Get Mystery Box with random crypto!

#እህቴ_ባትሆኚ_አገባሽ_ነበረ ፡ ፡ #በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ ፡ ፡ #ክፍል_ዘጠኝ ከምሽቱ አምስት ሰ | አትሮኖስ

#እህቴ_ባትሆኚ_አገባሽ_ነበረ


#በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ


#ክፍል_ዘጠኝ

ከምሽቱ አምስት ሰዓት ነው፡፡የምሰራበት ሆቴል ቤርጎ ይዛለች፡፡ስራ እንደጨረስክ ና ብላኝ ስለነበረ ስራዬን ጨርሼ ወደእሷ ለመሄድ እየተዘጋጀው ነው፡፡ስደርስ በረንዳ ላይ ባለ ወንበር ላይ ኩርምት ብላ ቁጭ ብላለች አይኖቾን ሰማይ ላይ ሰክታ ፈዛለች፡፡ከጎኗ ቁጭ አልኩና‹‹ጨረቃን እያየኋት ነው እንዳትይኝ?››አልኳት፡፡

‹‹አልኩህ››

‹‹እራስሽን ምን አሳየሽ?››

‹‹ማለት? ››

‹‹ያው እንቺም ጨረቃ ነሽ ብዬ ነዋ...››

‹‹ጨረቃ ነሽ ስትል በቀጥታ ምን ለማለት ፈልገህ ነው?››

"ከዚህ ንግግሬ ምን የማይገባ ነገር አገኘሽበት... ጨረቃ ነሽ ስል አደንዛዥ የሆነ ውበት ባለቤት ነሽ ማለቴ ነዋ።"

‹‹ጨረቃ እውነትም እንደምትለው አደንዛዥ ውበት አላት ?››

" የላትም እንዴ?"

‹‹እኔ ምን አውቄ እንደዛ ስላልከኝ ነው..ይህቺን አባባል ሁሉም ሰው ይጠቀማታል …ግን በትክክል በምሽት ስራዬ ብሎ የቤቱን በራፍ ከፍቶ በረንዳ ላይ ወጥቶ አንገቱን ወደ ሰማይ አንጋጦ፤ አይኖቹን ጨረቃ ላይ ተክሎ፤ ውበቷን ያስተዋለ ድምቀቷን ያጣጣመ..  ከመቶ ሺ አንድ ሠው ይገኝ ይመስልኸል...ግን ዝም ብሎ ስለሚባል ብቻ ትክክል ይሁን አይሁን ሳያውቅ ሁሉም ይደሰኩራል....

"እና ማጠቃለያሽ ጨረቃ ቆንጆ አይደለችም ነው?›

"አይ ነችምም አይደለችምም..ለምሳሌ እኔ ቆንጆ ነኝ?"

"ግጥም አድርጎ ...በጣም ውብ ነሽ"

"ከዚህ በፊት ሁለት ሰዎች ቀጥታ አሁን አንተ እንደቆምከው ፊቴ ቆመው ምንሽም የማያምር አስቀያሚ ሴት ነሽ ብለውኝ ያውቃሉ።እንደውም እንደዛ አይደለም.አስቀያሚ ወንዳወንድ ነገር ነሽ ነው ያሉኝ፡፡››

"እና ማንኛችንን አመንሽ?"

"ሁለታችሁኑም"

"ሁለታችንንማ ልታምኚ አትችይም ..አንቺ ወይ ቆንጆ ወይ አስቀያማሚ ነሽ.."

"አይ እንደየሁኔታው ቆንጆም አስቀያሚም ልሆን እችላለሁ...ውበት እንደየተመልካቹ ነው በሚለው ንግግር አምናለሁ...ለዚህ ነው ቆንጇ ነሽ ሲሉኝ ብዙ የማልፈነጥዘው አሰቀያሚም ሲሉኝ አንገቴን የማልደፋው።"

