Get Mystery Box with random crypto!

+በመካከላችን ያለችው የእግዚአብሔር መንግስት+ በዚህ ምድር ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር ካልተዛመድን | ማዕተብ

+በመካከላችን ያለችው የእግዚአብሔር መንግስት+

በዚህ ምድር ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር ካልተዛመድን በሰማያት ልንዛመደው አንችልም፤ የመንግሥቱ ጣዕም ያለው በዚህ ነውና። ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ዝምድና እዚህ ምድር ላይ ይጀምራል። ይህም እንደ እግዚአብሔር እንደ ራሱ "ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ።" ምሳ 23፥26 በሚለው ጥያቄ ይጀምራል። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ልብን አንጽቶ በፍቅር ከሞላው በኋላ በዚያ ራሱን ያሳድራል። ወንጌል "የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና።"ሉቃ 17፥21 ብሎ እንደሚናገር ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ማረጋገጫ ይሆናል።

ስለዚህ የሰማያትን መንግሥት ከማግኝት በፊት ሰው በውስጡ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ማግኝት መቻል አለበት። ይህ ይሁን እንጂ አንድ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረት ሊያገኝ የሚችለውስ እንዴት ነው? ሁል ጊዜ ከእርሱ ጋር የሚሆነውስ እንዴት ነው? በዚህ ዙሪያ የምሰጣችሁ ምክር ምንጊዜም ቢሆን በእርሱ እንድትጠመዱ ሲሆን ይህም በቤተክርስቲያን ውስጥ ስላለው ስለ እርሱ ሥራና ስለ ራሱ በማንበብ የሚከናወን ይሆናል።

ከቅዱሳኑ ጋር ስላለው ዝምድና ስለ ድንቅ ባሕርያቱና በማንኛዎቹም አጋጣሚዎች ውስጥ ስላለው ስለ እርሱ እጅ አንብቡ ። በዚህ ጊዜ ልባችሁ በእርሱ ፍቅር ይንቀሳቀሳል። በማንኛውም ጊዜ ውስጥም ከእርሱ ጋር ይገናኝ ዘንድ ዝግጁ ነው ።

+አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ+