Get Mystery Box with random crypto!

  አንድ በእግዚአብሔር ሕያው አምላክነት በእውኑ አምናለሁ የሚል ግለሰብ፤ ንስሐ በሚባል መንፈሳዊ | በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪

  አንድ በእግዚአብሔር ሕያው አምላክነት በእውኑ አምናለሁ የሚል ግለሰብ፤ ንስሐ በሚባል መንፈሳዊ መንገድ ላይ ለመጓዝ ሲዘጋጅ፤ በኑሮና በዕድሜው ውስጥ ከተፈጸመው የኃጢአት ሥራ ጀርባ መግፍኤ የሆነ ጉልበት ያሳደረ ክፉ መንፈስ እንዳለ ማወቅ ያስፈልገዋል፡፡ ምክንያቱም ንስሐ በመግባት ከሚገኙ መሠረታዊ ሰማያዊ ትሩፋቶች መካከል አንዱና ዋነኛው፤ ኃጢአትን እንደ ምቹ ምሽግ ተጠቅሞ በባሕሪይ የሚደበቀውን ዲያቢሎስ በቀጥታ መቃወምና መጣል ስለሆነ፡፡ ባለ ራእዩ የሚለንን እንመልከት፦

"ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአል።" (የዮሐንስ ራእይ 12፥10)

   አጥፊው መንፈስ ትልቁና መድረሻ ሥራው፣ ዓላማው፣ ራእዩና ፍላጎቱ፤ በጽድቅና በኩነኔ መካከል ባለ የክስ መዝገብ ላይ ኃጢአታችንን አብዝቶ መደርደር ነው፡፡ በእያንዳንዷ ዕለት ላይ (ቀንና ለሊት) ኃጢአትን በኛ ፈቃድና ውሳኔ እንድንሠራ በተለዋዋጭና በዘርፈ ብዙ መናፍስታዊ ስልቶች በየደቂቃው በመፈተን፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚነበብ የበደልን ጽሕፈት በስማችን ይከትባል፡፡

   ይህ በእንዲህ ሳለ፤ እግዚአብሔርን በአፍ አመልካለሁ ብለን በተግባር ስንተወው፤ በአንጻሩ ሰይጣንን በአፍ ከድቻለሁ ብለን በተግባር ኃጢአትን ያለምንም ሥጋትና ቅደመ ሁኔታ በመፈጸም አብረነው ስንኖር፤ "እኔ መንፈስ የለብኝም" እያልን፤ የ'የለብኝም" ድምፃችንን እንደ ጭዳ ቆጥሮ ከማንነታችን ኋላ ይበልጥ ተሰውሮ እንዲገባ እና ራሳችን ቀድመን እንደሰየምንለት "እንደሌለ ሆኖ" የሚያደፍጥበትን ጊዜ እንዲጨምር፤ አቅሙን የምናበልጽግለት ሰዎች ጥቂቶች አይደለንም፡፡

   የመናፍስት ብቸኛ መግለጫና ኃይል የሆነውን ኃጢአት ዘወትር እንደልብ እየሠራን በእግዚአብሔር የጽድቅ ነገራት ላይ ድንዝዝ ብለን ስንቀመጥ፤ "ምንድነው ነገሩ? ለምንድነው በእምነት ሕይወቴ ውስጥ በእውነተኛ ምግባር መመላለስ ያቃተኝ? በእርግጥ የኃጢአት ራስ ከሆነው የዲያብሎስ መንፈስ የጸዳሁ ሰው ብሆን ኖሮ ፥ኑሮዬ ታዲያ ከጥፋት ገጽታዎች ስለምን ጸድቶ አይታይም? በአምላክ ላይ ያለማቋረጥ ዓመፃን እያስነሳሁ የምኖር መሆኔን በሚገባ ሳውቅ፥ የዓመፅ መሠረት የሆነው ክፉው መንፈስ የለብኝም ለማለት እንደምን ይቻለኛል?" ብለን በረጅም ጥሞና ተረጋግተን መመርመር ገና አልጀመርንም፡፡
 
