Get Mystery Box with random crypto!

+ በጾመ ፍልሰታ እንፍለስ + እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ አስቀድ | በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪

+ በጾመ ፍልሰታ እንፍለስ +

እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ አስቀድሞ ጤናውና ሰላሙ ይኑራችሁ፡፡ ስለርሱም ዘወትር አመስግኑ፡፡ ሌላው ሁሉ በጊዜው ይደርሳል፡፡

ፍልሰታ በጥሬ ቃል ፍቺው መፍለስ ከሚለው ግስ የተነሣ ሲሆን፤ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ መዛወር፣ መንቀሳቀስ፣ መጓዝ የሚለውን ትርጉም ይይዛል፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና እርገት ጋር የቃልኪዳን ትስስር ያለው ልዩ ጾም ነው፡፡

ጾመ ፍልሰታ በዐሥራ ስድስት ቀናት ውስጥ ተጀምሮ የሚያልቅ ቆይታ ሲኖረው ይኸውም መግቢያ ቀንና መውጪያ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ይሆናል፡፡ አንድ ሱባዔ ሰባት ቀን ሲሆን፤ ሁለት ከሆነ ዐሥራ አራት ቀን ይሆናል፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያው መነሻና መፈጸሚያ መድረሻ ቀናት የጾሙ መግቢያና መውጪያ ጊዜያት ይሆናሉ፡፡ ጾሙ ደቀመዛሙርቱ እንደያዙት ሱባዔ፤ ሰማያዊ መልስ፣ የመንፈሳዊ ሚስጢር መገለጥና የበረከት ስጦታ የምናገኝበት ጾም ነው፡፡ ሐዋሪያቱ ሰማያዊ መልስ ጠይቀው አግኝተውበታል፡፡ ሚስጢር የሆነባቸውን ጉዳይ በመንፈሳዊ መገለጥ ፈትተዋል፡፡ በመጨረሻው ስለ እመቤታችን ትንሣኤ የበረከት ምልክት የሚሆነውን ሰበን ሐዋሪያው ቶማስ ተቀብሎአል፡፡

እኛም መልስ ያጣንለት ጥያቄ ይኖረናል፡፡ ሚስጢር ሆኖ አልገለጥ ያለን ጉዳይ ይኖረናል፡፡ የበረከት ማነቆ በሰላቢ መናፍስት፣ በቡዳ መናፍስት፣ በመተት መናፍስት ምክንያት ደርሶብን፤ የልፋታችንን ከንቱነት እያሰብን የምንገኝ እንኖራለን፡፡ በጾመ ፍልሰታ ታዲያ፤ ከነፍስ፣ ከልብና ከአሳብ በተሰበሰበ አንድ የፍቅር ምዕራፍ ከፈለስን፤ ብዙ ቦታ ላይ አልገጥም ብሎ ያሰቃየን ጉዳይ ቅርጹን ይይዛል፡፡

ጾመ ፍልሰታን እንዴት እናሳልፍ ?

፩. በፍቅር

የመንፈሳዊ ሕይወት ግንባታ መሠረት "ፍቅር" ነው፡፡ ሃያ ዐራቱን ሰዓት ሁሉ ብንጾም፣ ከደመና በላይ ጮኸን ብንጸልይ፣ አጥንታችን እስኪሰበር ብዙ ብንሰገድ፣ ኃይል ከሰማይ እንደዝናብ ቢወርድ፣ የቱንም ያህል ደረጃ ነገሩ ቢሳካ፤ ሕይወታችን ፍቅር ከሌለበት ሁሉ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ነው (ይሄ፥ ጥሬ አባባል የሚመስለው፥ ለብዙ ሰው ነው)፡፡ (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፥2) ፍቅር የሌለው መንፈሳዊነት ወግ ይሆናል፡፡ ዘልማድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ፍቅር ሲኖረው መንፈሳዊነቱ ላይ ጠንካራ እምነት ይገኝለታል፡፡ በጣም ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡ ወድደን የምናደርገው እና ተገደን አሊያ ማድረግ አለብን ብለን አስበን የምንከውነው ጉዳይ መካከል የራሱ የሆነ ርቀት አለ፡፡ ዐሥራ ስድስቱ ቀናት እየጣፈጡህ ማለቃቸውን እንኳ ሳታስተውል እንድትፈልስባቸው፤ መጀመሪያ ቀን አንድ ስትል፥ ከፍቅር ጀምር፡፡ እውን የእመቤታችን ፍቅር ነፍስህን ይዞት፤ ትንሣኤዋ ልብህ ላይ ተቀምጦ፤ የሐዋሪያቱ ሱባዔ አሳብህ ውስጥ ሆኖ ክብሩን ባነገሠ ምግባረ ክርስትና መሄድ ስትጀምር፤ ቀኖቹ እንዲያልቁ ሳይሆን እንዳያልቁ በስስት እያየህ እያንዳንዷን ቀነ ደቂቃ እየነጠልክ ትጾማቸዋለህ፡፡