‹‹እና ማየቴን ላቁም?››

‹‹እንዳሰኘህ…ግን ጨረቃ በትከክልም  ምን ግዜ ውብ እንደምትሆን ታውቃለህ?››
‹‹አላውቅም ንገሪኝ ››
ጦር ሜዳ ፊት ለፊት ግምባር ላይ እያለህ የሆነ ግዳጅ  ተሰጥቶህ ከጓደኞችህ ጋር ድቅድቅ ባለ ጨለማ እየተጓዝክ መንገድ ጠፍቶህ ከጠላት ምሽግ ሰተት ብዬ ገባሁ ወይስ የጠላት ደጋፊ ከሆኑ ህብረተሰብ እጅ ወደቅኩ እያልክ አቅጣጫህን እንዴት እደምታስተካክል ግራ ገብቶህ እያለ ድንገት ብልጭ ብላ ስትወጣ…ከዛ እየደመቀች ስትሄድ….በቃ ውብ መሆኗ የሚገባህ የዛን ጊዜ ነው፡፡ምክንያም ህይወትህ የምታድንበት ጭላንጭል እድል ሰጥታሀለችና፡፡
‹‹ወይም ደግሞ›› ብዬ እኔ ቀጠልኩላት
‹‹ወይ ደግሞ.. በጣም የምትወጃትን ማለቴ የምታፈቅሪያት ልጅ  አባትዬው ከእቅፍሽ ነጥቀው ለሌላ ሊድሩብሽ መሆኑን ስትሰሚ እሷን በጠፍ ጨረቃ ከቤት አስኮብልለሻት በየጫካው ይዘሻት ስትጠፊ በዛን አስደሳችና ጭንቀት በተቀላቀለበት ወሳኝ ሰዓት ለመንገድሽ ብርሀን ሆና ከፊት ለፊትሽ ቦግ ስትል .. በዛን በክፉና በደስታ ቀን የመንገድሽ አጃቢና መሪ ብሎም  ለፍቅርሽም ድምቀት ስትሆን…አዎ የዛን ቀን ነው ጨረቃ ከውብም ውብ መሆኗን በደንብ የሚገባሽ››
‹‹አየህ ጨረቃን እንደየልምዳችን ነው ለውበቷ ትርጉም የሰጠነው..››
‹‹እንደልምዳችን  ማለት?አንቺ ወታደር ነሽ እንዴ?››ግራ ገብቶኝ ጠየቅኳት፡፡
‹‹አይ ማለቴ ጓደኛዬ ወታደር ነው….ታውቃለህ አይደል?››
‹‹አዎ የበቀደምለታው ጄኔራል አይደል?››
‹‹አዎ ..እሱ ነው››
‹‹ግን…እንዲህ ከሌላ ሰው ጋር በምትሆኚበት ጊዜ ችግር አይፈጥርብሽም?››
አይኖቾ በንዴት ግልብጥብጥ አሉ….‹‹እንደዚህ ከማን ጋር ስሆን አይተኸኛል?›አፋጠጠችኝ፡፡
‹‹አረ አረጋጊው…ከእኔ ጋ ለማለት ፈልጌ ነው›
‹‹ካንተ ጋርስ ምን አድረግናል?››
‹የባሰ አለ ሀገርህን አትልቀቅ› ይላል የሀገሬ ሰው..ድንብርብሬ ወጣ…ምን ብዬ በንዴት ወደላይ የተመነጠቀ ስሜቷን  ልመልሰው?‹‹ምንም አለማድረጋችንን እኮ የምናውቀው እኔና አንቺ ብቻ ነን…ቢያንስ ሁለት ቀን አንድ ክፍል ውስጥ አንድ አልጋ ላይ አድረናል…››
‹እ..እሱስ እውነትን ነው….ግን ያ ምንም ችግር የለውም..እሱም አመቱን ሙሉ ከሚስቱ ጋ ሲተኛ እኔ ምንም ብዬው አላውቅም፡፡››
‹‹ሚስቱ?›
‹‹አዎ ሚስቱ….ሚስትና ሶስት ልጆች አሉት››
‹‹ከባድ ነው››
‹‹አዎ ፍቅር ምን ጊዜም ቀላል ሆኖ አያውቅም››
‹‹ግን ምንድነው ስራሽ..?››
