Get Mystery Box with random crypto!

+ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ አለ + “ከልቦቻችን በማይነቀሉ የፍቅሩ ችንካሮች ተቸነከር | አትሮንስ ዘተዋህዶ-atronss zethewahdo

+ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ አለ +

“ከልቦቻችን በማይነቀሉ የፍቅሩ ችንካሮች ተቸነከርን:: ያዝነው አንለቀውም እርሱም አቀፈን አልተወንም:: ወደ እርሱ በሃይማኖት አቀረበን:: ከእርሱም ወደ ቀኝ ወደ ግራ አንሸሽም:: እንደ ቀለበት በልባችን እንደ ማኅተም በክንዳችን አኖርነው:: እንደ ዕንቁ በልባችን ሳጥን አስቀመጥነው:: እንደ ወርቅ በሕሊናችን መዝገብ አኖርነው::
እንደ ግምጃ ለበስነው:: እንደ ሐር ግምጃ ተጎናጸፍነው:: እንደ ወታደር ሰይፍ ታጠቅነው:: ለጦር ዕቃ እንደተዘጋጀ የድል ጋሻ ተደገፍነው:: ተከዜና ግዮን በኢሎል ወር እንደሚሞሉ ፍቅሩ በልባችን መልቶአል:: እንደ መከር ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ እንደ ክረምት ጊዜም የጤግሮስ ወንዝ ስንዴ ሲያሹት እንደሚሆን እንደ ኤፍራጥስ ወንዝ ልባችንን በወንጌል ፈሳሽነት አረሰረሰው:: መርከባችንንም በሃይማኖት ወንዝ አስዋኘው"
መጽሐፈ ምሥጢር 24:20

"ከእኛ ወገን ክርስቲያን እየተባሉ በገዛ መንገዳቸው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው ... የእንስሳ ሥጋ ከመብላት የሚከለከሉ የሰውን ሥጋ ለመብላት ግን የሚተጉ እነዚህ ናቸው"

"ስምዖን ጴጥሮስ ከሐዋርያት ሁሉ አብልጦ ክርስቶስን ወደደው:: ክርስቶስ ግን ከሐዋርያት ሁሉ አልቆ ወንጌላዊው ዮሐንስን ይወድደው ነበር::
ስለወደደው ግን አለቃ መሆንን ለዮሐንስ አልሠጠም:: እርሱ ከወደደው በላይ እርሱን የሚወደውን አለቃ አደረገው እንጂ"

"ክርስቶስን መውደድ ከወንድሞቹ ይልቅ በጴጥሮስ ላይ በዛ:: ከወንድሞቹ ይልቅ ወደ ጌታ ኢየሱስ ለመድረስ ቸኩሏልና ከመርከቢቱ ዘልሎ ወደ ባሕር ተወረወረ እንጂ በመርከብ ለመጎተት አልቆየም::
ወደ ወደደው ለመድረስ ቀደማቸው:: ከመርከቢቱ ላይ ያዘለለችው ወደ ጥልቁም ባሕር የወረወረችው ፍቅር እርስዋ የክህደቱን መጽሐፍ ደመሰሰችለት::
ራሱን ወደ ጥልቁ የጥብርያዶስ ባሕር በወረወረ ጊዜ የዕዳው መጽሐፍ ሰጠመ:: እርሱ ግን በብዙ ጭንቅ በብዙም ፍለጋ በዋናተኞችም በብልጠታቸው ጥበብ እንደሚገኝ እንደሚያበራ ዕንቁ ሆኖ ከባሕር ውስጥ ወጣ"

#ከመጽሐፈ ምሥጢር ውብ ገጾች


"ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)