    ዓለማችን በዚህ ዘመን ባለ ዕድሜዋ ኃጢአትን ሥር በሰደደ አኳኋን በብዙ ለምዳና የመኖር አንድ አካል አድርጋ፤ ከትውልዶች ፊተኛ የለውጥ ግስጋሴ ጋር አብሮ ቅርጽና ይዘት እየለወጠ በሚከተል የእርግማን፣ የርኩሰትና የክፋት ገጽታዎች የተሞላች ስትሆን፤ ይኸውና አሁን የጽድቅ እውነት ኃጢአት፥ የኃጢአት ውሸት ደግሞ ጽድቅ ሆኖ ተገላብጦ ቁጭ ብሏል፡፡
 
    አምላካዊ መሥፈርት የሆኑ የቅድስና እውነታዎች ነጻነትን እንደሚገፍፉ የባርነት እስር ቤቶች በአእምሮ ስሌት ተቆጥረው፤ በሥጋ ምቾት ላይ የተለጠፉ ኃጢአቶች የየዕለት ሽርፍራፊ ክስተቶቻችን ሆነው እንዲዛመዱን፤ በእግዚአብሔር የተቀደሱ አምባዎች ላይ መቆም በምድር የሚገባንን የቅንጦት ኑሮ እንዳንኖር የጎታችነት ቀንበር የሚያሳርፍ ተጽዕኖ እንዳለው ክፉ መናፍስቶች በቀላልና ለመቀበል በሚስማማን ጥቁር ጥበብ ካሳመኑን አያሌ ዘመናት አልፎዋል፡፡

    በተለይም በ17ተኛው ክፍለ ዘመን ከተነሳው፥ የኢንዱስትሪ ሥልጣኔን ሽፋን አድርጎ ከተቀጣጠለው የርዕዮት ሽግግር ወዲህ፤ የፉክክር መድረክ እንድትሆን አብዮታዊ ቅርጽ በወጣላት ዓለም ውስጥ አሸናፊ ለመሆን፤ የርኩሰትንና የዓመፃን ግብራት መፈጸም እንደ ተራ የተለምዶ ክብደት እየተዘመነ፤ "ሁሉም ሰው ኃጢአት ይሠራልና እኔም በዚህ ሁሉነት ውስጥ የደርሻዬን ኃጢአት ልውሰድ" በሚል ጋርዮሻዊ አኗኗር ሁላችን እየተመራን፤ የነፍሳችንን ዘላለማዊ ጩኸት አፍነን የሥጋችንን ጊዜያዊ ሹክሹክታ አድምቀን በመስማት ወደ ጨለማው ጠለል በዝግታ አንድ በአንድ ስንወርድ እንገኛለን፡፡

    በእውነት አስቸጋሪው የጥፋት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ኃጢአትን በመልመድ የኖርንበት ጊዜ የመልካምነትን ፍቅርና መሥዋትነት ከጠባያችን ውስጥ ደምስሶ፤ "በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም" ለሚለው የሮሜው ቃል መጽደቂያ ፍጻሜ አስገኝቷል፡፡ ኃጢአትን በመልመድ የቆየንበት ኑሮ የእግዚአብሔር ረድኤት በእጅጉ ርቆበት፤ የማይነዋወጽ ሰላም የምንለው የቅድስና አንድ መልክ "በበረሃ ውስጥ እንደሚፈልቅ ምንጭ" በጣም ውድ ሆኖብን ይገኛል፡፡ ኃጢአትን በመልመድ ያሳለፍንበት ቸልተኛ ዕድሜ በሁላችን ታሪክ ላይ ተመሳሳይ ሆኖ ሲገኝ፤ ቅዱስ መሆን ተአምር እስከሆነበት ጥግ ድረስ ርኩሰት ተላምዶን፤ ስለ ነፍስ መጨረሻ መጨነቅ እያቃተን፤ የደመወዝ ቀን መድረሻው እያስጨነቀን፣ የሥጋ ድሎት መጀመሪያው እያስጨነቀን፤ የውስጥ ሕልውናችን ባላወቅነው ደባል ጠላት በአዚምነት ግርዛዜ መካከል ተሸፍኖ እንዳለ ሳይገባን እንኖራለን፡፡

