Get Mystery Box with random crypto!

5ተኛው የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የክልልና የፌደራል ባለድርሻ አካላት | Authority for Civil Society Organization (ACSO)

5ተኛው የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የክልልና የፌደራል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባኤ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
*****************************************************************
በጉባኤው ላይ የተለያዩ ሚኒስትሮች ሚኒስትር ዴኤታ፣የፌደራልና የክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ እና ጠቅላይ አቃቤ ህጎች፣የጋሞ አባቶች እንዲሁም የተለያዩ የፌደራል የባለድርሻ ተቋማት ሃላፊዎች በጉባኤው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የጉባኤውን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዬን ጢሞቲዬስ የመድረኩ መመስረት በጣም መሰረታዊ እና አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት እንደሃገር የሞራል ሚዛን መዛባት አጋጥሞናል ይህንን ለማስተካከል አዲስ አስተሳሰብ የተላበሰ ማህበረሰብ ለመፍጠር፣እርቅ፣ማህበራዊ እሴት እንዲዳብር እና ሰላም እንዲሰፍን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንደ ሃገር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ደግሞ ወደ ተግባር ለመለወጥ የዚህ ጉባኤ እና የቅንጅታዊ አሰራሮች በጣም አስፈላጊ ነው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በንግግራቸው እንደገለጹት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቀሴ ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ያላቸው የመንግስት አካላት በህግ የተሰጣቸው ስልጣንና ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ በዘርፋ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በህግ አግባብ በመንቀሳቀስ የህዝብን የላቀ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስራ ማከናወን እንዲችሉ እንዲሁም በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጎልበት እና ለሚያጋጥሙ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስችል ጉባኤ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጉባዔው የተመሰረተበትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ አበረታች ውጤቶች የታዩ ሲሆን ከሁሉ በላይ በአስፈጻሚ አካላት መካከል መቀራረብን የፈጠረ፣ወጥነት ያለው አሰራር ከመዘርጋት አኳያም ጠቃሚ ውጤቶች ተገኝተዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በተለይም ከአራተኛው ጉባኤ በኋላ የተጀመረው የባለሙያዎች /CSO/NGO Desk ኃላፊዎች/ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምክክርና የልምድ ልውውጥ መድረክ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተዳደር ጋር በተያያዘ መልካም ተሞክሮዎችን መለዋወጥ የተቻለበት መድረክ እንደነበርም አስታውሰዋል ፡፡