2022-04-25 19:24:55
ፍቅራችንን በልጦት ፣ ምድር ትርምሱ፣
ተስፋችንን ውጦት ፣ መለያየት ምሱ፣
እንደወጣን ቀረን፤
መ፟ለየት በረደን፤
ተፈጥሮ ሳይሞቀን፣
ሳንተያይ መሸ ፤ ሳንተያይ ነጋ ፤ በመተያያ ቀን።
አንቺ ከአስመራ ፤ ናፍቆትሽ ተኩሎ፤
እኔ ካ'ዲሳባ ፤ ያውም ካራት ኪሎ።
በተቃጠርንበት ፣ በዚያች ምጽዓት 'ለት፣
አጊኝቼ ልስምሽ ፣ የተሳልኩት ስለት፣
አልሠመረም መሰል…
ከቤቴ እንደወጣኊ ፣ ከቤት እንደወጣሽ፣
ምን ጋር ስ'ደርሺ ነው ፣ ተፈጥሮ የቀጣሽ?
እኔ…
በስልክ ካወራነው
ከነገርኩሽ ቦታ ፣ ኾኔ እየጠበኩኝ፣
አሻግሬ ባይሽ
ከወዲያ ወደዚኽ ፣ ድንበር ነው ተባልኩኝ።
አትመጪም ማለት ነው?
ድንበር ነው ምንድነው?
ድንበር ማለት ማነው? ወደኔ ያስቀረሽ?
ድንበር የሚባለው…
የድሮ ባልሽ ነው ፤ ያልነገርሺኝ ፈርተሸ።
እኔ…
እየጠበኩሽ ነው፤
በጎረምሳ ልቤ ፤ ባረጀው አቋሜ፤
ዘመናት ቢነጉዱም
ሌላ ቀን አልቆጥርም ፤ ቀጠሮሽ ላይ ቆሜ።
ነይልኝ የኔ ቀን ፤ ነይ የኔ ጨረቃ፤
ፍቅሬ ገና ልጅ ነው ፤ ዕድሜዬ እያበቃ።
ከጊዜ በኋላ ፣ ድንገት የኾነ ቀን
ከዚኽ ቦታ መጥተሸ፣የሌለኹኝ መስሎሽ ፣ ከቶ አታቀርቅሪ፤
በስልክ ያልኩሽ የለም ፤ አርጅቼ ይኾናል ፤ ምልክት ቀይሪ።
አለኹኝ ቆሜያለኊ ፤ በቀጠሮ ነፍሴ፣
ያኔ ስንቀጣር ፣ ስወጣ የነገርኩሽ ፣ ተቀይሯል ልብሴ፤
በይ አድፏል በወዜ፤
ተቀዷል በጊዜ፤
ተቦጫጭቆ አልቋል፤
ተቆራርጦ ወድቋል፤
የቀጠርሽኝ ዕለት ፣ የለበስኩት ጫማ
ከእግሬ ላይ ደርቋል ፤ ቀልጦ እንደሻማ።
ጣቴ ተጠባብቆ፤
ተረከዜ ደቆ፤
አይመጣም ፤ አይሄድም ፤ አልመጣም ፤ አልሄድም፤
ልብ እግር አይደለም አይሰነጠቅም።
የቀጠርሽኝ ዕለት ፣ ጺሜን ባነሣውም ፣ ለዚያ ዘመን ውበት፣
አድጎ ይበጠራል ፤ ቀለሙን ቀይሮ ፣ ተውጧል በሽበት።
የቀጠርሽኝ ዕለት…
ይዤ የወጣሁት ፣ አበባውም ደርቋል፤
ዘመን ተለውጦ ፣ ሌላ አበባ ፈክቷል፤
ምልክት እንዲኾን…
በስልክ የነገርኩሽ ፣ አበባ ይዣለኊ፤
ደርቆ ረግፎብኛል ፤ ባዶ እጄን ግን አለኊ፤
ባዶ እጄን ግን አለኊ ፤ ከነሙሉ ልቤ ፣ በርታልኝ እያልኩት፤
አልጸድቅ ያለኝን ፣ ቀጠሮ መውደዴን ፣ ተስፋ እያጠጣሁት፤
አለኹ ከዚኽ ቦታ ፤ እንደ ተራ ጥሬ፤
ከቅዱስ ቃል እኩል ፣ ቃልሽን ቆጥሬ።
ዕድሜዬን ገብርኩኝ ፤ ለሌላ ሴት ላልኾን፤
ከመቀመጥ ብዛት ፣ ላላፊው ላግዳሚው ፣ ምልክት እስክኾን።
ከጊዜ በኋላ ፣ ድንገት የኾነ ቀን…
ከዚኽ ቦታ መጥተሸ ፣ የሌለኹኝ መስሎሽ ፣ ከቶ አታቀርቅሪ፤
በስልክ ያልኩሽ የለም ፤ አርጅቼ ይኾናል ምልክት ቀይሪ።
ያልኩሽን በሙሉ ፣ ፀሐይና ውርጩ ሲፈራረቁበት፣
በመሸው ዕድሜ ላይ ፣ ቀን እየመሸበት።
ወዴትም ባልሸሽም ፣ ከዕድሜ ለመ፟ደበቅ፣
እንዳትደነግጪ!
