Get Mystery Box with random crypto!

እግዚአብሔር ሰዎችን ኹሉ ሲፈጥራቸው በመንፈሳዊ ማንነታቸው እኩል አድርጎ ነው፡፡ እንዲህም ስለ ኾነ | ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

እግዚአብሔር ሰዎችን ኹሉ ሲፈጥራቸው በመንፈሳዊ ማንነታቸው እኩል አድርጎ ነው፡፡ እንዲህም ስለ ኾነ እያንዳንዱ ሰው በጎም ኾነ ክፉ ግብር ለመሥራት እኩል ዝንባሌ አለው፡፡ እግዚአብሔርን ለመታዘዝም ኾነ ላለመታዘዝ እኩል የመምረጥ ዕድል አለው፡፡ ከዚህ ውጪ በኾነ ነገር ግን ሰው ኹሉ እኩል አይደለም፡፡ አንዳንዱ እጅግ አስተዋይ ነው፤ ሌላው ደግሞ ደከም ያለ ነው፡፡ አንዳንዱ በሰውነቱ ብርቱና ጤናማ ነው፤ ሌላው ደግሞ ደካማና ሕመም የሚበዛበት ነው፡፡ አንዳንዱ ሰው መልከ መልካምና ማራኪ ነው፤ ሌላው ደግሞ አይደለም፡፡

ይህ ኹሉ ቢኾንም ግን በኾነ ነገር ስጦታው ያለው ሰው ስጦታው የሌለውን ሌላውን ሰው ሊንቀው አይገባም፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ለእያንዳንዳችን የተለያየ ስጦታን የሰጠን አንዳችን አንዳችንን እንድንጠቅም ነውና፡፡ እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ከሌላው ወንድማችን የምንፈልገው ጥቅም እንዲኖር ያደረገው በመካከላችን መጠላላትና መለያየት እንዳይኖር ነው፤ እንድንፋቀርና አንድ እንድንኾን አስቦ ነውና፡፡

ስለዚህ ወዳጄ ሆይ! ወንድምህ ከአንተ ይልቅ አስተዋይና ዐዋቂ፥ ብርቱም ቢኾን በዚህ ቅር አይበልህ፡፡ ከዚህ ይልቅ እግዚአብሔርን አመስግን፤ ከወንድምህ አስተዋይነትና ዐዋቂነት ብርታትም ትጠቀማለህና፡፡ በዚህ ብቻ ሳታቆምም ራስህን፡- “ስጦታዬ ምንድን ነው? ወንድሜን እኅቴን በምን ልጠቅም እችላለሁ?” ብለህ ጠይቅ፡፡ ይህን ጥያቄ በትክክል ስትመልስ፥ እንደ መለስከው ምላሽም ስትተገብር በአንድ መልኩ በሚበልጥህ ሰው ቅር መሰኘትህን፥ በሌላ መልኩ ደግሞ የምትበልጠውን ሌላውን ወንድምህን መናቅህን ታቆማለህ፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