Get Mystery Box with random crypto!

ከአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል በህቡዕ ተላልፏል የተባለውን የትራንስፖርት እንቅስቃ | Ayu Zehabesha-Official (አዩ ዘሀበሻ)

ከአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል በህቡዕ ተላልፏል የተባለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ገደብ ጥሪን ተከትሎ በአንዳንድ አከባቢዎች ላይ የትራንስፖርት ፍሰት መስተጓጐል ቢያጋጥምም በአብዛኛው ሰላማዊ እንቅስቃሴ አለ

ባለፈው ሳምንት በትውልድ ቀዬያቸው መቂ የተገደሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል በህቡዕ ተላልፏል የተባለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ገደብ ጥሪን ተከትሎ አንዳንድ አከባቢዎች ላይ የትራንስፖርት ፍሰት መስተረጓጎል ሲያጋጥም በሌሎች አከባቢዎች ደግሞ እንቅስቃሴው በመደበኛ ሁኔታ ስለመቀጠሉ ተገልጿል፡፡

ከባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 05 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በውል ከማይታወቅ አካል ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል በተባለው በዚህ ጥሪ መሰረት ከከተሞች ወደ ከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ መጠየቁን ማህበረሰቡ በስጋት ያነሳዋል፡፡ መሰል የእንቅስቃሴ ገደቦች እስካሁንም በኑሮ ውድነት፣ በግጭት እና ስራ አጥነት የተፈተነውን የማህበረሰቡን ህይወት ይብልጥ እንደምፈትንም እየተገለጸ ነው፡፡

ትናንት ማምሻውን ከአዲስ አበባ ወደ ሃዋሳ በሞጆ፣ ባቱ እና ሻሸመኔ በኩል በርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን አቆራርጠው ወደ ሃዋሳ ለስራ ያቀኑት ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በዚህ መስመር ከመደበኛ ጋር የተጠጋ የትራንስፖርት ፍሰት ማስተዋላቸውን አንስተዋል፡፡ “መንገድ አንግዲህ አንዳንዶቹ ክፍት ነው ይላሉ አንዳንዶቹ ግን እንደወትሮ አይደለም ይላሉ፡፡ እኔ ግን ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ሃዋሳ ስመጣ ምንም ያስተዋልኩት ችግር የለም፡፡ በመደበኛ እንቅስቃሴ ነው የመጣሁት፡፡ አሁን ዛሬም ከሻሸመኔ ወደ አዳማ የሄዱ ጓደኞቼ ነበሩ መቂ ላይ ካለው መጠነኛ ስጋት ውጪ በሰላም ገብተዋል” ብለዋል፡፡

ሌላው በትናንትናው እለት ከሀዋሳ በዚሁ ተመሳሳይ መስመር ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ አስተያየት ሰጪም የተለመደው የትራንስፖርት ፍሰት ማስተዋላቸውን ገልጸው፤ ከትናንሽ የግል ተሽከርካሪዎች እስከ ትላልቅ የህዝብ ማመላለሻ ባሶች እና የጭነት ተሽከርካሪዎች ስጓዙ መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ “እኛ በመጣንበት ከሃዋሳ ወደ ባቱ በዚያም በፍጥነት መንገድ በኩል ምንም አላየንም፡፡ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ነው አዲስ አበባ የገባነው፡፡ ትላልቅ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ጨምሮ ሁሉም ስሄድ ተመልክተናል” ነው ያሉት፡፡

ጥሪው ቀርቧል ከተባለበት ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እስከዛሬ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ወዳሉ ከተሞችም መደበኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ስደረግ ሰንብቷል፡፡ ከዚህም መስመር አልፎ ከአዳማ ወደ አሰላ እና ከአሰላ ወደ በቆጂ ያለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ይዞታ የጠየቅናቸው አንድ የበቆጂ ከተማ ነዋሪ እንዳሉት፡ “ባለፈው ሳምንት አከባቢ በነዳጅ እጥረት ነው በሚል ከተስተጓጎለው መደበኛ ፍሰት ውጪ ባሁኑ ዛሬንም ጨምሮ ትራንስፖርት በመደበኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው” ይላሉ፡፡

ከምዕራብ ኦሮሚያ ነቀምቴ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ ደግሞ “ከተማ ውስጥ የባጃጅ እንቅስቃሴ አለ መደበኛ ነው፡፡ ምንም ከተለመደ ውጪ የሆነ ነገር የለም፡፡ ግን ከከተማ ወደ ከተማ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን ምዕራብ ወለጋ ባለሚ በምትባል ከተማ መኪና ስለመቃጠል ሰምተናል” ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ተነስተው በሲሚንቶ ግብዓቶቿ ወደ ምትታወቀው የምዕራብ ሸዋ ዞን አደዓ በርጋ የምንቀሳቀሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች እንደወትሮ መንገድ ላይ ባይታዩና የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርትም መንገድ ላይ በዝተው እንደወትሮ ባይስተዋሉም መንገድ ግን ክፍት ነው ይላሉ፡፡ “መንገድ ክፍት ነው ዛሬ ነው ወደ እንጭኒ ከተማ የመጣሁት፡፡ ግን እንደ ወትሮ አይደለም፡፡ ይህን የትራንስፖርት ገደብ ስባል እንጂ ማን እንደሚጠራው አናውቅም፡፡ አሁን ዛሬ በተለይ ከተለመደው እንቅስቃሴው ቀንሷል” ነው ያሉት፡፡
#ዶቼቨሌ #አዩዘሀበሻ
========================
ጥቆማ
የቴሌግራም ቻናሉን join አድርጉ፣ለሌሎች ጋብዙ
http://t.me/ayuzehabeshaofficial
http://t.me/ayuzehabeshaofficial