Get Mystery Box with random crypto!

ቀን 5 አይኖቼን ክፈት ከ2014 ወደ 2015 በጸሎት ለመሻገር እየተሳተፍን በምንገኝበት በዚህ | የህይወት ቃል / Word of life

ቀን 5
አይኖቼን ክፈት
ከ2014 ወደ 2015 በጸሎት ለመሻገር እየተሳተፍን በምንገኝበት በዚህ መርሃ ግብር፣ የዛሬው የጸሎት ርእሳችን የሚያተኩረው በአይናችን ላይ ሲሆን “ዐይኖቼን ክፈት” በማለት ወደ ጸጋው ዙፋን እንቀርባለን።
ይህ ጸሎት እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ለመረዳት ጌታችን ኢየሱስ ስለ ዐይን ሲናገር እንዲህ ያለውን ማስታውስ ተገቢ ነው ፦
“ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል።” ማቴ 6:22
በተለይም ደግሞ የልቦናችን ዐይን ካልበራና የአምላካችንን መገኘትና የእርሱንም ሃሳብ ካላስተዋልን ሕይወት በጨለማ እንደመዳከር ይሆንብናል።
ይህንን የተረዳው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ሲጸልይ እንዲህ በማለት ነበር የጻፈው ፦
“እንዲሁም በእርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ። ” ኤፌ 1:18፣ 19
“ዐይኖቼን ክፈት” በማለት ስንጸልይ ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደሆነ እንድናስተውል ሊሆን ይገባል።
በእርግጥም ዐይናችን ሲከፈት የተጠራንለትን ተስፋ እናስተውላለን። ይህ ተስፋ ደግሞ ታላቅ የሆነው የእግዚአብሔር ኀይል በእምነት በተቀበሉት ህይወት ውስጥ እንደሚሰራ ዋስትና የሚያስጨብጠን ተስፋ ነው።
ዛሬ ምልናባት የእግዚአብሔርን ቃል በዘልማድ የምናነብና ቃሉም ከእኛ ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ተዋህዶ እየጠቀመን ካልሆነ፣ ጌታ ዐይናችንን እንዲያበራልንና በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን ተአምራት አድራጊውን የእርሱን ድንቅ ኀይል ለማየት እንጸልይ።
ጌታችን ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ በኤማኡስ መንገድ ላይ እየጠወለጉ የሚሄዱ ደቀመዛምርት ነበሩ። “በቃ! ተስፋ ያደረገነው ከዳን! ተስፋችን ሞተ!” እያሉ ያዝኑ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ተነስቶ ድንገት ከእነርሱ ጋር አብሮአቸው መጓዝ ጀመረ። በጉዟቸው መጨረሻም ዐይናቸው ተከፈተና ተስፋቸው መና እንዳልቀረ ይልቁንም ህያው እንደሆነ ተረዱ።
ዐይናቸው በተከፈተ ጊዜ ኀይላቸው ደግሞ ታደሰ። ህይወታቸው ተለወጠ።
አባት ሆይ፣ እኛም የልባችን ዐይኖች እንዲበሩልንና የአንተን ማንነትና ለእኛም የተሰንጠን ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይልን እንድናስተውል ዐይናችንን ክፈትልን። አሜን።