Get Mystery Box with random crypto!

_በትእግስት ያንብቡ_ ኢየሱስ ማን ነው ክፍል ፩? Who is Jesus part 1? ሙስ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_በትእግስት ያንብቡ_
ኢየሱስ ማን ነው ክፍል ፩?
Who is Jesus part 1?
ሙስሊሞችም፣ ፕሮቴስታንቶችም፣ ካቶሊኮችም ካላችሁ በነጻነት እስከመጨረሻው መወያየት እንችላለን ኑ።
+
ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረ በኋላም ዓለምን ለማዳን ሥጋ ሰብእን የተዋሐደ አምላክ ነው። ሮሜ ፱፣፭ "ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ የዘላለም ቡሩክ አምላክ ነው" እንዲል። ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ከመፈጠሯ በፊት ነበረ ስንል ግን በቃል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ዮሐ. ፩፣፩ "በመጀመሪያ ቃል ነበር፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፣ ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም" ። መሐመዳውያን ፈጣሪ በአካል አንድ ነው ቃሉ የዚያው የአንዱ ስለሆነ ልክ እንደሰው ነው ለምሳሌ እኛ አንድ ሰው ነን። ነገር ግን ቃል አለን። ቃል ስላለን ብለን ግን በአካል ሁለት ነን አንልም ይላሉ። ነገር ግን ሰውና ፈጣሪ በባሕርይ የተለዩ ስለሆኑ የእግዚአብሔር ቃል እንደሰው ቃል ስላልሆነ ቃሉን የአካሉ ዝርው ንባብ አድርገን መውሰድ አንችልም። ምክንያቱም ለምሳሌ የእኛን የሰዎችን ቃል ብንመለከት እኛ ሰው ነን። ቃላችን ግን የሰው እንጂ ሰው አይደለም። በመሆኑም ቃላችን ሌላ አካል እኛ ሌላ አካል ተብለን ሁለት አንባልም። አንድ አካል እንባላለን እንጂ። የእግዚአብሔር ግን ከዚህ የተለየ ነው። ምክንያቱም በመጀመሪያ ቃል ነበር ካለ በኋላ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር ካለ በኋላ ቃል ራሱ እግዚአብሔር ነው ይላል። እኛ ሰው ነን። ቃላችን ግን ሰው አይደለም። ስለ እግዚአብሔር ስንናገር ግን አብ እግዚአብሔር ነው ቃሉም እግዚአብሔር ነው። በዚህ ቃል መሐመዳውያን ይረታሉ። ሌላው ኢየሱስ ክርስቶስን ነቢይ ነው። ፍጡር ብቻ ነው ይሉታል። ነገር ግን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐ. ፰፣፶፰ "አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ" ብሏል። በሌላ ቦታ ደግሞ በማቴ. ፩፣፩ "የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ" ብሎ በመናገር ኢየሱስ ክርስቶስ የአብርሃም ልጅ መሆኑን ተናገረ። ሁለቱም ልክ ነው። በቃል ከአብርሃም በፊት የነበረ የአብርሃም ፈጣሪ በሥጋ ከአብርሃም ዘር ተወለደ ስለዚህም የአብርሃም ልጅ ተባለ። ጥያቄ ለመሐመዳውያን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰው ብቻ ነው ፈጣሪ አይደለም ካላችሁ ከአባቱ በፊት የነበረ ልጅ አለ ወይ?። የለም በፍጡራን ዘንድ ከአባቱ ቀድሞ የነበረ ልጅ የለም። የዘካርያስ ልጅ መጥምቁ ዮሐንስ በሥጋ በመወለድ ከክርስቶስ ይቀድማል። ሉቃ. ፩፣፭-፹ ይመልከቱ። ነገር ግን ዮሐንስ ስለጌታ ሲናገር ዮሐ. ፩፣፳፮ "እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ ነገር ግን እናንተ የምታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት የነበረው" ብሎታል። ይህም በቃል ይቀድመዋል። ድንግል ማርያም የወለደችው ዮሐ. ፩፣፫ ላይ ሁሉ በእርሱ ሆነ የተባለውን እሷን የፈጠራትን ወልድን ነው። አፈ በረከት ኤፍሬም በሃይ. አበ. ፵፯፣፪ "ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው እርሱም እናቱን ፈጠረ" ይላል። አስቀድሞ "ቃል" የተባለውና ሰማይና ምድርን አጠቃላይ ፍጥረታትን የፈጠረው እርሱ አዳም በተሳሳተ ጊዜ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሀለሁ ብሎት ነበርና ሰውን ለማዳን ረቂቅ ኃያል በሁሉ ቦታ ያለ አምላክ በሁሉ ቦታ መኖሩን ሳይለቅ በድንግል ማኅፀን ተወሰነ፣ ረቂቁ እና የማይታየው የማይዳሰሰው አምላክ አለመዳሰስን ርቀትን እንደያዘ መዳሰስን ግዘፍን ገንዘብ አደረገ። ኃያሉ አምላክ ኃያልነቱን ሳይለቅ ድኩም ሥጋን ተዋሐደ። መዝ. 101፣27 አንተ ግን ያው አንተ ነህ ስለተባለ እግዚአብሔር መለዋወጥ የለበትምና። ለእኛ ያለውን ፍቅር ለእኛ ለማሳየት እኛ ባጠፋን እርሱ ስለእኛ ተሰቀለ። በኪሩቤል ጀርባ እንዳለ በተዋሐደው ሥጋ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ታየ። አዳም እፀ በለስን ከበላ የሞት ሞት እንደሚፈረድበት ዘፍ. ፪፣፲፯ "ከእርሱ (እፀበለስ) በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ" ብሎታል። አዳም ግን ትእዛዙን ተላልፎ ዘፍ. ፫፣፮ ላይ እንደተጻፈው በላ። ስለዚህ አዳም ሞተ ነፍስ አገኘው ከእግዚአብሔር ተለየ። ስለዚህ እንዴት አዳነው ስንል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሀለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባለት።ገላ. ፬፣፬ "ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ" ይላል። ስለዚህ አዳምን ለማዳን እግዚአብሔርነቱን ሳይለቅ ሰው ሆኖ ተወለደ። ሳይሰቀል ማዳን አይችልም ወይ ከተባለ ይችላል። ታድያ ለምን ተሰቀለ ከተባለ እኛ ልንከፍለው የሚገባንን እዳ እርሱ ከፍሎ ሲያድነን ለእርሱ ያለን ፍቅር ይጸና ዘንድ ነው። እንዲሁ ሳይሰቀል ኃጢአታችንን ይቅር አይለንም ነበር ወይ ከተባለ ደግሞ እግዚአብሔር በእውነት ፈራጅ ነው። መዝ. 50፣6 "እግዚአብሔር ፈራጅ ነው" እንዲል። አዳም ላጠፋው ጥፋት ፍርዱ ሞት ነው። እግዚአብሔር መሓሪም ስለሆነ የአዳምን እዳ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከፈለለት።
+
ታድያ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? ሰው ብቻ ነውን ቢሉ መልሳችን አምላክም ሰውም የሆነ ነው ነው እንላለን።

ክፍል ፪ ይቀጥላል።