፪. በአምልኮትና በጸጋ ስግደት

ስግደት ጸሎት ማጽደቂያና ማሰሪያ ነው፡፡ መሥዋዕት የማቅረቢያ አንድ መንገድ ነው፡፡ የመገዛትና የማክበር መግለጫ ነው፡፡ እነሆስ፥ "ተወዳጂቱ ቤዛዊት ዓለም ሆይ፥ ቢመጣም ባይመጣም፣ ቢሠራም ባይሠራም፣ ቢከናወንልን ባይከናወንልም፣ ቢደርስም ባይደርስም በእውነትም እንወድሻለን!" የምንለው በጸጋ ስግደት በኩል ነው፡፡ የሚሰግድ ሰው የፍቅሩ ኃይል ላይ ማኅተም አለው፡፡ ማረጋገጫ አለው፡፡ ዋጋ ስለመስጠቱ መታያ ነው፡፡ እንኪያስ፥ የእመቤታችንን ስግደት በጾመ ፍልሰታ ከዘወትሩ ስግደት ጋር አስተባብራችሁ በደንብ ስገዱ፡፡

፫. በጸሎት

ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን ወደ አፀደ ሕይወት መፍለስ እያሰብን የምንጾመው ከሆነ ዘንዳ፤ እንግዲያው እኛም በመንፈሳዊ ጉዞ በኩል ወደላይ መፍለስ አለብን፡፡ መጨመር አለብን፡፡ የአምልኮት ልምምድ፤ ጊዜ፣ ብዛትና አቅም መጨመር አለብን፡፡ ሁለቴ የምትጸልየው ሦስቴ፥ ሦስቴም ከሆነ አራቴ፥ አራቴም ከሆነ አምስቴ ለማድረግ እንጀግን፡፡ በሥጋ ላይ ያለን ከፍታ ለማምጣት ዓለም ሁሉ ይሮጣል፡፡ የነፍስ ብልጽግና ግን ለተመረጡት ነው፡፡ ድምፁን ለሚሰሙት .. ለበጎቹ! (ውዳሴ ማርያምን ጸሎት በገባችሁ ልክ ብትጸልዩ ጥሩ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ቀን 6:00 መልክአ ሚካኤል ሲነበብ፤ አስቀድማችሁ ውዳሴ ማርያምን በመቀጠል የመልአኩን መልክአ መጸለይ፡፡ በሥራና ሌሎች ጉዳዮች የተወጠራችሁ ሰዎች እስከምትችሉት ያህል ጸልዩ፡፡ ከፍቅር መሠረት ላይ መነሣት የሚገባን ለዚሀ ነው፡፡ ፍቅሩ ካለ እስከ የትኛው አቅም ልክ እየሄድን መበርታት እንዳለብን ማንም ሳይጠቁመን እናውቀዋለን)

