Get Mystery Box with random crypto!

ከራስ ጋር ትግል ተከታታይ ልብወለድ ምዕራፍ=ሁለት ክፍል=54 ሳባ | CHRIST TUBE - ETH🇪🇹

ከራስ ጋር ትግል
ተከታታይ ልብወለድ
ምዕራፍ=ሁለት
ክፍል=54
ሳባ ካሳሁን

ያልጠበቅነው ጭራሽም ያላሰብነው ነገር አየን መሀላቸው ያለችው ሰው ሊያ ነበረች ዐይኔ ያየውን መቀበል ሲያቅተኝ በፍርሀት ይዤው የነበረውን የናሆምን ኮት እጆቼ በመወዛገብ ዝለው ለቀቁት ሁላችንም በጥያቄ ተሞላን "ሊያ እዚህ ምን ታደርጋለች?" ብዬ ለማሰብ ሞከርኩ አፋችን ማውራት አቅቶት ተሳስሮ ሳለ በድንገት ሊያ ከት ብላ ደስ በሚል ግን በዚያ ሰዐት ላይ በሚያወዛግብ ሳቅ ሳቀችብን ከበዋት የነበሩ እኛንም መከራ ፍዳችንን ያሳዩን ከሊዱዬ ጋር ስንመጣ ያገኘናቸው ሰዎችም ድክም ብለው መሳቅ ጀመሩ በሰዐቱ "እኔ አብጄ ነው? ወይስ እነሱ?" ብዬ ይባስ ማሰብ እስኪያቅተኝ ግራ ተጋባሁ ሊያ ወደኛ ጠጋ አለችና ሰዎቹ ዞር እንዲሉ አደረገች የዚህን ጊዜ ሊዱም ልክ እንደነሱ እየሳቀች ድፍን ሀገራችን በሚያውቃት ፍልቅልቅነቷ ሮጣ መጥታ ተጠመጠመችብን ሁላችንም ልክ እንዳየናት ነገሩን መቀበል አቅቶን በመሬቱ ላይ ድፍት ብለን ተቀመጥን ሁኔታው እጅጉን ተወሳሰበብኝ ምንም ሳይቆዩ እነ ኬብሮን ሳሮንና በዚያ ቤት ውስጥ የለመድናቸው ፍቅራቸውን ወደን የተገዛንላቸው ልጆች እነሱም እየሳቁብን እያሽካኩ መጥተው ተቀላቀሉን። ህልም ወይ ቅዠት መስሎ የታየው ቢኒ ነገሩን መቀበል አቅቶት ከወደቀበት መሬት ብድግ እያለ "....አልገባኝም. .ምን እየተፈጠረ ነው?" ብሎ ሁሉንም በጥያቄና በመወዛገብ አስተያየት ተሞልቶ ጠየቃቸው ይህን ጊዜ ሊያ ደስ በሚል ፈገግታዋ ተሞልታ ጠጋ አለችውና "አይዟችሁ ጓደኞች ሁሉም ነገር ጨዋታ ነው ሁላችንም አቀናብረነው ነው ሀሳቡን እነ ሳሮን አመጡትና ሜሪን ልንወስዳት ስንል የላክነው ልጅ ስለማያውቃቸው ተምታተውበት ሊዱን አመጣት. . ብቻ ውዶች ሁሉንም ነገር በስልክ ቀድተነዋል ታዩታላችሁ!!" አለችን ሁሉም በእኛ መዝናናታቸውን አላቆሙም ነበር ናሆሜ እጅጉን በንዴት ተሞልቶ "ድንቄም ጨዋታ!!" አላቸውና ሊያያቸው እንደማይፈልግ እንደተበሳጨ ለማሳወቅ የኔንና የቢኒን እጅ ይዞ እንድንሄድ ጠየቀን።
ለመረጋጋት እየሞከርኩ ስለነበር ድርቅ ብዬ መሄድ እንደሌለብን አምኜ አሳመንኩት ሁሉም መደንገጣችንን ስላዩ እንድንረጋጋ ዝም ብለውን ለራሳቸው የቀረፁትን የድምፅ ቅጂ ማዳመጥ ጀመሩ በሰዐቱ እንዲህ ብዬ ተረዳሁት እንጂ ነገሩስ ሌላ ነው በመካከላችን ሰፋ ያለ ርቀት ነበር እነሱ በአንድ ቦታ ተሰባስበዋል እኛ አራታችን የአብርሀም በጎች ደግሞ በሀሳብ ተክዘን ማውራት አቅቶን ተቀምጠናል ሊያ ሀሳቧን በስልኩ ላይ የጣለች መስላ ትኩረቷ ግን በእኛ ላይ ነበር ድመት ዐይጥን ለማጥመድ አድፍጣ የምትጠብቀውን ያህል እሷም አይንና ጆሮዋን ወደኛ ቀስራ ተወጥራለች። ዝም ስንል ሊዱዬ ተቀይመን ያኮረፍናት መስሏት በእጆቿ ያዝ አድርጋን እየተንሰፈሰፈች "ጓደኞቼ በእውነት በእናንተ እምላለሁ እኔ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም ብቻ ግን ሰውዬው ይዞኝ ከወጣ በኋላ ከዚህ የባሰ በቅጡ እንኳን በር የሌለው በረጅም መስኮት ተዘሎ የሚገባበት ቤት አስገብቶኝ እዚያ ውስጥ ብዙ ከተቀመጥኩ በኋላ እነ ሊያ ሲጨቃጨቁ ድምፃቸውን ሰማሁና በተደጋጋሚ ስጣራ ሁሉም ተሰባስበው መጥተው ጨዋታ እንደሆነ ነገሩኝ ከዛ እንደማይሆንና እናንተ እንደምትጨነቁ ስለማውቅ ቶሎ ወደዚህ እንድንመጣ ነገርኳቸው" ብላ እየተቁለጨለጨች አየችን እኛም በእሷ ስለማንጨክንና ልናስጨንቃት ስላልፈለግን ጥያቄ ሳናበዛ ነገሩ ይበልጥ ግልፅ ሆኖልን ጨዋታ የተባለውንም ወጥመድ በተደፈነው አይናችን ጨዋታነቱን ብቻ አምነን ተረጋጋን ወዲያው ሊዱን እቅፍ አደረግናትና ዕርስ በዕርሳችን ያሳለፍነውን ያሰብነውን የቀባጠርነውን ሁሉ እያሰብን ከት ብለን መሳቅ ጀመርን ሊያም እየሮጠች ወደኛ መጣችና ". . .እ እናንተ ጉደኞች አሁን ተረጋጋችሁ?!" ብላ ያወራነውን ደግማ እየነገረችን ቀለደችብን ቀስ በቀስ ሁሉም መጡና እነሱም በእኛ እየሳቁ ተመልሰን ወደዚያ ቤት ደስታ ገባን በዚህ መሀል ሁላችንም በጣም የምንወደው ከመካከላችን በኮልታፋነቱ የሚታወቀው ምስኪኑ ጓደኛችን ሱራፌል ግን በፊቱ ላይ የሆነ መልዕክት ያሳውቀን ይመስል ዐይን ዐይናችንን እያየ በሀሳብ ተውጧል እኛ ግን በዙሪያችን ባለው ሆይታና ጫጫታ ተሞልተን እንደ መፅሀፈ ቅዱሱ ሳምሶን በብዙ ደሊሊዎች ተከበን ቀናት ቀናትን እያስቆጠሩ የዐይናችንን ዕይታ በአለም ነገር ላይ እንደተከልን ከፈጠረን በላይ ፍጡርን እያስቀደምን ፍቅርን ካስተማረን ይልቅ ፍቅር ናቸው ብለን ካመንናቸው እየዋልን፣ ካደግንበት ካሳደገን ክፉ ደግ ከተማርንበት መንፈሳዊ እህት ወንድም ከልብ የሆነ ትህትናን ከተማርንበት ሁሉ ነገራችን ከሆነው ቤተክርስትያን እየሸሸን የእነሱ ደስታ የእኛ መኖር፣ መልበስ፣ መደሰት መሳቅ የሆነው በእኛ ብዙ ነገር ያዩ ቤተሰቦቻችንን እየራቅን ለእኛ በጊዜው ደስታ መስሎ የታየንን ስናሳድድ የአለም ነገርን ክንፍ እስክንል እየወደድነው ክረምቱ አልቆ አዲሱ ዐመት ብቅ አለ ለብዙዎች ሌላ ተስፋ የሆነው መስከረም ጠባ።

ከዚህ ቀደም አዲስ ዐመት በመጣ ቁጥር ነጋ አልነጋ እያልን እንቅልፍ አጥተን መንጋቱን ለማየት የመኝታ ቤታችንን መስኮት አብዝተን እየተመለከትን ልክ ወፍ ሲንጫጫልን የለበስነውን ልብስ እንኳን ሳንቀይር በጉጉት እየፈነጠዝን ሁሌ ወደማንጠፋበት ቸርች እንሄድና የበዐሉ ፕሮግራም ገና ሳይጀመር ብርክክ ብለን ጌታን እንዲህ እንለው ነበር "አባታችን ሆይ በዐመታት ላይ ዐመታትን ጨምረህ እኛን ደግሞ ለዚህ ጊዜ አብቅተህ ይህን ቀን በሰላም እንድናይ ስለረዳኸን እናመሰግንሀለን ጌታ ሆይ ደግሞ በዚህ ዐመት በትምህርታችን ስኬታማ ሆነን አንተን ሀገራችንን ቤተሰቦቻችንን በኩራት የምናስጠራ ልጆችህ አድርገን አሜን!!" እንልና የልጅ ነገር ሆኖብን ተመልሰን ወደ ቤት ሄደን ድጋሚ ደሞ ለፕሮግራሙ እንመጣ ነበር። ዛሬ ያ ሁሉ ቀርቶ ዐላማችን ስኬታችን ሁሉ ተረስቶ መቃም ማጨስ መጠጣት ለእኛ normal ነገር ከሆነ ሰነባብቷል ሶሲ የተፈተነችው የማጠቃለያ ፈተና ውጤት መጥቶ በከፍተኛ ነጥብ ከትምህርት ቤታችን አንደኛ ሆና አለፈች እኛ ደግም ከነመፈጠር የዘነጋነውን ትምህርት የ12 ክፍል ተማሪዎች ሆነን ዛሬ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እየተጣደፍን ነው. .
. . . .ይቀጥላል. . .
ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ነው
ቻናሉን ይቀላቀሉ
➥ @CHRIST_TUBE
➥ @CHRIST_TUBE
ሼር በማድረግ ለሌሎች ያድርሱ!