Get Mystery Box with random crypto!

'እኔ እስክመጣ ድረስ ለማንበብ [ልታነብላቸው]፣ ለመምከርና ለማስተማር ትጋ' (1 ጢሞ 4፡13) | አስተምህሮተ 🔱ክርስትና

"እኔ እስክመጣ ድረስ ለማንበብ [ልታነብላቸው]፣ ለመምከርና ለማስተማር ትጋ" (1 ጢሞ 4፡13)

ከወደቅንባቸው ታላላቅ ነገሮች መካከል ብዬ ከማስባቸው አንዱ፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ «የግል መንፈሳዊ ልምምድ» ብቻ ማድረጋችን ነው። እንደ ክርስቲያናዊ ማኅበረብ፣ የኅብረት ጾም፣ የኅብረት ጸሎትና አምልኮ እናደርጋለን። እንደ ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ ግን በጉባኤ ወይም በቡድን በጋራ ቁጭ ብሎ ረጃጅም የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባባት የማንበብ ልማድ ግን አላዳበርንም። ይህ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ያስከተለው አያሌ ጉዳት ያለ ይመስለኛል። ዕዝራ "ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ፣ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ያነብ" ነበር። ጳውሎስም ለሌሎች ያስነብብ ነበር። ኢየሱስ በሙኹራቦቻቸው መጻሕፍትን ያነብ ነበር። አቡቀለምሲሱ ዮሐንስ ጠቅላላ የራዕዩን መጽሐፍ ለታዳሚው "የሚያነብ ብፁዕ ነው" ይላል፤ "የሚሰሙትም የሚያደርጉትም ብፁዓን" ናቸውም ብሎናል።

እውነት ነው፣ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሞላ ጎደል በግል ማንበብ እድል ስላልነበራቸው (በዋነኝነት የግል ቅጂ መያዝ እጅግ ውድ በመሆኑ፣ አንዳንዱም ማንበብ ስለማይችሉ) በጉባኤ እንዲነበብ መታዘዙ የግድ ነው። ግን ይህ ብቻ ነው ብሎ ለመስውሰድ ያዳግተኛል። ሲጀመር፣ ብዙዎቻችን በግል ዲሲፕሊን ኖሮን ለማንበብ የምንቸገር ስንት ነን? የቃሉስ ንባብ "በግልህ ብቻህን የምትጋፈጠው እንጂ የጉባኤ ልማድ አይደለም" ብሎስ ማን አዘዘን? ይህን ስል በግል ቅዱሳት መጻሕፍት ማንበብና ማሰላሰል «ጣል፡ ጣል እናድርግ» እያልኩ አይደለም። ተቃራኒውን እንጂ። እንደ ሕዝብ አንድን ንባብ አንብበን፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ አንድ ሕዝብ ቢመክረን፣ ቢገስጸን፣ ቢናገረን...አንዳንዴ በሳቅና በእንባ...አንዳንዴም ተንበርክከን ቃሉ እንደ ወንዝ ቢፈስ፣ ምን አለበት ግን? ሁለት ሰዓት ቁጭ ብለን ፊልም እያየን? አራት ሰአት "ቢንዥ ተከታታይ ፊልም" እያየን? ሦስት ሰአት አምልኮ በፉጨት እየዘመረን? ምን አለበት? ግን ደግሞ ወደ እግዚአብሔር «ኧረ ጠፋን መልሰን!» ብለን እንጮኻለን አይደል? መጮኹስ አይቅር። አብዝተን እንጩኽ። ግን ሠይፍ የሆነውንና ኀያል-ቃሉ እየተደመጠ ብንጮህ እንደቃሉ ቃሉ ይሠራል። በምስባኮቻችን «አንድም ቀን ተነበው የማያውቁ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት አሉ» ብላችሁ ታምናላችሁ? አታምኑም! ስንት ዓመት ነበር ያገልገልኩት...ስንት አመት ነበር በአንድ አጥቢያ ያመለኩት...የትዬ ለሌ! ነገር ግን በጉባኤ ተነበው ያልተመከርንባቸው፣ የልተገሰጽንባቸውና ያልተጽናናንባቸው አያሌ ምንባባ አሉ ብላችሁስ! አታምኑኝም። ይህ የኔ ብቻ ልምምድ ነውና። እግዚአብሔርም ያድርገው። ይህ የኔ ብቻ ገጠመኝና ቅዠት ሆኖ እኔ በጠፋሁ። እኔ ውሸተኛ በሆንኩ። ግን ከዚህ ቅዠት አልነቃ አልኩ።

የሮሜ ደብዳቤ እኮ፣ በአንድ ቁጭታ ነበር ለጉባኤው የተነበበው። እውነት ነው ምናልባት አገልጋይቱ ፌበን አሊያም የቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች ለረጅም ሰዓታት፣ በተከታታይ ሰንበት ለሕዝቡ እየተነተኑ ማብራሪያ እንደሰጡ ጥርጥር የለውም። ግን የ16ቱ ምዕራፍ ንባቡ አላጠረም:: እናም፣ የቃሉ ንባብ ጋር ስንመጣ ረጅም ንባብ አይደብረን። ለምን በስቅለቱ ሰሞን ወንጌላት አይነበቡም? ቢያንስ ኢየሩሳሌም ከገባበት ቀናት ጀምሮ እስከ ስቅለቱ የወንጌል ትራኬ በጉባኤ ቢተረክልን ምናለበት? ቁጭ ብለን። ተንበርክከን። ቆመን። ደግሞ እሁድ የትንሳኤውን ንባባት፣ እያጨበጨብን!

ማን ነው የቃሉ አገልግሎት በ30-40 ደቂቃ ስብከት ብቻ ይወሰን ያለን? ማለቴ፣ እንዴት በሳምንት በ30 ደቂቃ ሕዝብ እንዲለወጥ፣ የአስተሳሰብ ተሓድሶ እንዲመጣ እንጠብቃለን? ምንስ እንደዚያ ይመጣል? ሕዝብ እንዲያ ተለውጦ ያውቃል? አድማሳዊ የሆነ (የፓራዳይም) ለውጥ በቅጽበት መጥቶ ያውቃል? ግን ደግሞ "ጸጋው" ጎደለብን አይደል? ለመቆም ጉልበት አጣን፣ ኀጢአት በላይና በታች አወከን አይደል? የስህተት ትምህርት በግራና በቀኝ አጣፋን አይደል? ላዩም ጆሯችን ጭው እስኪል ድረስ። ልጆቻችን እንግዳ ልምምድ ውስጥ ገቡ አይደል? ግራ ተጋባን! ይህ ሁሉ በጉባኤ ንባብ አይፈታም። መች በቀላል። ግን ወደ መሠረታዊውና ወደ ዋነኛው መመለስ፣ የት እንደወደቅን አውቀን ወደ ሚበጀን መመለስ ጥበብ ይመስለኛል። ደግሞስ "ሊያንጻችሁና በቅዱሳኑ ሁሉ መካከል ርስት ሊያወርሳችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል ዐደራ" ሰጣቸው (ሐዋ 20፡32) ሲል፣ ቃሉ ጉልበት እንዳለው ታሳቢ ያደረገ ነው አይደል? እንደ ጉባኤ አንድን ነገር ሰምተን፣ ተመሳሳይ ምላሽ ለቃሉ ስንሰጥ እድገታችንም እንዲሁ ብስለታችንም እንዲሁ እያደገ የሚመጣ ይመስለኛል።

ጳውሎስ በአንድ ከተማ ለጥቂት ሳምንታት ቢበዛ ለጥቂት ወራት ነበር ሰብኮ፣ ቤተ ክርስቲያን ተክሎና መሪዎችን ሾሞ የሚሔደው። ለምሳሌ በተሰሎንቄን የነበረው ቆይታ ቢያንስ ለሦስት ሰንበታት ወይም ቢያልፍ ጥቂት ሳምንታት ነበር (ሐዋ 17፡2-10)። ከኤፌሶንና ከቆሮንቶስ በስተቀር ይህ ልማዱ ነበር። ግን ምን ያህል በየዕለቱ የትየሌለ የሚያህል የብሉይ መጻሕፍትን (ከሰብዓ-ሊቃናቱ? ወይም መሰል የግሪክ ትርጉም?) ቢያነብላቸው ይሆን፣ በመልእክቱ ሁሉ ከልጅነታቸው ጀምሮ ብሉይን እንዳነበቡ ሰዎች የሚጽፈው። የገላትያን መልእክት ተመልከቱ። እነዚህ ሰዎች ብሉይ ንባባትን ከልጅነት ጀምሮ የሚያውቁ እንጂ ለአፍታ ከጥቂት ጊዜ በፊት አብርሃም የሚባል ሰውና የድነቱን ትራኬ፣ ኢሳያስ የተባለ ትንቢትና የትድግናውን ተስፋ (ከነትንታኔው) የማያውቁ እንደነበሩ የሚጠቁም የለም። በተጨማሪም፣ ለከፍ አድርጎ የሚያልፋቸው፣ ብሉይን ንባባት አስደምመው (allusions) የሚያልፉ ጽሑፎቹ፣ ከአንባቢያኑ ምን ያህል የብሉይ ንባባትን እውቀት እንደሚጠብቅ ያስረዳል። እነዚህ ሰዎች በአጭር ጊዜ በቅዱሳት መጻሕፍት ባህር ውስጥ እንደሚዋኙ ሰዎች ነበር የሞገታቸው። ምን እያልኩ ነው? የቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን ልማድ ነበር።

በጉባኤ ማንበብ ግን ብቸኛ አማራጭ አይደለም። ዛሬ ዙም አለ። ስልክ አለ። በአካል የሚገኝ በአካል፣ ካልሆነም በርቀት ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ጉባኤ ማንበብ ይቻላል። የግድ በሰንበት ስብስባችን መሆን የለበትም። ዋናው ቁም እንደ ጉባኤ በአንድነት መነበባቸው ላይ ነው። የዚያን ጊዜ አንድ ነገር ይሆናል። በስብከት እንዲተጋ የእግዚአብሔር ጸጋ የበዛለት "በዚህ ቃል እስኪ አበረታታንና ምከርን" ሕዝብ ይላል። በማስተማር የሚተጋውን "እዚህ ጋር ጥያቄ አለን፦ በዚህ ንባብ ጸሐፊው 'ምን ለማለት ፈልጎነው' ተንትነህ አስረዳን" ጉባኤው ይጠይቃል። የጸሎት ኮረንቲ የሚያቀጣጥለውም፣ "ኧረ በዚህ ቃል ላይ እንጸልይ" ይላል። የቅኔው ሰውም፣ ቃሉን በዜማ ቅኔ አድርጎ ይዘርፈዋል። ተሓድሶ ዝም ብሎ አይመጣም። ለመታደስ ማደስ ያሉብንም ነገሮች አሉ። ከእነዚህ መካከል፣ በዋነኛነት፣ የቃሉ ንባብ ወደ ሕዝበ ክርስቲያኑ መመለሱ ነው።

ጌታ ሆይ ከቃልህን ረሃብ፣ ቃልህን ወደ መራብ አምጣን!

"ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣
ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣
በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።" (ኢሳያስ 66:2)

ሳምሶን ጥላሁን