፬. ክፉውን በመዋጋት

ጥሩ ንቃተ ሕሊና የታደለ ሰው መናፍስት ብርታት የሚሆኑ የጽድቅ ጠላቶች እንደሆኑ ያውቃል፡፡ በተለያየ መንገድ ፈተና ውስጥ የሚከቱን አጥፊ ኃይሎች ባይኖሩ ኖሮ ማን ያበረታናል? .. አባቶቻችን መከራ ሲርቃቸው ተጨንቀው ያለቅሱ ነበረ፤ እግዚአብሔር የተዋቸው እየመሰላቸው፡፡ በአንክሮ ስንገንዘብ፤ ያለ ፈተናና ትግል ክርስትና ውስጥ መንፈሳዊነት ለካ አይበረታም፡፡ የተዘጋብንን ለማስከፈት በሰገድን፣ በጸለይን፣ በመቁጠሪያ በተዋጋን ቁጥር ወደ አርያም ሰማይ ምን ያህል እየፈለስን እንደሆነ ብዙዎቻችን አይገባንም (ችግር ችግሩን ስለምንቆጥር)፡፡ እስኪ ከትናንት ዛሬ የመጣንበትን በደንብ እናጢነው፡፡ ስግደት አናውቅም ነበረ አሁን እንዴት ሆነናል? ጸሎት በርትተን አንጸለይም ነበር አሁን ከምን ደርሰናል? .. መናፍስቱን በተዋጋንበት ልክ፤ የኛም መንፈሳዊ ለውጥ በዛው ልክ ከፍ ይላል፡፡

በሉ ስለዚህ በጾመ ፍልሰታ መናፍስቱ ላይ መለኮታዊ ማዕበል አውርዱ፤ ዝመቱ፤ በደንብም አድክሟቸው፡፡ በነገራችን የፍልሰታ ጊዜ የሱባዔ መልክ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ሱባዔ ደግሞ ብቸኝነት ይፈልጋል፡፡ አርምሞ ይወዳል፡፡ ከሥጋ ወከባና መዝናኛ መለየት ደስ ይለዋል፡፡ ስለዚህ .. የነፍስ ቆይታ ላይ ትኩረት እንስጥ፡፡ ከለመድናቸው የሥጋ ጉዳዮች ሸሸት እንበል፡፡ ዘፈን ከመዝሙር አናምታታ፤ ጸሎትን ከቂም አንቀላቅል፤ ዓለማዊን ከመንፈሳዊ አናወሳስብ፡፡ ምክንያቱም ተወዳጁ.. እንኳን በሰላሙ ሰዓት .. በመሰቀል ጭንቅ ሳለም .. ቀላቅለው የሰጡትን መጠጥ ሊጠጣው በፍጹም አልወደደም!

፭. በመቀደስ

ጾመ ፍልሰታ ጊዜ ውስጥ የሁለት ሳምንታት ቅዳሴዎች አሉ፡፡ በመሆኑ የምንችል ሰዎች ስናስቀደስ፤ በዛውም መቀ'ደስን እንወቅ፡፡ ንስሐ ገብታችሁ ያለ ቅዱስ ቁርባን ቁጭ ያላችሁ ወገኖቼ መቼ ልትቆርቡ ነው? ምን እየጠበቃችሁ ነው? ምንድነው'ስ አላስቆርብ ያላችሁ? ..

በነዚህ የፍልሰታ ሳምንታት መቁረብ እጅግ ታላቅ ጥቅም አለው፡፡ ምክንያት ካልን፤ አንደኛ ጾሙ በራሱ የሱባዔ መልክ እንዳለው ተነጋግረናል፡፡ ሱባዔና ቅዱስ ቁርባን ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚሄዱ ባልንጀሮች ናቸው፡፡ ሁለተኛ፤ ፍልሰታ የቃልኪዳን በረከት ያለው ጾም ነው፡፡ ይሄ በረከት ደግሞ ስለመኖሩ ራሱ የሚታወቀን በቅዱስ ቁርባን ስንቀደስ ነው፡፡ ሦስተኛ፤ ጾሙ ውስጥ መንፈሳዊ መገለጥ ታሪካዊ መዝገብ ሆኖ ይገኛል፡፡ የዚህ የመገለጥ ቁልፍ መክፈቻ ደግሞ የመድኃኒቱ ሥጋና ደሞ ነው፡፡ እናሳ? .. እንዴት ነው ምን ወሰናችሁ?