2022-08-18 16:51:59
[ደብረ ታቦር]
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
❖ ይኽ በዓል ከጌታችን 9ኙ ዐበይት በዓላት አንደኛው ሲኾን በዓሉ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ላይ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ታሪኩ በ3ቱ ወንጌላት ላይ የተጻፈ ሲኾን ጌታችን አምላችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎቹን ሐዋርያትን ከእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ የምስጢር ደቀ መዛሙርት የሚባሉት፣ በእምነት በተስፋ በፍቅር የሚመሰሉት ሦስቱን (ጴጥሮን፣ ያዕቆብን፣ ዮሐንስን) ይዟቸው ወደ ታቦር ተራራ ወጣ።
የሞተውን ሙሴን ከ1644 ዓመታት በኋላ አምጥቶ፤ የተሰወረውን ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ የሕያዋን አምላክና የሙታን አሥነሺያቸው ርሱ መኾኑን የገለጸበት ታላቅ ምስጢር የተከናወነበት ነው፡፡ (ማቴ 17፡1-9)።
❖ ጌታ 8ቱን ሐዋርያት ይዟቸው ያልወጣበት በይሁዳ ምክንያት ነው ምክያቱም ከምስጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባኹበት ባለ ነበርና ነው፤ ነገር ግን በተራራው ላይ ለ3ቱ የተገለጸው ምስጢር ከተራራው ሥር ላሉት ከይሁዳ በስተቀር ተገልጾላቸዋል፤ ለእኛም እንደ ሐዋርያት ምስጢሩን ጥበቡን ይግለጽልን፡፡
❖ ብዙ ተራሮች ሳሉ የታቦር ተራራን የመረጠበት
1)አስቀድሞ የጌትነት ክብሩ በዚያ ተራራ ላይ እንደሚገልጽ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 88፡12 ላይ፦ “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚኣከ ይትፌሥሑ” (ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ይደሰታሉ) በማለት ጌታ በዚያ ተራራ ላይ ብርሃኑን ሲገልጽ የብርሃኑ ነጸብራቅ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ እንደሚታይ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡፡
❖ ሌላው ታቦር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 12 ጊዜያት ሲጠቀስ በተለይ በመሳ 4 እና 5 ላይ እንደተጻፈው አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ጠላት የነበረው ሲሳራን መስፍኑ ባርቅ በተራራው ላይ ድል ነሥቶበት ነቢይቱ ዲቦራም በተራራው ላይ በደስታ አመስግናበታለች ዘምራበታለች። በተመሳሳይ መልኩ የእስራኤል ዘነፍስ የክርስቲያኖችን ጠላት የኾነውን ዲያብሎስን የኹላችን ፈጣሪ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ላይ አምላክነቱን ገልጦ ድል ስለነሣው ነቢያት ሐዋርያት ምእመናን የሚያመሰግኑት ስለኾነ ለምሳሌነቱ ተስማሚነት ያለውን የታቦርን ተራራን መርጦታል፡፡
❖ ለምን ሙሴንና ኤልያስን ከነቢያት መኻከል መረጠ? ቢሉ፦
ሀ) በማቴ 16፡13 ላይ ሐዋርያትን ስለማንነቱ እንደጠያቃቸው እንደመለሱለት ኹሉ በእውነት ጌታችን የሙሴና የኤልያስ በአጠቃላይ የነቢያት ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ሲገልጽላቸው ነው።
ለ) በዘፀ 33፡17-23 ላይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ጥልቅ ግንኙነት የተነሣ “እባክኽ ክብርኽን አሳየኝ” ብሎ ልመናን አቀረበ፤ እግዚአብሔርም "ወአነብረከ ውስተ ስቊረተ ኰኲሕ ወእከድን እዴየ በላዕሌከ እስከ አኃልፍ" (በሰንጣቃው ዐለት አኖርሃለኍ፤ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይኽ እጋርዳለኍ፤ ካለፍኍ በኋላ እጄን አንሥቼልኽ ጀርባዬን ታያለኽ፤ ፊቴ ግን አይታይም) ብሎታል (ዘፀ ፴፫፥፲፯-፳፫)፡፡
❖ ይኸውም ጀርባ በስተኋላ እንደሚገኝ ኹሉ በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በታቦር ተራራ ላይ እንደሚገለጽለት ሲያመለክተው ነው።
❖ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብም ስለ ታቦር በሚተነትነው መጽሐፉ ሙሴ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውሃ ከእስራኤል ጋር በበደለው በደል ምክንያት ምድረ ርስት ኢየሩሳሌም እንዳይገባ አይቷት ብቻ በናባው ተራራ ላይ እንዲያርፍ ኾኗል (ዘፀ ፴፪፥፶፪፤ ዘፀ ፴፬፥፩-፰)፡፡
