Get Mystery Box with random crypto!

ቀን 2 “ኃጢአትን ሠርተናል፥ … አቤቱ፥ ይቅር በለን፤” ከ2014 ወደ 2015 በጸሎት ለመሻገር | የህይወት ቃል / Word of life

ቀን 2 “ኃጢአትን ሠርተናል፥ … አቤቱ፥ ይቅር በለን፤”
ከ2014 ወደ 2015 በጸሎት ለመሻገር በምንሳተፍበት በዚህ መርሃ ግብር፣ ትናንትና የግል ኃጢአታችንን ይዘን ዳዊት “አቤቱ ማረኝ” ብሎ የጸለየውን ጸሎት በመጋራት በእግዚአብሔር ፊት በንስሓ ቀርበናል።
ዛሬ ደግሞ ከዳንኤል ጋር በመተባበር ስለ ግል ብቻ ሳይሆን በማህበር ስለሰራነው ኃጢአት በንስሓ በእግዚአብሔር ፊት በመቅረብ የእርሱን ምሕረት እንለምን። ምንም እንኳን ዳንኤል የአምላኩን ፈቃድ ይከተል የነበረም ቢሆን፣ ነገር ግን የሕዝቡን ኃጢአት እንደራሱ በመቁጠር “በድለናል፣ ክፋትን አድርገናል” እያለ በንስሓ በአምላኩ ፊት ስለ ህዝቡ ዐመፅ ይቅርታን ለመነ።
እኛም ተመሳሳዩን መንፈስ በመጋራት በምድራችን ላይ ስለተፈጸመው ክፋት በደል፣ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር የፍቅር ሕግ ዘወር ብለን በጥላቻ ስለተፈጸሙት ድርጊቶች ሁሉ “አቤቱ፣ ይቅር በለን” እያልን ይህንን ዳንኤልን ጸሎት ከልባችን እንጸልይ።
“ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፤ ጌታ ሆይ፤ እኛ ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናልም፤ ክፋትን አድርገናል፤ ዐምፀናልም፤ ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል። …
እግዚአብሔር ሆይ፤ እኛና ንጉሦቻችን፣ ልዑሎቻችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኀጢአት ስለ ሠራን በኀፍረት ተከናንበናል። ምንም እንኳ በእርሱ ላይ ያመፅን ብንሆን፣ ጌታ አምላካችን ይቅር ባይና መሓሪ ነው። እግዚአብሔር አምላካችንን አልታዘዝነውም፤ ደግሞም በአገልጋዮቹ በነቢያት በኩል የሰጠንን ሕግ አልጠበቅንም፤ …
“አሁንም አምላካችን ሆይ፤ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ። ጌታ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ። አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው። ጌታ ሆይ፤ አድምጥ! ጌታ ሆይ፤ ይቅር በል! ጌታ ሆይ፤ ስማ! አድርግም፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ።” ዳንኤል 9፡ 4-20
አዎ፣ ስለጽድቃችን ሳይሆን ስለ ታላቅ ምሕረቱ አምላካችን የእኛንና የህዝባችንን በደል ይቅር ብሎ እንዲደርስልን እንጸልይ።
አባት ሆይ፣ እኛም ዳንኤል እንደ ስለራሳችንና ስለሕዝባችን ኃጢአት በፊትህ በስሓ እንቀርባለን፤ ስለታላቅ ምሕረት ብለህ ቅር በለን። በቃችሁ በለን። አሜን።