   ንስሐ፥ በኃጢአት ውስጥ የኃጢአት ኃይል ሆኖ የመሸገው ርኩስ መንፈስ በኛ ሕይወት ውስጥ የሚደበቅበትን የማድፈጫ ቦታ እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ በሚገባ ጸድቶ የተወለወለ ጠረጴዛ ላይ ቆሻሻን የምትፈልግ ዝንብ ልታርፍና ልትቆይ አትችልም፡፡ ሆኖም ጠረጴዛው በሚገባ ካልጸዳ፤ ባልጸዳው የቦታ ክፍል ላይ አንዣባ ሄዳ ታርፋለች፥ ትቀመጥማለች፡፡

   ምሳሌውን ወደ መንፈሳዊው እውነት ስናመጣው፤ ዲያቢሎስ ኑሮአችን ውስጥ ተመሳስሎ ገብቶ ራሱን ለመከለል የሚጠቀምባቸው መደበቂያዎች ንስሐ ያልገባንባቸው የኃጢአት ታሪኮቻችን በሙሉ ናቸው፡፡ (ልብ ውስጥ እስኪሰርጽ ተደጋግሞ ይነበብ)

   ከእግዚአብሔር ፈቃድ የተለየንበት፣ የእግዚአብሔርን ንጹሕ አሳብና ባሕሪይ የሳትንበት፣ በእግዚአብሔር መልካም ነገር ላይ ያመፅንበት፣ የቅድስናን ሕግ የጣስንበት ማንኛውም አስተሳሰብ፣ አነጋገርና አኗኗር ሁሉ፤ ከሥጋዊ ኑሮአችን የተደበቀ የጠላት መንፈስ መጋረጃ አድርጎ የሚከለልባቸው የዲያቢሎስ መጠለያዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ንስሐ በገባን ቁጥር እያፈረስን የምንሄደው የኃጢአትን ክምር ተራራ ብቻ ሳይሆን ከተራራው (ፊትና ጀርባ) ሆኖ በተጨባጭ በማይታይ ገመድ እንዳንርቅ ጠፍንጎ ያሰረንን ኃይል ነው፡፡

   አገላለጻችንን በጳውሎስኛ አጻጻፍ መልክ ብናሲዘው፤ ንስሐ ማለት በኛ ውስጥ አድሮ እኛ ሳንፈልግ የምንሠራውን፥ ደግሞ ፈልገን የማንሠራውን ሥራ እንድንፈጽም ምክንያት የሚሆን ኃጢአትን የሚያስወግድ መለኮታዊ መሣሪያ ነው፡፡

   ወይንም ደግሞ የራእዩን ጥቅስ መግቢያ በራችን አድርገን ንስሐን ብናይ፤ ንስሐ ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት የሚከሰንን የወገኖቻችን ከሳሽ፤ የኃጢአት መዝገቡን የሚያሰፍርበትን ሰነድ የሚቀድ የእግዚአብሔር መሐሪ እጅ ነው ልንል እንችላለን፡፡

   (እናስተውል!) ካለ ንስሐ በምንመራው ሕይወት ውስጥ፤ የዲያቢሎስ እርምጃ ከኛ አንድ እርምጃ የሚቀድምበትን ዕድል ያገኛል፡፡ በሌላ አነጋገር ንስሐ ባልጎበኘው የዕድሜያችን ዘመናት ሁሉ ላይ መናፍስት ወደፊት ቀድመው በመጓዝ ፈቃዳቸውንና እቅዳቸውን በኛ ላይ ለመፈጸም የሚያስችል ጥንካሬና አቅም አላቸው፡፡ ምክንያት? .. የእግዚአብሔር ኃይል ጽድቅ ነው ከተባለ፤ እንኪያሳ የዲያቢሎስ ኃይል ደግሞ ኃጢአት ይሆናላ፡፡ በመሆኑም በንስሐ ያልተገረሰሱ የኃጢአት ጊዜዎቻችን ራሳቸውን የቻሉ ዲያቢሎሳዊ ጉልበቶች ሆነው ለክፉው መንፈስ ያገለግላሉ፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን. . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek