Get Mystery Box with random crypto!

#ጥር_30_ቅድስት_ሶፍያና_ሦስት_ልጆቿ_በሰማዕትነት_ዐረፉ ። ይኽችም ቅድስት ሶፍያ ከአንጾኪያ | ዝክረ ብሒለ አበው

#ጥር_30_ቅድስት_ሶፍያና_ሦስት_ልጆቿ_በሰማዕትነት_ዐረፉ ።

ይኽችም ቅድስት ሶፍያ ከአንጾኪያ ከከበሩ ወገኖች የተገኘች ናት፡፡
የልጆቿ ስም ጲስጢስ፣ አላጲስና አጋጲስ ነው፡፡ የስማቸውም ትርጓሜ በቅደም ተከተላቸው መሠረት ‹‹ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር›› የሚል ነው፡፡ ዕድሜአቸውም 12፣ 10 እና 9 ነው፡፡ የራሷ የሶፍያ የስሟ ትርጓሜ ደግሞ ጥበብ ማለት ነው፡፡

ልጆቿንም ወደ ሮሜ ከተማ ወስዳ እግዚአብሔርን መፍራትንና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማረቻቸው፡፡ የልጆቹም ምግባር ሃይማኖታቸው በከሃዲው የሮም ንጉሥ በአርያኖስ ዘንድ ስለተሰማ ንጉሡ ጭፍሮቹን ልኮ አስመጣቸው፡፡

እናታቸውም ‹‹ልጆቼ ተጠበቁ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ክብር በማየት ልባችሁ እንዳይደክምና ከዘላለማዊ ክብር እንዳትርቁ፣ ከሙሽራው ከክርስቶስ ጋር ሆናችሁ ወደ ሰማያዊው ሠርግ እንዲትገቡ ጠንክሩ…›› እያለች ትመክራቸውና ታጽናናቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ እናታቸው ይዛ ወደ ንጉሡ አቀረበቻቸው፡፡

ንጉሡም ታላቂቱን የ12 ዓመቷን ጲስጢስን ‹‹ስታድጊ ከመንግሥቴ ታላላቅ ባለሥልጣናት ውስጥ ከአንዱ ጋር አጋባሻለሁ፣ ብዙ ስጦታንም እሰጥሻለሁ፡፡ አሁን ግን ለጣዖቴ ለአጵሎን ስገጂ›› እያለ ሊደልላት ሞከረ፡፡ እርሷም ንጉሡንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገመቻቸው፡፡ ንጉሡም አማልክቶቹንና እርሱን ስለረገመች ቅድስት ጲስጢስን እጅግ በጽኑ ሥቃዮች አሠቃያት፡፡ በብረት ዘንግ አስደበደባት፤ ጡቶቿን አስቆረጣቸው፤ በብረት ምጣድ አድርጎ ከሥር እሳት አስነደደባት ነገር ግን በእሳቱ ውስጥ ሆና ስትጸልይ እሳቱ እንደጠዋት ጤዛ ቀዝቃዛ ሆነ፡፡ በዙሪያዋ ያሉና ይህንን ተአምር ያዩ ሰዎች ሁሉ ‹‹በዚህች ብላቴና አምላክ እናምናለን›› ብለው ጮኹ፡፡ ወዲያውም ራሶቻቸውን ቆረጧቸውና በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡

ከዚህም በኋላ የቅድስት ጲስጢስ አንገት ይቆርጡት ዘንድ ንጉሡ አዘዘ፡፡ እንዳዘዘውም አንገቷን ሰየፏትና ሰማዕትነቷን በድል ፈጽማ የክብር አክሊልን ተቀዳጀች፡፡ እናቷም ሥጋዋን አንሥታ ወሰደች፡፡

አሁንም ንጉሡ በሁለተኛይቱ ልጅ በቅድስት አላጲስ ላይም እንዲሁ ተመሳሳይ ሥቃይ አደረሰባትና አንገቷን አስቆረጠው፡፡ አሁንም እናቷ ቅድስት ሶፍያ ሥጋዋን አንሥታ ከወሰደች በኋላ እንዳትፈራ በማሰብ ስለ 9 ዓመቷ ታናሽ ልጇ ስለ አጋጲስ ጸለየች፤ አጽናናቻትም፡፡
ወዲያውም አጋጲስን አንስተው በመንኰራኩር ውስጥ ጨመሯት፡፡ የታዘዘ መልአክም መንኰራኩሩን ሰበረውና በሰላም ወጣች፡፡

ዳግመኛም ነበልባሉ እስከ ሰማይ የሚደርስ እሳትንም አንድደው በዚያ ይጨምሯት ዘንድ ንጉሡ አዘዘ፡፡ ቅድስት አጋጲስም በመስቀል ምልክት አማትባ ወደ እሳቱ ተወርውራ ገባች፡፡ ጌታችንም መልአኩን ልኮ እሳቱ እንደ ውርጭ አቀዘቀዘላት፡፡ በዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሁለት ነጫጭ ልብሶችን የለበሱ ሰዎች በልብሳቸው ሲጋርዷት አይተው እጅግ አደነቁ፡፡ በጌታችንም ስም አምነው ምስክንርነታቸውን ሲሰጡ ራሶቻውን በሰይፍ ቆርጠዋቸው በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡

በመጨረሻም የቅድስት አጋጲስንም አንገቷን በሰይፍ ቆርጠው ሰማዕትነቷን በድል ፈጽማ አክሊልን እንድትቀዳጅ አደረጓት፡፡ የከበረች ሶፍያም የሦስት ልጆቿን ሥጋቸውን ወስዳ ገነዘቻቸውና ከከተማው ውጭ ወስዳ ቀበረቻቸው፡፡

በ3ኛውም ቀን መቃብራቸው ላይ ሄዳ በማልቀስ ነፍሷን ይወስድ ዘንድ ጌታችንን ለመነችው፡፡ ጌታችንም ልመናዋን ሰምቶ ጥር 30 ቀን ነፍሷን ወሰዳት፡፡ ምእመናንም መጥተው ገንዘው ከልጆቿ ጋር ቀበሯት፡፡ ከሃዲው ንጉሡ ግን በተአምራት ወዲያው ዐይኖቹ ጠፍተው ሥጋው ሁሉ ተሰነጣጠቀ፡፡ እጆቹም ተቆራርጠው፣ ሰውነቱ ተልቶና ሸቶ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በሰማዕታቱም ጸሎት ይማረን!!!