2023-01-19 18:15:30
#ጥር_12_ጌታችን_የፈጸመው_የመጀመሪያው_ተአምሩ_የሚታሰብበት_በዓል_ነው።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አውራጃ በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ተወልዶ በሠላሣ ዘመኑ በሠላሣ ዓመተ ምሕረት በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾመ ጸለየ፤ በጠላት ዲያብሎስ ተፈተነ። ፈተናውን ድል አድርጎ ሱባኤውን ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን ከእናቱ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም እና ከቅዱሳን ሐዋርያቱ ጋር በመሆን በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር በሰርግ ቤት ተገኝቶ ቤተ ከብካቡን በትምህርቱ በተአምራቱ ባረከ። ኢየሱስ ክርስቶስ ይኽን ድንቅ ተአምር በቃና ዘገሊላ ያደረገው በገዳመ ቆሮንቶስ ሱባኤውን ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን የካቲት 23 ቀን ነው። ይሁንና አባቶቻችን ሊቃውንት «የውኃ በዓል ከውኃ በዓል ጋር መቀናጀት አለበት» በማለት በጥምቀት በዓል ማግስት ጥር 12 ቀን እንዲከበር አድርገውታል። እኛም ይኽንኑ ቀን ጠብቀን በዓሉን በማክበር ላይ እንገኛለን።
የዮሐንስ ወንጌል ም.2፤1 “በሦስተኛው ቀን በገሊላ አውራጃ በቃና ሰርግ ነበር” ይላል፡፡ ከዚህ በኋላ የታሪኩን ምስጢራዊ ትርጉም በቅደም ተከተል እንመልከት:-
1.“#የኢየሱስ_እናት_በዚያ_ነበረች_ኢየሱስ_ደቀመዛሙርቱ” ይላል፡፡ከዚህ ላይ የምንረዳው መጀመሪያ እመቤታችን ድንግል ማርያም አስቀድማ በሰርጉ ውስጥ መኖሯን ነው፡፡ እናት ከተጠራ በኋላ ነው ልጅ የሚጠራና ከዚያም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ከመምህር ጋር ደቀመዝሙር ይጠራልና ከእርሱም ጋር ደቀመዛሙርቱ ተጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር በወቅቱ ወይን ባለቀ ጊዜ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወይን የላቸውም ያለችው፡፡ እርሱም “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ፤ ጊዜዬ ገና አልደረሰምና” አላት፡፡ ወደምሥጢሩ ስንገባ፤
2.#ሦስተኛ_ቀን_ምንድን_ነው?
#ሀ. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀ ጥር 11 ቀን ነው፡፡ ወዲያውኑ እንደተጠመቀ ሳይውል ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፤ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመ፤ ጾሙ የካቲት 20 ቀን ይፈጸምና የካቲት 23 ቀን “በሦስተኛው ቀን ሰርግ ነበር” ይላል፡፡
#ለ_ሦስተኛ_ቀን_የሚለው · የመጀመሪያ ቀን የሚባለው ዘመነ አበው ፤ አዳም፤ እነአብርሃም፤ ይስሐቅ አበው የነበሩበት ዘመን ሲሆን፤ · ሁለተኛ ቀን የሚባለው ዘመነ ኦሪት ነው፤ እነሙሴ የነበሩበት ዘመን ሲሆን · ሦስተኛ ቀን የተባለው ዘመነ ሐዲስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ሰርግ የሆነው፡፡
3.“#እመቤታችን_አስቀድማ_ነበር” ሲል ደግሞ እመቤታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋዊ እድገቱ እንደምትቀድመው ነው፡፡ እንኳን የእርሱ እናት ትቅርና ዮሐንስ መጥምቁም በ6 ወር ይቀድመው ነበር፡፡ እንግዲህ እናትን ሳያውቁ ልጅን ቢጠይቁ ያስቸግራል፡፡ አስቀድማ የነበረችውን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆን በፊት አብራን የኖረችውን ድንግል ማርያምን ሳናውቅ ኢየሱስ ብንል ትርፉ ድካም ብቻ እንጂ አይሳካም፡፡ ዛሬም ቢሆን “ኢየሱስ” ከማለት በፊት አስቀድመን እርሷን አማልጅን እንበላት፡፡
ነገረ ድኅነትን ስናስብ በህሊናችን አስቀድመን እርሷን መሳል አለብን፤ ነገረ ማርያም የምሥጢረ ሥጋዌ መቅድም (መጀመሪያ)፤ የነገረ ድኅነት መሠረት ነውና፡፡ ጌታችን ተወለደ፤ ተሰደደ፤ አስተማረ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተነሳ፤ አረገ፤ ዳግም ይመጣል ሲባል በድንግል ማርያም ሥጋ ነው፡፡ በነገራችን ሁሉ እርሷን ማስቀደም እንዳለብን ነው የምንረዳው፡፡
4.#ወይኑ_ባለቀ_ጊዜ “#ወይን_የላቸውም” አለች፡፡