❖ ይኽ ለሙሴ አሳዛኝ ቢኾንም በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሙሴ በፊት በሩቁ ያያት ግን ያልገባባት በምድረ ርስት በኢየሩሳሌም ያለች ታቦር ተራራ ላይ አምጥቶት በዘመነ ብሉይ በአካለ ሥጋ ያልገባባትን ርስት እንዲገባባት አድርጎታል፤ ይኸውም አዳምና ልጆቹ በአካለ ሥጋ ያጡትን ርስታቸው ገነትን በአካለ ነፍሳቸው ዳግመኛ ሊያገባቸው እንደመጣ የሚያመለክት መኾኑን በስፋት አስተምሯል፡፡
❖ ጌታችን በብሉይ ኪዳን ከነበሩት ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን በሐዲስ ኪዳን ከነበሩት ከሐዋርያት ሦስቱን በታቦር ተራራ ላይ ማውጣቱ፦
1) የታቦር ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በመኾኗ ሲኾን በቤተ ክርስቲያናችን ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን እንደሚነገሩ ለማመልከት
2) በተራራ በተመሰለች በጉባኤ ቤት ብሉይና ሐዲስ እንደሚነገሩ ለመግለጽ፡፡
3) ሌላው የታቦር ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ስትኾን ይኸውም ጌታ ነቢያትንና ሐዋርያትን በተራራዋ ላይ መሰብሰቡ መንግሥተ ሰማያትን ነቢያትም ሐዋርያትም እንደሚወርሷን ለማመልከት
4) ሙሴ ያገባ ሲኾን ኤልያስ ድንግል ነውና መንግሥተ ሰማያትን ደናግልም ያገቡም እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ነው፡፡
5) እንደ ያዕቆብ ዘሥሩግ ትርጓሜ ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን ሲጽፍ፦ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ 1፡1) እንዳለ፤ ዮሐንስም “በመጀመሪያ ቃል ነበር” (ዮሐ 1፡1) ብሎ እንደ ሙሴ አምላክነቱን የሚመሰክር ነውና ሙሴ አስቀድሞ የጻፈልኝ፤ አኹንም ዮሐንስ አምላክነቴን የሚጽፍልኝ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡
6) ሙሴና ኤልያስ ይመሳሰላሉ፤ ይኸውም በሲና ተራራ 40 ቀንና ሌሊት እንደጾመ ኤልያስም በደብረ ኮሬብ 40 ቀንና ሌሊት የጾመ ነውና፨
7) ሙሴ ንጉሡ ፈርዖንን የገሠፀ እንደነበር ኤልያስም ንጉሡ አክዐብን የገሠፀ ነውና፨
8) ሙሴ ከንጉሡ ፈርዖን ፊት ሸሽቶ እንደሄደ ኤልያስም ከንግሥቲቱ ኤልዛቤል ፊት ሸሽቶ ሄዶ ነበር።
9) ዳግመኛም ሰማይኑን ዝናብ እንዳያዘንም በተሰጠው ሥልጣን ባሰረውና ከ3 ዓመት ከ6ወር ቆይታ በኋላ እንዲዘንብ በፈታው ኤልያስን እንዳመጣ ኹሉ የማሰር የመፍታት ሥልጣን ሥልጣነ ተሰጥቶት “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” (ማቴ 16፡18-19) ላለው ለጴጥሮስን ታላቅ ሰማያዊ ሥልጣን መስጠቱን ለማመልከት አምጥቷቸዋል፡፡
❖ በቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን ያለው መንፈሳዊ አከባበር ደማቅ ነው፤ ይኽ በዓል በቤተ ክርስቲያን በማሕሌት በቅዳሴ በትምህርት የሚከበር በዓል ሲኾን በሀገርኛ የቡሄ በዓል ይባላል፤ ቡሔ ማለት ሊቁ ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት ላይ ሲገልጹት ቧ ብሎ በደብረ ታቦር የተገለጠው የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል የልብሱን እንደ በረዶ ነጭ መኾን ያስረዳል ስለዚኽ የብርሃን፣ ብርሃናዊ ማለት ነው፡፡
❖ በዚህ በዓል በታቦር የታየው የብርሃኑ ምሳሌ የሚሆን ችቦ ይበራል፤ ሌላው በዚኽ በዓል ሰሞን በገጠር ከተራራ ላይ እረኞች ሕጻናት ዥራፍ እየገመዱ ማስጮኻቸው ጌታ በተራራ ላይ ብርሃኑን በገለጸ ጊዜ አብ በደመና ኾኖ “እርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ባለ ጊዜ ሐዋርያት በድምፁ ደንግጸው መውደቃቸውን ለማመለክት ነው፡፡
ጌታችን ጌትነቱን ገልጦበታል። የአብ ድምፅ ተሰምቶበታልና ታቦር ተራራ ቅዱስ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ "ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ ¹⁸ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።" በማለት ገልጦታል (2ኛ ጴጥ 1:17-18)
2.9K viewsተርቢኖስ ሰብስቤ ምንዳ, 13:51