Get Mystery Box with random crypto!

#የኩሽ #ዘር #ነህ #ወይስ #የሴም? ሰው መጣላት ሲፈልግ የውሸት መለያያ ይፈጥራል። የሴምና የካም | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

#የኩሽ #ዘር #ነህ #ወይስ #የሴም?
ሰው መጣላት ሲፈልግ የውሸት መለያያ ይፈጥራል። የሴምና የካም በማለት ለማለያየት ይሞክራል። ድንቁርና ሰልጥኖብንና ጠበን ነው እንጂኮ ከፍ ብንል የሴምና የካም አባታቸው ኖኅ ነው። የኖኅ ልጆች ነን ብለን ብናስብ የጠራ እውነት ነው። ምክንያቱም አሁን በዓለም ያለ ሰው ሁሉ የኖኅ ልጅ ስለሆነ። የካም ነኝ የሴም ነኝ የሚለው አነጋገር ግን የነሲብ የግምት አነጋገር ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመለከት የሚከተሉትን ጉዳዮች ያነሣል።

"የኩሽ ዘር በእስር ደቡብ ከዚያም ወደ አፍሪካ ተሻግረው ተራብተው በርክተው ከዛሬው ሱዳን ጀምሮ እስከ ኤርትራ ባሕር ያለውን ሀገር ይዘውት ይኖሩ ነበር። በኋላ ዘመን ደግሞ የሴም ዘሮች ነገደ ሳባና ነገደ ዮቅጣን ከደቡብ አረብ የኤርትራን ባሕር እየተሻገሩ ከካም ዘር ጋር ተደባልቀው በመጻተኝነት ቆዩ። ረኀብ በተነሳ ጊዜም አንደኛው ነገድ ተሰዶ ወደ አንደኛው ነገድ ሄዶ ይደባለቃል" [ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ናፓታ መርዌ]። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ ሴማውያንና ካማውያን ተደባልቀው የሚኖሩባት ሀገር ናት። አረቦች ሐበሻ ይሉናል። ድብልቅ ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጠው ዘፍ. 10፣6 ኖኅ ካምን፣ ካም ኩሽን ይወልዳል። ኩሽ ራጌምን ይወልዳል። ራጌም ሳባን ይወልዳል። ኢትዮጲስ የኩሽ ሁለተኛ ስሙ ነው። በእርሱ ሀገሪቱ ኢትዮጵያ፣ የኩሽ ምድር ተብላለች። ከዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል 10፣21 ከሴም ዘር ዮቅጣን ይወለዳል። ዮቅጣን ሳባን ይወልዳል። ከሴምም ከካምም ሳባ ሳባ የሚባሉ እንደነበሩ አስተውል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የካምና የሴም ድብልቅ ነው። "የሴም የልጅ ልጆች የመንን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው ሳባ በትግሬ፣ አባል በአዳል (አፋር?)፣ ኦፌር በውጋዴን (ሶማልያ) ተቀመጡ። የቀድሞው የኢትዮጵያ ግዛት የአሁኑን ሱዳን ያካተተ ነበር። ኑብያ የሚባለው የዛሬው ሱዳን ነው" [ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ናፓታ መርዌ]።

"ካም ኩሽን ይወልዳል። ኩሽ ሳባንና አቢስን ይወልዳል። ኢትዮጵያ በአቢስ አቢሲኒያ ተብላለች። ሳባ የትግሬዎች አቢስ የአማሮች ሀገር ነው። በኋላ የአቢስ ክፍል አምሐራ ተብሏል። አምሐራ ማለት ነጻ ሕዝብ ጨዋ የጨዋ ልጅ ማለት ነው" ይላሉ [አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍል፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ]። አማራን፣ አፋርን፣ ሶማልያን፣ ትግራይን የሴም ዘሮች አድርገው ሌላውን የኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ የካም ዘር ነው ብለው የሚሉ ጸሐፍያን አሉ። ነገር ግን አሁን ላይ ይህ የካም ይህ የሴም ነው ለማለት የሚያበቃ በቂ ማስረጃ የለም። ምክንያቱም ሁሉም የታሪክ ጸሐፍያን የሴም ዘሮችም ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ጽፈዋል። የካም ዘሮችም ወደኢትዮጵያ እንደመጡ ጽፈዋል። ያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደበላልቋል። ለምሳሌ በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በኦሮሞ እንቅስቃሴ (Oromo Movement)፣ በተለያዩ ክፍለ ዘመናት በነበሩ ጦርነቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደበላልቋል። ይህ ምሳሌ ነው እንጂ ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አውሮፓውያንም በተለያየ ምክንያት ኢትዮጵያ ገብተው እንደኖሩም ታሪክን እናያለን። ስለዚህ ያፌታውያን ድብልቅም ሊኖሩ ይችላሉ።

በአመክንዮ ደረጃ አንድ ሰው የካም ዘር ነኝ ለማለት በእናቱም በአባቱም እስከመጨረሻው እስከ ካም ቆጥሮ ማቅረብ አለበት። የሴም ዘር ነኝ ለማለትም እንዲሁ። ብዙ ሰው ጠይቄያለሁ ከአሥርኛ ትውልድ በላይ ቅድመ አያቶቹን ስማቸውን ሳይቀር አያውቀውም። ይህ ከሆነ 11ኛው የአያት ትውልድ ከአውሮፓ መጥቶ ኢትዮጵያ ኗሪ ሆኖ ወልዶህስ ቢሆን?! 11ኛው አያት የሴም ይሁን የካም ምን ማስረጃ አለህ!? ከፍ ብለህ 20ኛ 30ኛው አያትህስ ማን እንደነበር ታውቃለህ? ይህ በማይታወቅበት ሁኔታ እኔ የካም ነኝ እኔ የሴም ነኝ ብሎ ብጥብጥ ማንሳት ድንቁርና ነው።

አንድ እውነታ ግን አለ። ኢትዮጵያ አሁን ላለነው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀገራችን ናት። እንዲህ ከሆነ በአንዲት ሀገራችን በአንድነት በእኩልነት እንዴት መኖር እንዳለብን ብንነጋገር መፍትሔው ቅርብ ይሆናል። ከዚያ ውጭ በ1984 በተፈጠረ የብሔር ማንነት አንዱን ለመጥቀም ሌላውን እየጎዱ መኖር እየቆየ ትልቅ ጉዳትን ያመጣል። እያንዳንዱ ሕዝብ በፍቅር በእኩልነት የሚኖርባት ሀገር ማድረግ ከመሪዎችም ከሕዝቡም ይጠበቃል። ሕዝብን በሕግ ማስከበር ስም ቤቱን እያፈረሱ ሜዳ ላይ የጣሉ መሪዎችን ከመሪነታቸው አንስቶ ሕዝብን በሚያከብሩ መሪዎችን መተካት ያስፈልጋል።

በትረማርያም አበባው