Get Mystery Box with random crypto!

ሐዋርያቱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ የጌታችን ዕርገት በመርቀቅ /በርቀት/ ሳይሆን ቀስ በቀስ ሐዋርያት | አትሮንስ ዘተዋህዶ-atronss zethewahdo

ሐዋርያቱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ

የጌታችን ዕርገት በመርቀቅ /በርቀት/ ሳይሆን ቀስ በቀስ ሐዋርያት እያዩት  በመራቅ /በርኅቀት/ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህንን ሲያስረዳ “ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው ” (ሐዋ ፩፡፱) በማለት ገልፆታል፡፡ ይህም የሚያመለክተው የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋን ይዞት እንዳረገ ነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ በቅዳሴው “በአካል ወደ ሰማይ ባረግህበት ዕርገትህ ላይ” እንዳለው በአካል ነው ወደ ሰማይ ያረገው። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በቅዳሴው “በዚያች ሥጋ በመለኮት ኃይል ወደ ሰማይ ወደ ቀድሞ አኗኗሩ ዐረገ” ያለው ይህንን ለማመልከት ነው፡፡ ይህንን ሲያብራራ “ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሔደ፣ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፡፡ ሥጋው አልተለወጠምና” በማለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱና ከትንሣኤው አስቀድሞ በውኃ ላይ እንደተራመደ ሁሉ፣ በለበሰው ሥጋ ወደ ሰማይ ማረግም እንደሚቻለው አስረድቷል /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ ክፍል ፲፫ ምዕ.፥፹፯፡፲፪-፲፫/፡፡ ቅዱስ ሉቃስም “እያዩት ከፍ ከፍ አለ” ማለቱ በእርግጥ ዕርገቱ በአካል እንደነበር ያስረግጥልናል፤ ምክንያቱም ሰው መለኮትን መመልከት አይችልምና ።
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ስለ ጌታችን ዕርገት  “በደብረ ዘይት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲመገብ እጁን በደቀ መዛሙርቱ ላይ አኖረ፤ እያንዳንዳቸውንም ባረካቸው ከዚያም የእሳት ደመና ተቀበለው፤ ከእነርሱም ሰወረው፤ በጨርቅ የጠቀለሉት ይህ ሥጋ በኪሩቤል ክንፎች ተጋረደ፤ በጒልበት ያቀፉት ይህ ሥጋ በእሳት ሠረገላ ተቀመጠ፤ በዚህ ዓለም የተራበና የተጠማ ይህ ሥጋ እህል መብላት፤ ወይን መጠጥን ውሃም መጠጣት ወደ ማይሻበት ወደ አርያም ከፍታ ወጣ፤ በሊቀ ካህናቱ አገልጋዮችና በጲላጦስ አደባባይ ራቁቱን የቆመ ይህ ሥጋ በምስጋና መብረቅ ተሸፈነ፤ በእሳት ደመናም ተጋረደ፤ ጉንጮቹን በጥፊ የተመታ ይህ ሥጋ ከፍ ከፍ አለ” ብሏል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ የጌታችንን ዕርገት በገለጸበት አንቀጽ “ጌታችን ኢየሱስም ከተነጋገራቸዉ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፥ በአባቱም በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡” (ማር. ፲፮፡፲፱) ብሏል፡፡ “ወደ ሰማይ” የሚለው ቃል ወደ ሰማየ ሰማያት ማለት ነው ። ይህም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሚሠራበት ወቅት በጸለየው ጸሎት ውስጥ እግዚአብሔርን “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ!” (፩ኛ ነገ. ፰፡፪፯) ብሎ በጸለየው ይታወቃል። “ዐረገ” የሚለውም ( መላእክት አሳረጉት አላለም) በራሱ ኃይል ሥልጣንና ማረጉን ያሳያል፡፡ ከጌታችን በቀር በራሱ ኃይል ያረገ የለም። ሌሎች ቅዱሳን፡ ለምሳሌ ኤልያስ እና ሄኖክም ቢሆኑ እግዚአብሔር ዐሳረጋቸው እንጂ በራሳቸው ስልጣን ዐላረጉም ።
ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ይህንን “የእግዚአብሔር ልጅ ግን ያለ መሰላል በሚንቦገቦግ የደመና ተን (ጉም) ዐረገ፤ መለኮቱ ይተጋለታልና ወደ አየራትም ነጥቆታልና፤ ነገደ መናብርት ሊያሳርጉት አልመጡም ርሱ ራሱ በመለኮቱ ኀይል አብን ተካክሎ በቀኝ በኩል ተቀመጠባቸው” ሲል ገልጾታል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም ስለ ዕርገት በተናገረበት አንቀጽ “በራሱ ሥልጣን ተነሣ፤ ርሱን ያስነሣው ማንም አይደለም፤ በሚያርግም ጊዜ ማንም ርሱን ያሳረገ አይደለም፤ ኤልያስን አስመልክቶ ዕርገቱ በጌታ አማካይነት የኾነ ነውና እንዲያርግ ያደረገው ጌታ ነው፤ ከዚኽም የተነሣ በሠረገላ እና በእሳት ፈረስ የከበረ ሥነ ሥርዐት ተደረገለት (፪ኛ ነገ ፪፥፲፩)፤ ምክንያቱም ወደ ዐረገበት ቦታ በራሱ ማረግ አይቻለውምና፤ የጌታችን ግን እንደተጻፈው ተለየ፤ ወደ ላይ ለመነሣት ምንም ዐይነት መንኰራኲር አላስፈለገውም፤ በአንድ ቦታ በተወሰነ ጊዜ የሚቀመጡት ሰው በአጋዥ መውጣት ያስፈልገዋል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ብቻ ነውና፤ የእግዚአብሔር ልጅ ግን ራሱ እግዚአብሔር ነውና መንኰራኲር አያስፈልገውም” በማለት የእርሱ ዕርገት በራሱ ስልጣን መሆኑን አብራርቶታል፡፡