Get Mystery Box with random crypto!

(የመጨረሻው ክፍል) ላነሳው የፈለኩት ትልቁ የዚህ ማጠቃሊያ ክፍል ነጥብ ዲያቢሎስን መዋጋት ማለት | በማለዳ ንቁ !

(የመጨረሻው ክፍል)

ላነሳው የፈለኩት ትልቁ የዚህ ማጠቃሊያ ክፍል ነጥብ ዲያቢሎስን መዋጋት ማለት ክፉውን ሁሉ መፋለም ነው የሚለውን ነው፡፡ በራስም ሆነ በዓለም ላይ ያለውን ክፋት ሁሉ በጽድቅ ተቃርኖ መታገል የምእመንነት ዋነኛው ኃላፊነት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እባብ ወደ ሔዋን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጆች ሕልውና ውስጥ በመከሰት ግራና ቀኝ ስለሚያደርጉት የርኩሰትና የቅድስና መተናነቅን በሚያስተነትኑ ታሪኮች የተሞላ መጽሐፍ ነው፡፡ በክፉው ዕውቀት እና በደጉ ዕውቀት መካከል የሚዋተት የባሕሪያችን የዘመናት ጉዞ ዓለምን አሁን እስካለችበት ድረስ አምጥቷል፡፡ በቃ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም! መልካምና ክፉ ተብለው ከተከፈሉት ውጪ ያለ አንድም ነገር የለም፡፡

እግዚአብሔር መልካም ነው፡፡ የእርሱ መልካምነት ከእርሱ የተገኙትንም ሁሉ ነገሮች መልካም አድርጓቸዋል፡፡ በእርሱ እውነትና ፈቃድ ውስጥ ለመኖር ይሄን መልካምነት መምረጥ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ሌላ ቀመር፣ ስልት፣ ንድፈ ሀሳብ የለም፡፡ የሃይማኖት መንገድ ሌላ ጎዳና የለውም፡፡ አምላክን ለማወቅና እርሱን ባወቅንበት ዕውቀት ውስጥ ለመቆየት መልካሙን መቀበልና ተቀብሎ መግለጥ ያስፈልጋል፡፡

ይሄ በእንዲህ ሳለ፥ መልካምነት የማይሳማማው ፍጡር በምድራችን ላይ እንዳለ አማኞች ያለ መዘንጋት ማጤን ይገባቸዋል፡፡ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ሁሉ የሚቃወም ባዕድ ኃይል ባለንባት ዓለም ላይ አለ፡፡ የበጎ ነገር ጠላት ሲሆን የምናየው ማንኛውም ነገር የዚህ ተቃዋሚ መንፈስ ውክልና ነው፡፡

እንደጠቀስነው ከእግዚአብሔር ባሕርይ ነቅተው የወጡት ሁሉ መልካም ሲሆኑ፥ ሰው መሆንም መልካምነት ነው፡፡ ክፉው ደግሞ መልካሙን ይፋለማል ካልን ሰው እንዳንሆን ይጻረራል ማለትን እናገኛለን፡፡ የዲያቢሎስ ሥራ በጠቅላላው እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ አስቀድሞ ያየውን ሰውነትን እንዳንኖር ማድረግ ላይ ያጠነጥናል፡፡ ይሄንን በሚገባ ካልተረዳነውና ካልስተዋልነው፥ ከእግዚአብሔር ጋር ያኖረናል የምንለውን መንፈሳዊ ሕይወት መኖር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

ነገሩ (አለመረዳቱና አለማስተዋሉ)፥ እንኳን መንፈሳዊውን ተሸብበንበት ያለውን ሥጋዊውን አኗኗር እንኳ በቅጡ መኖር የሕልውና ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጋል፡፡ በመሠረቱ ከመንፈሳዊነት የጀመረ ነጻነት ነው በሥጋው ኑሮአችን ሊገለጥ የሚችለው፡፡ ዕረፍት ያላገኘ ውስጥ የትም ቢወርድ የትም ቢወጣ እፎይ ሊል አይችልም፡፡ የሰላም መንፈስ ያለገራው ሕሊና መረጋጋትን ቢናፍቅ እንጂ አያገኝም፡፡ በማንነት መዝገባችን ላይ የተጻፈው ክታብ መልካሙ ጽሑፍ እስካልሆነ ድረስ በመሬታችን የምንመለከተው ውጥንቅጥ ሁሉ ለዘለቄታው ሊሰክን አይችልም፡፡

       "መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።"

                                                                    (ማቴ. 12፥35)


የዲያቢሎስ መሠረታዊ ፍልሚያ እግዚአብሔር በፈቃዱ ያስገኘውን መልካም ሰው እንዳንሆን መታገል ነው ብለናል፡፡ ይሄን ትግሉን ለማሳካትም በስብዕና ማኅደር ውስጥ ዘልቆ በመግባት የርሱን የክፋት ባሕርይ ያሰፍራል፡፡ እንደ ባላጋራነቱ ተፈጥሮአዊው መዝገባችንን አስቀድሞ በመጋራት የርሱን ማንነት ለኛ ያጋራናል፡፡ ከዛ በኋላ ወደ ውጪ ሲገለጥ የሚታየው ሁሉ ከውስጥ የታሰበው፣ የተፈለገውና የተለመደው ይሆናል፡፡

ጌታ ለተማሪዎቹ ያዛቸዋል፡፡ መንግሥተ ሰማያት መቅረቧን ስበኩ እያለ ይልካቸዋል፡፡ መስበክ ብቻ ሳይሆን የተቸገሩትንም እንዲያግዙ እንዲህ ይሳስባቸዋል፦

       "ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ።"

