Get Mystery Box with random crypto!

በተባበረ ክንድ ጠላትን ድል መንሳት ይቻላል! ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በተናጠል የተኩስ አ | በኩር ጋዜጣ Bekur Newspaper

በተባበረ ክንድ ጠላትን ድል መንሳት ይቻላል!

ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም
በተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ለወራት ከግጭት ርቆ የቆየው የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነቱን በሰላም ውይይት የመፍታት አዝማሚያ ታይቶበት እንደነበር ይታወሳል:: በተለይም በፌዴራል መንግሥት በኩል የሀገርን ጥቅም ባስከበረና ኢትዩጵያን ባስቀደመ የሠላም ውይይት ችግሩን ለመፍታት በየትኛውም ቦታ እና ያለ ቅድመ ሁኔታ ዝግጁ መሆኑ በተደጋጋሚ ገልፆል::
ይሁን እንጅ ከአመሠራረቱ ጀምሮ በውይይት ችግሮችን የመፍታት ልምድ የሌለው እና ጦርነትን መነሻ አድርጎ የመጣዉ አሸባሪዉ የትግራይ ወራሪ ቡድን ውጤት የማያመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር ለሠላም የሚደረገውን ጉዞ እንደ ልማዱ አጨናግፎታል:: ሁሌም ተጎጂ መስሎ በመቅረብ አለማቀፉን ማህበረሰብ የማወናበድ ልማድ ያለው ቡድኑ ይፋዊ የሆነ ጦርነትም ከፍቷል:: አሸባሪ ቡድኑ ካለው የቆየ ባህሪይ አንፃር ቀድሞውንም ቢሆን ለሠላም ውይይት ዴንታ የማይሠጥ መሆኑን አስመስክሯል::

መንግሥት እስከአሁን ለሠላም ሲባል የሄደበት ርቀት በመልካም ሊነሣ ይገባዋል:: ይሁን እንጂ ለሀገር ጥቅም ቆሞ የማያውቀው አሸባሪ ቡድኑ ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመወገን ዳግም ጦርነት ከፍቷል:: ወራሪ ቡድኑ ከዓመት በፊት በአማራና አፋር ክልሎች በከፈተው ወረራ በርካታ ሰብአዊና ቁሣዊ ውድመት ማድረሱ የሚታወስ ነው:: ወራሪ ቡድኑ ትግራይ ተነስቶ ሰሜን ሸዋን እስኪረግጥ ድረስም ይሠራው በነበረው የሀሠት ፕሮፕጋንዳ አብላጫውን ወስዶ እንደነበረ ሊታወስ ይገባዋል:: ያልተቆጣጠረውን ከተማ ተቆጣጥሪያለሁ፣ ይህን ያህል ሰራዊት ማርኪያለሁ፣ ደምስሻለሁ በሚሉ የሀሰት ወሬዎቹ ከሆነው በላይ ሆኖ ነበር:: በሚፈበርከው ወሬ ወራሪ ቡድኑ የጥቃት አድማሱን ያሰፋበት አጋጣሚ ተፈጠሮ እንደነበር ማስታወስ ይገባል::
አሁን ዳግም በጀመረው ጦርነት እንደ ከዚህ ቀደሙ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ መረበሽም መዘናጋትም አይገባም ብለን እናምናለን:: በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ መረጃዎችንም በጥንቃቄ መመልከት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደምንገኝ መገንዘብ ግድ ይላል:: ወራሪ ቡድኑ ራሱ የጀመረውን ጥቃት በተጠቃሁ መግለጫ አጅቦታል:: በዚህ መግለጫና በጀመረው ጦርነት መላው ኢትዩጵያዊያን ግራ ሣንጋባ ዳግም በአንድነት ቆመን ለማሸነፋችን ጥርጥር ሳይገባን ልንታገል ይገባል::

ኢትዩጵያዊያን ከዚህ የጥፋት ቡድን የሚሰነዘርን ማንኛውንም ተግባር በፅናት ታግለን የማሸነፍ አቅሙ እንዳለን መገንዘብ ይጠይቃል:: ይህም የሚሆነው እንደቀድሞው ታሪካችን በጋራ ቆመን ጠላቶቻችን በመፋለም ነው::

ዜጐችን ከጥቃት የመጠበቅ ሀላፊነት ያለበት መንግሥት ሀገርን የማዳን ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታውን በተገቢው መንገድ መወጣት ከመቸውም ጊዜ በላይ ይጠበቅበታል:: ይህንንም ጀግናዉ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች በተግባር እያሣዩን ነው:: ለዚህ ሀገርን የመታደግ ታላቅ ተጋድሎም መላው ኢትዩጵያዊ ድጋፉን ሊሰጥ ይገባል::
መንግሥት የመጀመሪያዉን ሕግ የማስከበር ዘመቻ በድል ካጠናቀቀ በኋላ ለስምንት ወራት ያህል የትግራይ ክልልን በጊዜያዊ የመንግሥት አስተዳደር መርቷል:: በወቅቱ በክልሉ የፖለቲካ ሥራ በመሥራት ህዝቡን ከአሸባሪ ቡድኑ መነጠል አልተቻለም ነበር:: አሁንም ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቅ ዘንድ የአሸባሪ ቡድኑን እኩይ አላማ በማጋለጥ ከህዝብ የመነጠል ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል::

በመንግሥት በኩል አሁን ያለውን ሕዝባዊ አንድነት ይበልጥ በማጐልበት የፀጥታ ሀይሉን ዝግጅት በማጠናከር ወራሪ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማክሰም ግድ ይላል:: የአሸባሪ ቡድኑን እንቅስቃሴ በዘላቂነት እልባት ለመስጠትም መንግሥት በተቀናጀ ዕቅድ በመመራት የፀጥታ ሀይልን ከማጠናከር እኩል የጎለበተ የፖለቲካ አካሄድን ሊከተል ይገባል:: አሸባሪ ቡድኑ በጦርነቱ ከገፋበትም ህልውናውን አጥፍቶ የህዝብን ሠላም በዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል::
የሀገር መከላከያ ሰራዊትና መላ የፀጥታ ሀይሉ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት እንዲችል ህዝባዊ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን መረዳት ይጠይቃል:: ይህ ሲሆንም የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነትን አስከብሮ መቀጠል ይቻላል::

የሕወሓት አፈቀላጢዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ሥም በማጉደፍ ተግባራቸው ተሰማርተዋል:: ይህ ተግባር እኩይ አላማ ያለው መሆኑን በመገንዘብ በተቃራኒ ቆሞ መታገል ይገባል:: አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ግን እኩይ ተግባሩን ከማውገዝ ይልቅ የተዛባን መረጃ ሲቀባበሉት ይስተዋላል:: እናም ከዚህ ተግባር መታቀብ ይገባል::
ሠራዊቱ ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት በፅናትና በጥንቃቄ ተዘጋጅቶ በቆመበት በአሁኑ ወቅት በጠላት የተለመደ የሀሰት የፕሮፓጋንዳ ወጥመድ መጠለፍ አይገባም:: የሰራዊቱን እንቅስቃሴ በመገናኛ ብዙሃን ባልተገባ መልኩ ማሰራጨትም የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመገንዘብ ዜጐች ከዚህ ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል:: ይህን ተላልፈው በሚገኙት ላይም ተጠያቂነትን በማስፈን ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል:: የጠላትን አጀንዳ ከማራገብ በመቆጠብ በሰከነ መንገድ ወቅታዊ ሁኔታውን መመልከት ተገቢነትን የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ እንገኛለን:: ህዝብ ከመንግሥትና ከፀጥታ ሀይሉ ጋር ተገቢውን መናበብ በመፍጠር የአሸባሪ ቡድኑን ዳግም ጥቃት የህልውናው ፍፃሜ ማድረግ የሚጠይቅበት ወሣኝ ወቅት ላይ መገኘታችን ልብ ሊባል ይገባዋል:: በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ድልነስታ እንደምትቀጥል አንጠራጠርም! ::

(ኤልያስ ሙላት)
በኲር ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp://www.amharaweb.com/Bekur ላይ ማግኘት ይችላሉ።