የወይኑን ማለቅ ለእመቤታችን ማን ነገራት? ሙሽራው ወይስ ከሰርገኞቹ መካከል አንዱ? ለዚህ ምንም አይነት መልስ እንደማይሰጥ ግልጽ ነው፡፡ ድንግል ማርያም ግን እራሷ ነበር ያወቀችው፤ ነቢይት ናትና፡፡ ስለሆነው እንዲሁም ስለሚሆነው ታውቃለች፤
ቅዱስ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ካመሰገኗት በኋላ “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” ማለቷ ወደፊት ስለሚመጣው ትውልድ ነበር የተናገረችው፤ ይህ ነቢይነቷን የሚገልጽ ነው፡፡ (ሉቃ. 1፤48-49) ኢሳይያስ በትንቢቱ በምዕራፍ 8፤1 “ወደ ነቢይቱ ሄድኩ ጸንሳም ነበር” የሚላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡
በ2ኛ ነገ. 6፤8 በሶርያ የነበረው ንጉሥ በኢየሩሳሌም ያለውን ንጉሥ ሊወጋ (ሊገድል) በፈለገ ጊዜ በእልፍኝ ሆኖ የሚመክረውን ምክር ነቢዩ ኤልሳዕ ኢየሩሳሌም ሆኖ ይመለከትና ያውቅ ነበር፤ ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን እያየ ነበር፡፡ ስለዚህም የኢየሩሳሌሙን ንጉሥ “ከቤትህ እንዳትወጣ ሶርያውያን ሊገድሉህ ይፈልጋሉ” እያለ ይመክረው ነበር፡፡ ምን አይነት ጸጋ እንደሆነ አስቡት፤ ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን ነገር ማወቅ፡፡
ታዲያ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ነቢያት እንዲህ የርቀቱን ነገር የሚያውቁ ከሆነ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዶኪማስን የቤት ችግር፤ የወይን ማለቅ ብታውቅ ብትረዳ ምን ይደንቅ? የመለኮት እናትም እንዴት ጸጋው ይበዛላት? እንደ እመቤታችንስ ጸጋው የበዛለት በዘመነ ብሉይ ማን ነበር? “ጸጋን የተመላሽ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ” የተባለች ድንግል ማርያም አይደለችምን? እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡
6. “ #አንቺ_ሴት ”
ጌታችን ይህንን ቃል የተናገረው ሴት የሚል ቃል የፆታ መጠሪያ ነውና በፆታዋ አክብሮ ሲጠራት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሔዋን ከአዳም በተፈጠረች ጊዜ አዳም እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር “ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ናት ስጋዋም ከስጋዬ ናት እርሷም ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ዘፍ.2፥23 በመሆኑም ጌታችን አንቺ ሴት ማለቱ ከስጋዋ ስጋ ከነፍሳ ነፍስ መንሳቱን ለማጠየቅ ነው ።
6.“#ከአንቺ_ጋር_ምን_አለኝ?” ያላትስ ምን ማለቱ ነበር?
ወግጅልኝ፤ ሂጂልኝ ማለቱ ሳይሆን “ያልሽኝን እንዳልፈጽምልሽ ምን የሚከለክለኝ ነገር አለ” ሲል ነው፡፡ “እናትና አባትህን አክብር፤ ለእናትና ለአባትህ ታዘዝ” ያለ አምላክ እናቱን ሂጂልኝ፤ ወግጅልኝ አላት ሲባል አያሳፍርም? ይህማ እንዳይሆን ለእናቱ እየታዘዘ አደገ ወንጌል ይል የለምን፡፡ (ሉቃ. 2፤51)
7.“#ጊዜዬ_ገና_አልደረሰም”
ይህን ያለው ወይኑ ከእንስራው በደንብ ካለቀ በኋላ ውሀ ሞልተው የጌታን ተአምር እዲታይ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ወይኑ በደንብ ሳያልቅ ከዚያው ላይ ቢሞላው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር አይታወቅም፤ ረድኤት አሳደረበት ይባላል አንጂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወይኑ ሁሉ ካለቀ በኋላ ግን ውሀ ተሞልቶ ወይን ሲሆን ተአምሩ ይታወቃል፤ ይገለጻል፡፡ ለዚህም ነው “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ተአምር በቃና አደረገ” የሚል፡፡( ሌላም ሰፊ ምሥጢር ቢኖርም ለአሁኑ ግን ይህን አቅርበናል፡፡)
የሰርገኛው ቤት ብቻ አይደለም፤ ወይን የጎደለበት ሁላችንም ወይን የለንም የሕይወት እንሥራችን ጎደሎ ነው፡፡ ይህ እንስራ (ጋን) የሚሞላው በእመብርሀን አማካኝነት ነው፡፡ እርሷ ከሌለችበት በፍጹም ሊሞላ አይችልም በመሆኑም ለሁሉም ሰው ለማስገንዘብ የምንወደው በቅድሚያ ጸጋ የበዛበት እመቤት መያዝ እንዳለብን፤ ለምን እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር ነውና፡፡
228 viewsbisrat, 15:15