችሁ:: ጸሎት በማድረጌ ከሕይወቴ ውስጥ ጭንቀት ፍርሃት ተስፋ መቁረጥና ቁጡነትን ቀንሻለሁ አላቸው::



የትንሣኤ ሰሞን ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ ብሎ ሰላምታ መለዋወጥ በኦርቶዶክሱ ዓለም እጅግ የተለመደ ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ግን ይህንን ዓመታዊ ሰላምታ የዘወትር አድርጎ ወደ እርሱ የመጣን ሰው ሁሉ በፈገግታ"ክርስቶስ ተነሣ" ብሎ ያበሥር ነበር::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ግንቦት 5 2011 ዓ ም
አዲስ አበባ
207 viewsGery, 10:57
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-23 12:51:37
"ሰላም ለትንሣኤኪ ትንሣኤ ክርስቶስ መንታ"
"እንደ ልጅሽ ትንሣኤ ስለሚከብር ትንሣኤሽ ሰላም እላለሁ"

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ!
166 viewsGery, 09:51
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-23 02:50:58 +++ አበው ስለ እመቤታችን እንዲህ አሉ +++

"አምላክ ከንጉሥ ሔሮድስ ሴት ልጅ ቢወለድ ኖሮ አልጋ ወራሽ በሆነና ባልተሰደደ ነበር። እርሱ ግን የድሆች ልጅ የሆነችውን ድንግል መረጠ" አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

"ታላቁ ተራራ ሆይ ታናሽዋ ብላቴና የተሸከመችህ ራስህን በሚቻላት መጠን አድርገህላት ነው ፣ ታላቁ እሳት ሆይ ታናሽዋ ብላቴና ተሸክማህ ያልተቃጠለችው ኃይልን ትችል ዘንድ አጽንተሃት ነው " ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

"ይህ ዓለም የእግዚአብሔርን ልጅ በቀጥታ ከእግዚአብሔር አብ እጅ ለመቀበል የተገባ ሆኖ ስላልተገኘ ፣ ዓለም ከእርስዋ ይቀበል ዘንድ አንድያ ልጁን ለድንግል ማርያም እናት ትሆነው ዘንድ ሠጣት" ቅዱስ አውግስጢኖስ

"ሔሮድስ የማይያዘውን ይይዝ ዘንድ ተነሣ ፣ ዓውሎ ነፋስንም በቤቱ አስገብቶ ሊዘጋ ታገለ" አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

"ጌታ ሆይ እናትህን ማን ብለን እንጥራት? እናት ብቻ እንዳንላት ድንግል ሆና አገኘናት ፣ ድንግል እንዳንላት ልጅ ታቅፋ አየናት። ጌታ ሆይ እናትህን ለመጥራት እንዲህ የሚያስቸግር ከሆነ አንተን ከቶ ምን ብለን እንጠራሃለን??" ቅዱስ ኤፍሬም
(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ )
219 viewsGery, 23:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-16 22:44:06 #የማክሰኞ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

ለምስጋና ኹለተኛ፣ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ቀንም እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ክርክር በዕለተ ሰኑይ አልቋልና “ባርክኒ” ብሎ ተባርኮ “አክሊለ ምክሕነ” ብሎ ምስጋናውን ይጀምራል፡፡

፩. ዳዊት ምንም ንጉሠ ነገሥት ቢባል የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም /፩ኛሳሙ.፲፮፥፲፫/፡፡ ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢኾንም የደኅንነታችን መጀመሪያ መኾን አልተቻለውም፡፡ ኤልያስም ምንም ንጹሕ፣ ድንግል ቢኾንም የንጽሕናችን መሠረት መኾን አልተቻለውም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፣ የንጽሕናችን መሠረት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የመመኪያችን ዘውድ “አክሊለ ሰማዕት” የሚባል ጌታችን ነው፡፡ የደኅንነታችን መጀመርያ “ጥንተ ሕይወት” የሚባል ጌታችን ነው፡፡ የንጽሕናችን መጀመርያም ኹሉ በእጁ የተጨበጠ፣ ዓለምንም በመዳፉ የያዘ፤ በጠፈር ላይ የሚቀመጥ ፣ ዳግመኛም መሠረቱን ከታች የሚሸከም “መሠረተ ዓለም” የሚባል ጌታችን ነው /ቅዳ.ማር. ቁ.፶፩/፡፡ እርሱም አካላዊ ቃልን በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን፡፡ እኛን ስለማዳን ሰው ኾነ፤ ሰውም ከኾነ በኋላ ግን ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ እንደ ወለደችው ኹሉ እርሱም አምላክነቱ ሳይለወጥ ሰው ኾነ፡፡ እርሷ “ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም)” ስትባል እንደምትኖር ኹሉ እርሱም “አምላክ ወሰብእ (ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው)” ሲባል ይኖራል /ሃይ.አበ.፷፯፡፯/፡፡ ተፈትሖ ሳያገኛት (ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ) እንደምን እንደወለደችው ግን የማይመረመር አንድም ሊነገር የማይችል፣ ከኅሊናት ኹሉ የሚያልፍ ድንቅ ነው፡፡
በማይመረመር ግብር ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. “ቃል ሥጋ ኾነ” እንዲል በእርሱ ፈቃድ /ዮሐ.፩፡፲፬/፣ “ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” እንዲል በአባቱ ፈቃድ /ዮሐ.፫፡፲፮/፣ “በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም እንደ ቀባው” እንዲልም /ሐዋ.፲፡፴፰/ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሰው ኾኖ አዳነን፡፡ ሊቁ እንዲህ ማለቱ “ወልድ ያለ ፈቃዱ ሰው ኾነ” የሚሉ መናፍቃን ስላሉ ነው፡፡ ሌሎች ሊቃውንትም፡- “የእግዚአብሔር ልጅ ያለ ፈቃዱ ሰው እንደ ኾነ የሚያምን፤ የሚያስተምር፤ ወይም የአብ ፈቃድ ሌላ ነው፤ የወልድ ፈቃድ ሌላ ነው፤ የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ሌላ ነው የሚል ቢኖር፤ ፈቃዳቸው አንድ፤ መንግሥታቸውም አንድ እንደኾነ የማያምን ሰው ቢኖር ውጉዝ ይኹን” ብለው አስተምረዋል /ሃይ.አበ.፻፳፫፡፪/፡፡

በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ፍጽምት የምትኾኚ እመቤታችን ሆይ! በድንግልና ጸንተሽ ብትገኚ ላንቺ የተሰጠሸ ጸጋ ፍጹም ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ካንቺ ጋራ አንድ ባሕርይ ቢኾን አንድም በጸጋ ቢያድርብሽ ባለሟልነትን አግኝተሸልና ለአንቺ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ ይህ ከቃላት በላይ የሚያልፈው ባለሟልነቷ ቅዱስ ባስልዮስ ከሌሎች ቅዱሳን ጋር እያነጻጻረ ሲያብራራው፡- “የዚህ ዓለም ነገር ኹሉ አይመጥናትምና የሚመጥናትን ምን ዓይነት ምስጋና እናቅርብላት? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን ሲናገር ዓለም አልተገባቸውም /ዕብ.፲፩፡፴፰/ ካላቸው ከከዋክብት በላይ ኾና እንደምታበራው ፀሐይ ለኾነችው ለአምላክ እናትማ ምን ልንል እንችል ይኾን?... ምን ምሥጢር እንደተከናወነ ተመልከት፤ ኅሊናን አእምሮን የሚያልፍ ነገር እንደኾነም አስተውል፡፡ ታድያ የአምላክ እናት ታላቅነት እንደምን ኹሉም ሰው አይናገር? ማንስ ነው ከቅዱሳን ኹሉ በላይ እንደኾነች ያላስተዋለ? እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ የሚልቅ ጸጋን ከሰጠና የሚነኩት ኹሉ ሰው ከበሽታው ከተፈወሰ፣ ጥላቸው ያረፈበት ተአምር ከተፈጸመለት፣ ጴጥሮስ በጥላው ካዳነ /ሐዋ.፭፡፲፭/፣ የጳውሎስ የልብሱ ዕራፊ መናፍስትን ካወጣ /ሐዋ.፲፱፡፲፩/ ለእናቱማ ምን ዐይነት ሥልጣንና ኀይል ተሰጥቷት ይኾን? በምን ዓይነትስ ሥጦታ አስጊጧት ይኾን? ጴጥሮስ፡- ክርስቶስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ስላለው ብፁዕ ነህ ከተባለና የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ከተሰጠው /ማቴ.፲፮፡፲፮-፲፱/ እርሷማ ከኹሉም ይልቅ እንዴት ብፅዕት አትኾን? /ሉቃ.፩፡፵፭/ ጳውሎስ ታላቅ ክብር ያለውን የክርስቶስን ስም በመሸከሙ ምርጥ ዕቃ ከተባለ /ሐዋ.፱፡፲፭/ የአምላክ እናትማ የምእመናን ምግብ የኾነ መናውን ሳይኾን የሕይወት ሰማያዊ እንጀራን ያስገኘች እርሷ ምን ዓይነት ልዩ ዕቃ ትኾን? … ነገር ግን ስለ እርሷ ብዙ እናገራለሁ ብዬ ስለ ክብሯ ጥቂት በመናገር ራሴን በኀፍረት ውስጥ እንዳልጨምር እፈራለኁ፡፡ ስለዚህ ከአሁን ወዲህ የንግግሬን መልሕቅ ስቤ በዝምታ ወደቤ ላይ ማረፍን መርጫለሁ”  ይላል /መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፣ ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣ ገጽ ፺-፺፩ ይመልከቱ/፡፡

ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያያት የወርቅ መሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲፰-፲፱/፡፡ መተርጕማኑ ይህ ምን ማለት እንደኾነ ሲያብራሩ፡- “ከምድር እስከ ሰማይ መድረሷ የልዕልናዋ፣ በላይዋ ላይ ዙፋን ተነጽፎባት ንጉሥም ተቀምጦባት ማየቱ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀኗ ለመሸከሟ፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ማየቱ ደግሞ ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ለማሳረግ አይወጡም አይወርዱም ነበር፤ ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከኾነ በኋላ ግን ለተልእኮ የሚወጡ የሚወርዱ ኾነዋልና ሲል ነው”  ይላሉ /ሉቃ.፪፡፲፬፣ ሐዋ.፲፡፫-፬፣ የኦሪት ዘልደትን ትርጓሜ ይመልከቱ/፡፡

ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ በአምሳለ ንጉሥ ካየው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡ

https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_12.html?m=
305 viewsGery, 19:44
ክፈት / አስተያየት ይስጡ