Get Mystery Box with random crypto!

ቀን 3 “ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ከ2014 ወደ 2015 በጸሎት ለመሻገር በምንሳተፍበት | የህይወት ቃል / Word of life

ቀን 3 “ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው”
ከ2014 ወደ 2015 በጸሎት ለመሻገር በምንሳተፍበት በዚህ መርሃ ግብር፣ በግልና በጋራ ስለሰራነው ኃጢአት ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ልንጠይቅ እንደሚገባ አይተናል። ዛሬ ደግሞ በእኛ ላይ በደል ለፈጸሙብን ከእስጢፋኖስ ጋር በመተባበር “ጌታ ሆይ፣ ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ብለን ከልባችን እንጸልይ።
ቂም ከምንም በላይ የሚጎዳው ያቄመውን ሰው ሲሆን ፣ይቅር ማለት ደግሞ ከሁሉም በላይ ነጻ ሚያወጣው ይቅር ባዩን ነው። ቂም ወደ ራሳችን አዙረን የያዝነው ጩቤ ነው። እንጎዳዋለን ብለን ያሰብነውን ሰው ከምንጎዳው በላይ እራሳችንን እንደምንጎዳ ቂም ይዘን የምናውቅ ሰዎች እናስተውላለን። አንድ ወዳጄ አበሳጭቶኝ በቂም የተሞላሁበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። በመንገድ ባየሁት ቁጥር ውስጤ በንዴት ይቃጠላል። በተለይ በተለይ ባገኘሁት ቁጥር ከሌሎች ጋር ሲሳሳቅ ሲደሰት አየው ነበርና፣ ናብከደነጾር ሰባት እጥፍ እንዳነደደው እሳት የኔም የንዴት እሳት ሰባት እጥፍ ይነድ ነበር። በእርግጥም ቂም ወደ ራሴ አዙሬ የያዝኩት ጩቤ እንደሆነ ተረዳሁ። እናንተስ? እስኪ የየራሳችሁን ተሞክሮ አስታውሱ ቂም በመያዛችሁ ሰላማችሁ ፣ ደስታችሁ፣ እረፍታችሁ ጨመረ ወይስ ቀነሰ? ጠቢቡ ሰለሞን ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦”በደልን ንቆ መተው መከበሪያው ነው” ምሳ 19፥11።
መጽሐፍ ቅዱስ በደፈናው ይቅር በሉ አላለንም። ይልቁንም “ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ” (ቆላ 3፥13) ነው የሚለው። ይሄንን በትክክል መረዳት ይኖርብናል። ምክንያቱም ብዙዎች ይቅርታን ስናደርግ ክርስቶስን ሞዴል ከማድረግ ይልቅ ከቃሉ ጋር የማይስማሙትን አለማዊ አካሄዶች የምንከተል ስለሆንን ነው። አንዳንዶቻችን “መጥቶ እግሬ ስር ካልተንደባለለ ይቅር አልለውም!” የምንለው መፈክር አለን። ጌታ ግን ይቅር ያለን ገና ጠላቶቹ ሳለን መሆኑን አንርሳ። እኛንም ያስተማረን አንደዚያው እንድናደርግ ነው። እስጢፋስኖ የጌታችን የኢየሱስን ሞዴል ነበር የተከተለው። በሃሰት ተወንጅሎ፣ በድንጋይ ሲወገር፣ እርሱም እንደ ጌታው “ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ ጸለየ።
አባት ሆይ፣ ቂም ይዘን በቀልን ተጠምተን ከአመት አመት እንዳንሻገር፣ ይልቁንም አንተ ጠላቶችህ ሳለን ይቅር እንዳልከን፣ እኛም ጠላቶቻችንን ይቅር እንድንል በጸጋህ እርዳን። አሜን።