Get Mystery Box with random crypto!

ቤተ ክርስቲያን 'እንቁዎቼ' ከምትላቸው ሴት ጻድቃን አንዷ ቅድስት እንባ መሪና ናት። ጣዕመ ዜናዋ | ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

ቤተ ክርስቲያን "እንቁዎቼ" ከምትላቸው ሴት ጻድቃን አንዷ ቅድስት እንባ መሪና ናት። ጣዕመ ዜናዋ ሙሉ ሕይወቷ አስገራሚም አስተማሪም ነው። ቅድስቷ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ተወልዳ ያደገች ክርስቲያን ናት። ወላጆቿ ከእርሷ በቀር ሌላ ልጅ የሌላቸው ሲሆን በአኗኗራቸውም ደግና ቅን ነበሩ።
ቅድስት እንባ መሪና ትክክለኛ ስሟ "መሪና" ነው። ምክንያቱም "እንባ መሪና" የወንድ ስም ነውና። ነገር ግን በወንድ ስም የተጠራችበት የራሱ ታሪክ አለውና እርሱን እንመለከታለን።
ቅድስት መሪና ገና ልጅ ሳለች እናቷ ማርያም ሞተችባት። ደግ አባት አንድ ልጁን በሥጋዊም በመንፈሳዊም ሳያጐድልባት አሳደጋት። ዕድሜዋ አሥራ አምስት ዓመት በሆነ ጊዜ ወደ ፊቱ አቅርቦ "ልጄ! እኔ ወደ ገዳም ስለምሔድ አንቺን መልካም ባል ላጋባሽ።" አላት።
ቅድስት መሪናም "ነፍሰ ዚአከ ታድኅን ነፍሰ ዚአየኑ ታጠፍእ - የአንተን ነፍስ አድነህ እንዴት የእኔን ትተዋታለህ? እኔም እመንናለሁ።" አለችው። አባቷ የተናገረችው ከልቧ እንደሆነ ሲያውቅ "ልጄ! ገዳም ሁሉ በአካባቢው የወንድ ብቻ ነውና ስሚኝ።" አላት።
እርሷ ግን "አባቴ! ግዴለህም ስሜን እንደ ወንድ ቀይረህ አለባበሴንም ለውጥ።" አለችው። (እንደ ወንድ ለበሰች ማለት ግን እንደ ዘመኑ ዓይነት እንዳይመስላችሁ አደራ!)
ከዚያ አባትና ልጅ ሃብት ንብረታቸውን ሸጠው ለነዳያን አካፈሉ። በፍጹም ልባቸውም መነኑ። በደረሱበት ገዳም ቅድስት መሪና በወንድ ስም "እንባ መሪና" በሚል ገባች። ቀጣዩ ሥራዋ እንደ ወንዶች እኩል መስገድ፣ መጾምና መጸለይ ነበር።
ይህችን ቅድስት ልናደንቃት ግድ ይለናል። ማንም በእርሷ አይፈተንም፤ አያውቋትምና። እርሷ ግን ወጣት ሆና አንድም ሴት በሌለበት ገዳም ጸንቶ መቆየት በራሱ ልዩ ነው። መልአካዊ ኃይልንም ይጠይቃል።
ተጋድሎዋ በጣም ስለ በዛ ወንድሞች መነኮሳት ይደነቁባት ነበር። ጺም ስለሌላትና ድምጿ ቀጭን ስለሆነ አልተጠራጠሩም። ምክንያቱም ጃንደረባ ናት ብለው አስበዋልና። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አባቷ ታሞ ከማረፉ በፊት አበ ምኔቱን ጠርቶ "ወደ ከተማ ልጄን እንዳትልክብኝ አደራ!" ብሎት ነበር።
ያም ሆኖ አንዳንድ መነኮሳት ቅሬታ በማንሳታቸው ወደ ከተማ ተላከች። ችግሩ ለተልእኮ ባደሩበት ቤት አንድ ጐረምሳ ገብቶ የአሳዳሪውን ልጅ ከክብር አሳንሷት ሔደ። ሲወጣም "ድንግልናሽን ያጠፋ ማን ነው? ካሉሽ ያ ወጣት መነኩሴ አባ እንባ መሪና ነው በይ።" አላት።
ከሦስት ወራት በኋላ የዚያች ዘማ ሴት ጽንስ በታወቀ ጊዜ ለአባቷ "አባ እንባ መሪና እንዲህ አደረገኝ።" አለችው።
አባት መጥቶ እየጮኸ መነኮሳትን ተሳደበ። አበ ምኔቱ ግራ ተጋብቶ ቢጠይቀው "የአንተ ደቀ መዝሙር እንባ መሪና ልጄን ከክብር አሳነሳት።" አለው። አበ ምኔቱ እውነት መስሎታልና ቅድስቲቱን ጠርቶ ቁጣና እርግማንን አወረደባት። በዚያች ሰዓት ተንበርክካ አንድ ነገር ወሰነች።
"ሴት ነኝ።" ብሎ መናገሩስ ቀላል ነው። ግን ደግ ናትና የእነዚያን አመጸኛ ሰዎች ኃጢአት ልትሸከም ወሰነች። ቀና ብላ "ማሩኝ ወጣትነት ቢያስተኝ ነው?" አለቻቸው። ተቆጥተው ዕለቱን እየገፉ ከገዳም አስወጧት። ከባድ ቀኖናም ጫኑባት። ከስድስት ወራት በኋላም የእርሷ ልጅ ነው የተባለ ሕፃን አምጥተው ሰጧት።
ይህኛው ግን ከባድ ፈተና ሆነባት። እንዳታጠባው አካሏ በገድል ደርቋል። በዚያ ላይ ድንግል የሆነች ሴት ወተት የላትም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት የበጋውን ሐሩር የክረምቱን ቁር ራሷ ታግሣ ለሕፃኑ ከእረኞች ወተት እየለመነች እየመገበች ሦስት ዓመታት አለፉ።
በዚህ ጊዜ ወደ ገዳሙ ከከባድ ቀኖና ጋር ተመለሰች። ሕፃኑን ስታሳድግ፣ ለገዳሙ ስትላላክ፣ ምግብ ስታዘጋጅ፣ ውኃ ስትቀዳ፣ የእያንዳንዱን ቤት ስታጸዳ ሠላሳ ሰባት ዓመታት አለፉ። ሕፃኑም አድጐ ደግ መናኝ ወጣው። (የቅድስቷ እጆች ያሳደጉት የታደለ ነው።)
በመጨረሻ ቅድስት መሪና (እንባ መሪና) ታማ ዐረፈች። እንገንዛለን ብለው ቢቀርቡ ሴት ናት። እጅግ ደንግጠው አበ ምኔቱን ጠሩት። በዙሪያዋ ከበው እንባቸውን አፈሰሱ። ጸጸት እንደ እሳት በላቻቸው። ሥጋዋን በክብር ገንዘው በአጐበር ጋርደው በራሳቸው ተሸክመው ምሕላ ገቡ።
ሙሉውን ቀን "ስለ ቅድስት መሪና ብለህ ክርስቶስ ሆይ ማረን?" ሲሉ ዋሉ። ድንገት ግን ከተባረከ ሥጋዋ "ይቅር ይበለን።" የሚል ድምጽን ሰምተው ደስ ብሏቸው ቀበሯት። እነዚያ ዝሙተኞችም ከእርሷ ይቅርታን እስካገኙበት ቀን አብደው ኑረዋል።