Get Mystery Box with random crypto!

ካርታ ማምከን/የይዞታ ማረጋገጫ መሰረዝ/ ==================== የማይንቀሳቀስ ንብረት ባ | Tsegaye Demeke - Lawyer

ካርታ ማምከን/የይዞታ ማረጋገጫ መሰረዝ/
====================
የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ማስረጃ /ደብተር ወይም ካርታ/ በመሰረዝ ዋጋ ማሳጣት
አንድ የአስተዳደር አካል የቤት ባለቤትነት ማስረጃ በፈለገው ጊዜ ከሕግ ውጪ እንዲሰረዝ ማስቻል በኢ.ፌ.ዲ. ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 40/1/ እና /2/ ድንጋጌ ሥር የተከበረውን የንብረት ባለቤትነት መብት ዋጋ የሚያሣጣው ነው፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195 እና 1196 ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲነበቡም የአስተዳደር አካል በባለቤት ማረጋገጫ ማስረጃ አሰጣጥ ላይ ፍጽም የሆነ አስተዳደራዊ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ አያሣዩም፡፡ ይልቁንም ድንጋጌዎች እርስ በእርሣቸውም ሆነ ከፍ/ሕ/ቁጥር 1198 ድንጋጌ ጋር ተዛምደው ሲታዩ የባለቤት ማረጋገጫ ደብተር የሚሰረዘው በሕጉ በተመለከቱት ምክንያቶች ብቻ መሆኑን ከሕጉ ውጪ ተግባሩ ተከናውኖ ከተገኘም መብቱ የተነካው ሠው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37፣78 እና 79 ድንጋጌዎች መሠረት ጉዳዩን ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አቅርቦ አቤቱታው እንዲታይለት የሚያርግበት ጉዳይ እንጂ አስተዳደር አካሉ የሰጠው ውሣኔ በፍርድ ቤት እንዳይታይ የሚገደብበት ስርዓት የሌለ መሆኑን የምንገነዘበው ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 42501 ቅጽ 15፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 37፣ 38፣ 79፣ ፍ/ህ/ቁ. 1195፣ 1196፣ 1198
አስተዳደራዊ ተቋማት በሕግ ተለይቶ በተሰጣቸው ጉዳይ የመወሰን ሥልጣን እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና ለአንድ ባለ ጉዳይ የተሰጠው ካርታ የተሰጠበት እና የተሻረበት አግባብ በሕግ አግባብ መሆን ያለመሆኑን አጣርቶ የመወሰን ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንድ ፍርድ ቤት የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታን የመሰረዝ ሥልጣን የአስተዳደር ክፍል ነው፣ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ የመወሰን ሥልጣን የለውም በማለት የሚደርስበት ድምዳሜ የጉዳዩን የክርክር ባህሪ እና ይዘት ያላገናዘበ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በአስተዳደር ክፍል የተሰጠው ካርታ የተሰጠበት ወይም የተሻረበት ሥርዓት እና አስተዳደራዊ ውሳኔው ሕግና መመሪያ ያገናዘበ መሆን ያለመሆኑን በማጣራት ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን እንዳላቸው ከፍ/ህ/ቁ. 1196 እና በህገ መንግስቱ ስለ ንብረት መብት ከአደረገው ድንጋጌና በፍርድ የሚያልቁ ጉዳዮችን በተመለከተ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 37 ከተመለከቱት ድንጋጌዎች ይዘት የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ 99071 ቅጽ 18፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 37፣ ፍ/ህ/ቁ. 1196