Get Mystery Box with random crypto!

በጸሎት መሻገር ቀን 1 “ማረኝ” በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር 2014ን ሸኝተን 2015ን ለመቀበል ዛሬ | የህይወት ቃል / Word of life

በጸሎት መሻገር
ቀን 1 “ማረኝ”
በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር 2014ን ሸኝተን 2015ን ለመቀበል ዛሬን ጨምሮ አስራ አራት ቀናት (ሁለት ሳምንት) ብቻ ቀርተውናል። ታዲያ አሮጌ ሊባል ትንሽ ከቀረው ከያዝነው አመት ወደ አዲሱ አመት በእግዚአብሔር የጸጋ ዙፋን ፊት ልዩ ቆይታን በማድረግ አብረን በጸሎት እንድንሻገር ለውድ አንባቢዎቼ ጥሪ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ። በሕይወት ብንኖርና ጌታ ቢፈቅድ ከዛሬ ጀምሮ በየማለዳው በተለየ ጸሎት ወደ ጌታ በመቅረብ በአዲስ መንፈስ ወደ አዲስ አመት መግባት እንዲሆንልን ልባዊ ጸሎቴ ነው።
ታዲያ ዛሬ በዚህ የጸሎት መርሐ ግብራችን የመጀመሪያ ቀን በእግዚአብሔር ፊት የምንቀርብበት የጸሎት ርእስ የእግዚአብሔርን ምህረት ለግል ኃጢአታችን የምንጠይቅበት ሊሆን ይገባል። እስቲ መለስ ብለን ያለፉትን የአመቱን ቀናት እንዴት እንዳሳለፍናቸው እንቃኝ። ንስሓ ያልገባንባቸው ኃጢአቶች ይኖሩ ይሆን? አሁንም ድረስ የምንወድቅ የምንነሳበት፣ የምናነክስበት የኃጢአት ልምምድ ይኖረን ይሆን?
ዳዊት በፈጸመው ከባድ ወንጀል ልቡ በተሰበረ ጊዜ ያቀረበውን እንዲህ የሚለውን ልመና እኛም ከልባችን እንጸልየው፦
"እግዚአብሔር ሆይ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ"፡፡ መዝሙረ ዳዊት 51:1
ይህንን ልመና በትክክል ለማቅረብ ደግሞ የሚከተሉትን ሦስት ነጥቦች ማስተዋል ያስፈልገናል።፡፡
1. ይህንን ልመና የሚያቀርብ ሰው በቅድሚያ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረት እንዳለ ሊያምን ይገባል።
"የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት፣ ሁሉን ቻይነት፣ ቅድስናው ሁሉ የሚገርሙ ባህርያቱ ናቸው።፡፡ ምህረቱ ግን ከነዚህ ሁሉ በላይ አስደናቂ ነው። ሊያጠፋን ሲችል፣ ከአእምሮእችን በላይ የሆነውን መስዋእትነት ከፍሎ፣ ይሄውም በመስቀል ላይ ራሱን በመስጠት፣ ይቅር ሊለን መረጠ። እንግዲህ "ምህረት አድርግልኝ" ስንል በእርሱ ዘንድ ይህ ምህረት እንዳለ በማስተዋል እንቅረብ።
2. ይህንን ልመና የሚያቀርብ ሰው ምህረት እንደሚያስፈልገው የሚያምን መሆን አለበት።
ምህረት 'ይገባናል' ብለን የምናገኘው ጉዳይ አይደለም።፡፡ ለኃጢአተኛው የሚገባው ሞት ሲሆን፣ ይህንን ደሞዙን ለኃጢአተኛው መክፈል ደግሞ ለእግዚአብሔር የቅድስናውን ክብርን አያጎድልበትም።፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀድሞ በተሠራ ጽድቅ ምህረት ይገባኛል ብሎ መጠየቅ አይቻልም።፡፡ እናም በሃጢአት ለወደቀው ሰው ብቸኛው ማምለጫ የእግዚአብሔር ምህረት ነው።፡፡
3. ይህንን ልመና የሚያቀርብ ሰው ምህረትን ለመቀበል የሚናፍቅ ልብ ሊኖረው ይገባል።፡፡
ለአንድ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ምህረት መኖሩንና፣ ያም ምህረት ለእርሱ እንደሚያስፈልገው ማወቅ ብቻውን በቂ አይደለም።፡፡ ይልቁንም ይህንን ምህረት በግል ለመቀበል መጓጓትና ‹‹እኔን ማረኝ›› ማለት ያስፈልጋል።፡፡ እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑን ማወቅ ብቻውን ሩቅ አያስኬድም፤ ምህረቱን በግሉ ያልተካፈለ ሰው የበረከቱ ተካፋይ ሊሆን አይችልም።
አባት ሆይ፣ አንተ መሐሪ መሆንህን በማስተዋል፣ እኔ ደግሞ ምሕረትህ የሚያስፈልገኝ ኃጢአተኛ መሆኔን በመረዳት፣ "እንደ ቸርነትህ መጠን ምሕረት አድርግልኝ" ብዬ ከልቤ እንድጸልይ እርዳኝ። አሜን።