‹‹እሱን ማፍቀር?››
‹‹አይ ስራ መትተዳደሪበትን  ነው የጠየቅኩሽ..?››
‹‹ነገርኩህ ስራዬ እሱን ማፍቀር ነው….ገንዘብ ማገኝበትን ከሆነ የጠየቅከኝ ሌላ ጊዜ ነግሀለሁ…ግን ለራሴ የሚበቃ በቂ ገቢ አለኝ፡፡››
‹‹አይ ጥሩ ነው‹‹
‹‹ጥሩ ባይሆንስ ምን ምርጫ አለኝ....በል አሁን ይብቃን ገብተን እንተኛ››
‹‹አዎ ተነሽ.. ግን እኔ ወደቤቴ ልሂድ››
ፈገግ አለች‹‹ምነው ምን አሳቀሽ?››
‹‹አይ ወደቤት ልሂድ አባባልህ እራሱ ያስቃል..ምነው የጄኔራሉ ሽጉጥ ፊትህ ላይ ሲደቀንብህ በምናብህ አየህ እንዴ ››
‹‹ቀላል…ትቀልጂያለሽ እንዴ…?ገና በቅጡ እንኳን ያላየኋት እና ያላሰደኳት ልጅ አለችኝ..ድፍት ቢያደርገኝ ምን እላለሁ፡?፡››
ከተቀመጠችበት ተነስታ እጄን ይዛ ወደክፍሏ እያመረን ነው.. በራፍ አካባቢ ስንደርስ ነው ስለልጄ የነገርኳትን …ስትሰማ በድንጋጤ እጄን ለቀቀችና ባለችበት በመቆም አፍጥጣ አየችኝ፡፡
‹‹አንተ የእውነትን እንዳይሆን?››
‹‹ግራ ገባኝ ..ስለፍቅረኛዬ እያወራኋት ቢሆን ልሸመጥጣት እችል ነበር ..የልጅ ነገር ግን እንዴት አድርጌ…?መጀመሪያ አዳልጦኝ የተናገርኩ ቢሆን ወደኃላ ልመልሰው ግን እልፈለኩም …ቀጠልኩበት፡፡
‹‹አዎ ልጅ..አለቺኝ..የ7 አመት ልጅ..ተአምር ትባላለች››
‹‹ከዚህ በፊት ግን ፍቅረኛም ሚስትም እንደሌለህ የነገርከኝ መሰለኝ››
ይሄን ደግሞ መች ይሆን የቀባጠርኩላት…ማስታወስ አልቻልኩም፡፡አሁን ወደፊት ተንቀሳቅሰን በራፍ ጋር ደርሰናል….በእጇ ያንጠለጠለችውን ቁልፍ በማስተካከል በራፉን እየከፈተች ነው‹‹አዎ አሁንም  ሚስትም ፍቅረኛም የለኝም ….እውነቴን ነው››
ወደውስጥ ገባች…ሄዳለሁ ያልኩት ሰውዬ ተከትያት ወደውስጥ ገባሁ ..መልሳ በራፉን ከውስጥ ቆለፈችው፡፡አልጋው ጠርዝ ላይ ተቀመጠች፡፡ከጎኗ ተቀመጥኩና ወሬዬን ቀጠልኩ፡፡
‹‹ነገሩ ውስብስብ እና የድሮ ታሪክ ነው… ሀይስኩል ተማሪ እያለው ነው የልጅ አባት የሆንኩት››
‹‹ታድለህ….ምን አለ እኔም ከእናቴ ቤት ሳልወጣ አንድ ዲቃላም ቢሆን ወልጄ በሆነ››
‹‹እውነትሽን ነው?፡፡››
‹አዎ..እውነቴን ነው…..የህይወቴ አንዱ ህመም የልጅ እናት ካለመሆኔ ጋ የተያያዘ ነው…››አይኖቾ በእንባ ተሞሉ…አረ ዘረገፈችው፡፡
‹‹ታዲያ እኮ አሁንም  ይቻላል.. ገናነው አልረፈደም…ሶስትም አራትም ልጅ መውለድ ትችያለሽ››
ኩስትርትር ብላ‹‹መቻሌን በምን አወቅክ?››በሚል ጥያቄ አስበረገገችኝ፡፡