                                                                      (ማቴ. 10፥8)


አጋንንትም 'ወጡ' መባሉ መቼም ከውስጥ ወደ ውጪ ነው፡፡ ከሰው ውስጥ! የሰው ውስጡ ደግሞ መዝገቡ ነው፡፡ መዝገብ ባለበት በዚያ ልብ ደግሞ ይኖራል፡፡ በዚህ መዝገብ የተጻፈው በሕይወት ፊት ላይ ይነበባል፡፡ የምናስበውን እንናገራለን፣ የምንፈልገውን እንከውናለን፡፡ ከውስጣችን ያለው ውጪያችንን ይነግራል፡፡ በገሐድ የምትታየዋ የዛሬይቱ ዓለም የብዙ ውስጠቶች ውጤት ናት፡፡

ዓለም እኔ፣ አንተ፣ አንቺና ሁላችንን ነን፡፡ የእያንዳንዳችን የሕይወት መልክ የዓለምን ነባርም ነባራዊም መልክ አስገኝቷል፡፡ ዓለም ላይ ሲገለጥ የታየው ሁሉ ዓለም ውስጥ የምንኖረው እኛ የገለጥነው ነው፡፡ እንግዲህ ዓለም ክፉ ናት፣ ኢ-ፍትሐዊ ናት፣ ውሸታም ናት፣.. ስንል የዓለም መዝገቧ ስለሆንነው እኛ እያወራን ነው፡፡ ስንት ርኩስ ሀሳቦች፣ ክፉ ቃሎች፣ ስግብግብ ድርጊቶች፣ ዝብርቅርቅ መሻቶች፣ ትዕቢት ጠባዮች፣ ዓመፃ ስሜቶች ይሁኑ ዓለምን ያበላሹት?.. ቤቱ ይቁጠራቸው!

አንባቢ! በልብ መዝገብህ ውስጥ ተጽፎ እስኪታተም ድረስ ደጋግሜ እጽፈዋለሁ፡፡ ክፉ የሆነው ሁሉ ከክፉው ዲያቢሎስ ነው፡፡ ዓለም ስትፈጠር ክፉን አውቃ አልተፈጠረቺም፡፡ ዘፍጥረት አንድን ማንበብ የምለውን ያረጋግጥልሃል፡፡ መልካም ሳይሆን የተፈጠረ አንድም ነገር የለም፡፡ የፈጣሪ መልካምነት የተፈጠረውን ሁሉ መልካም አድርጎ አስገኝቶታል፡፡

ስለዚህ ዓለምን አበላሹ የምንላቸው በኛ የተገለጹ ክፋቶች ሁሉ ከክፉው መንፈስ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ከልብ ውስጥ የሚወጡት "መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ" ሁሉ የእርሱ ናቸው፡፡ (ማቴ. 15፥19) ይህንን በመተማመን ክፉውን መዋጋት ካልጀመርን በእርግጥም ዓለምን ከመክፋት የሚመልሳት የጽዋው ሙላት ብቻ ይሆናል፡፡ የጽዋውም ሙላት መቅሠፍት ነው፡፡ ከመቅደስ ጀምሮ እያንዳንዱን ክፋት እየመነጠረ የሚያጠፋ ታላቅ መቅሠፍት!

ከውስጥ የሚወጣው ነው የሚያረክሰው፡፡ ዓለም በመላዋ በክፋት እንድትያዝ ያደረጋት የአብዛኞቻችን በመልካም ያልተያዘ ውስጥ ነው፡፡ በሌላ አባባል በሕይወታችን ውስጥ ያሉ ክፉ መናፍስት ዓለምን አክፍተዋታል፤ በባሕርያቸው ባለው ጥላቻ ፍቅርን አቀዝቅዘዋታል፡፡ ፖለቲካ፣ ቴክሎኖጂ፣ ሳይንስ፣ ጥበብ፣.. ከፍታውን አግኝቷል በምንልበት በዚህ የሥልጣኔ ዘመን ክፋትም የራሱን የከፍታ ጫፍ እንዳገኘ እናያለን፡፡ ሰውነት ጎድሎ፥ ለሰው የሚያስፈልጉት ቁሶች ግን ሞልተዋል፡፡ በጎነት ከሰው ሕልውና ሸሽታለች፡፡ ውሸት አምሮባታል፥ ወፍራለች፡፡ ግብዝነት ተለምዳለች፡፡ ገንዘብ ከጭንቅላት ዙፋን ነግሣለች፡፡ ደግነት ተደብቃለች፡፡ እውነት መኖሯ እስኪያጠራጥር ድረስ ዝምታን መርጣለች፡፡ ይሄ ሆኖ ሳለ ነገሩን ይበልጥ የሚያከፋው ደግሞ የዓለም እንዲህ መክፋት ምናችንም ያልሆነ ያህል የሚሰማን ጥቂት የምንባል አይደለንም፡፡ አዎ በትክክልም.. ከውስጣችን የተከማቸ አንዳች ክፉ ጉድ አለ!

"ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያቢሎስ.." ሲል የእግዚአብሔር ቃል የሚነግረንን እያየን የማናይ ዓለማዊያን፥ ከብዙ መልካም ነገር ስተንና ሌሎችንም እያሳትን ይኸው አለን፡፡ (2ኛ ጢሞ. 3፥13) ቅድስናን የሳቱ አእምሮዎች ምን ያህል ቀውስ እስከዛሬ አመጡ ይሁን? ጽድቅን የሳቱ ልቦናዎች ምን ያህል እርግማንን አቆዩልን ይሁን? ከእግዚአብሔር የሳቱ መሪዎች ምን ያህል ጦርነት አስከተሉ ይሁን?..