አካሌ በሙሉ ፣ ደክሟል በመጠበቅ።
ተጣጥፏል ቆዳዬ፤
አይወርድም ዕንባዬ፤
ከንፈሬ አርጅቷል ፤ ላንቺ ለምውድሽ እንደተቀመጠ፤
አፌ ዳቦ ረስቷል ፤ ተስፋ እያላመጠ።
እኖራለኊ ላንቺ ፤ ኹሉን ተቀብዬ፤
ፈገግ እላለሁኝ ፤ ተፈጥሮ ነው ብዬ፤
ብዙ አላዳምጥም ፤ የመኪና ታምቡር፤
ጆሮዬ ደክሞብኝ
ለራሴ እዘፍናለኊ ፤ የሀገሬን መዝሙር።
ደምሥሮቼ ኹሉ
ቀን እየተመኙ ፣ ቀን የተነጠቁ፣
ነይልኝ ይመስላል!
በከንፈሬ መሐል ፣ የሞላው ሥንጥቁ።
የቀጠርሽኝ ዕለት…
የነገርኩሽ ጸጉሩ ፣ በዕድሜ ተሟሽቶ፣
ገፍቼው ይመስላል ፣ ወደኋላ ሸሽቶ።
ባረጀው አካሌ ፣ ከሐዘን እንዳለኊ
አርጅቼልሽ የለ ፣ ጺም መንካት ወዳለኊ።
የቀጠርሽኝ ዕለት…
ስሜ ስም ብቻ ነው ፤ ያኔ ስናፍቅሽ፤
ጋሼ ተጨምሯል ፤ አንቺን ስጠብቅሽ።
አንቱ ተባልኩልሽ ፤ ሠርክ ሳብሰለስል፤
የቀጠረኝ ድምጽሽ ፣ ሒድ ይለኝ ይመስል።
የቀጠርሽኝ ዕለት…
ያረኩት ቀለበት
ጠቦኝ ፣ ጠቦኝ ፣ ጠቦኝ ፣ ጣቴን አሳመመው፤
መቼ ትመጫለሽ? እስከዛ ላስታመው።
ከየትም የሚጮህ ፣ያ ሰላላ ድምጼ ፣ ከጭስ እንደዋለ፣
አርጅቼልሽ የለ!
አኹን ስተነፍስ ፣ በቃላቴ መሐል ፣ የኾነ ሳል አለ።
የቀጠርሽኝ ዕለት ፣ የነበርኩት ኹሉ ፣ ያደረኩት ኹሉ፣
ደብዛው እንኳን የለም፤ የነበረው ውሉ።
አለኹኝ ከቦታው ፤ አለኹ ከሰዓቱ፤
ቆጥረሽ አስረጂልኝ ፤
ስንት ቀን ኾኖኛል ከመጣሁኝ እቱ?
መቁጠር እኮ አልችልም!
ምልክቱ ኹሉ ዛሬ ተቀይሮ
በእርጅና በድካም ፣ ዙሪያ ተከብቤ፣
ዐይኔ እንደፈዘዘ ፣
ምልክት ይኹንሽ ፣ ተንቀልቃዩ ልቤ።
ከቶ አይቀርምና ፣ ላንቺም ማጎንበሱ
በቀጠሮ ቦታ ፣ የወደቀ ካየሽ ፣ ተጣሪ በስሱ።
እኔ ነኝ!
ባልሰማሽም እንኳን ፣
የሌለኹኝ መስሎሽ ፣ በዕንባ እንዳታመሪ፤
የኔ ውብ ፣ የኔ ዓለም ፤
አርጅቼ ይኾናል ፤ ምልክት ቀይሪ።
በነፋስ ቢበተን ፣ ሐሳቤ ፣ ሐሳብሽ፣
በድንበር ቢበትን ፣ ናፍቆቴ ፣ ናፍቆትሽ፣
የኔ ሰዓት ቆሟል ፤ ስንት ይላል ሰዓትሽ።
መቁጠር እኮ አልችልም!
ገጣሚ ኤልያስ ሽታሁን
"ዋነኛ አላማችን ጀማሪ የጥበብ ባለተሰጦዎችን ማበረታታት ነው"
━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━
ሼር ያድርጉ
⇨ @CareArtsss ⇨ @CareArtsss
⇨ @CareArtsss ⇨ @CareArtsss
⇨ @CareArtsss ⇨ @CareArtsss
━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━
255 views16:24