Get Mystery Box with random crypto!

#እህቴ_ባትሆኚ_አገባሽ_ነበረ ፡ ፡ #በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ ፡ ፡ #ክፍል_ሦስት አስተናጋጅ ሆኜ ከ | አትሮኖስ

#እህቴ_ባትሆኚ_አገባሽ_ነበረ


#በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ


#ክፍል_ሦስት

አስተናጋጅ ሆኜ ከተቀጠርኩ አንድ አመት  አለፈኝ።በሲቪዬ ላይ የስራ ልምድ በሚለው ርዕስ ስር የንብረት ክፍል ተቆጣጣሪ እና የሆቴል አስተናጋጅነት የአንድ አመት የስራ ልምድ የሚለውን አስገብቼ መፃፍ እችላለሁ፤አዎ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም።እያንዳንዱን የሠው ትዕዛዝ በትሪ ይዤ አቀርብና በዛው ትሪ ባህሪያቸውን  ያስረክቡኛል። ትሁቱ... ቁጡ.. ጉረኛ... ጋግርታም... እርብትብት... ለጋስ...ንፉግና ተነጫናጭ...በየቀኑ ፀባዩ የሚገለባበጥ ሙልጭልጭ በቃ እኔ ትምህርት ሚኒስቴርን ብሆን ኖሮ ሳይኮሎጂ እና ሶሾሎጂ ለሚያጠኑ  ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት ቢያንስ ለስድስት ወር እንደዚህ አይነት ቦታ አፓረንት እንዲወጡ አደርጋቸው ነበር..ሆቴል ማለት የሠው ባህሪ በብፌ መልክ የሚቀርብበት ቦታ እኮ   ነው።

አሁን ከምሽቱ አራት ሰዓት ሆኗል ፡፡ባሩ ውስጥ አንድ ተስተናጋጅ ብቻ ነው ያለው፡፡ ለዛውም ሴት ደንበኛ...፡፡ይሄንን ብላክ ሌብል  ትጋተዋለች ።አሁን አሷ ብትወጣልን ሌላ የቀረን ስራ ስለሌለን ወደየቤታችን እንሄድና አረፍ እንል  ነበር ስል አሰብኩ ስናስተናግድ ከነበረነው  ስምንት ሴትና አራት ወንድ አስተናጋጆች መካከል አምስቱ ሴት ቀድመው መውጫ ቆርጠው ሄደዋል?ምን? መውጫ ምንድነው ?አላችሁኝ... መውጫ ማለት አንድ ሴት አብሯት የሚያድር ሰው አግኝታ የስራ ሰዓቷ ከመጠናቀቁ በፊት መውጣትና ከደንበኛዋ ጋር መሄድ ከፈለገች እንደሰዓቱ እየታየ ከምታገኘው ላይ እንድትከፍል ይደረጋል...ያው ግብር በሉት ።
ብዙውን ጊዜ በኢትዬጵያ የቡና ቤት ሴቶች ግብር አይከፍሉም ይባላል..እኔም እንደዛ አምን ነበር፡፡ አሁን ግን እንዲህ ተጠግቼ ሳይ አመት እስከ አመት እንደውም እንደእነሱ የሚከፍል የለም? ያው ግብር ማለት ከደሀው  መቀነት  ተቀንሶ  ለኃያላኑ ጡንቻ ማፈርጠሚያ  በግዳጅም ይሁን በይሁንታ የሚሰጥ መባ ነው።ኃያሉ መንግስት ሊሆን ይችላል..ባለሀብት ሊሆን ይችላል...የሠፈር አስተዳዳሪ ባለጡንቻ ሊሆን ይችላል...፡፡  ሁሉም በሚስኪኑ ደሀ ጫንቃ ላይ ተፈናጦ ከርሱን የሚሞላ  ብልጉ አውሬ ነው...ውይ በማሪያም አለቃዬን ነው ከሌላው ባለጉልበት ጨምሬ እንዲህ የጨፈጨፍኩት .አምላክ ሰምቶ ውለታ ቢስ ብሎ እንዳይቀየመኝ፡፡

አሁን ሆቴል ውስጥ የቀረነው ሁለት ወንድ  አስተናጋጆች እና አንድ ሴት አስተናጋጅ እና ደግሞ የእለቱን የተሰራ ሂሳብ ተረክቦ   እየደመረ ያለው ባሉካ ብቻ ነኝ...ሽኩክ ብዬ ወደእሱ ሄድኩና ፡፡
"ጋሼ እንዴት ነው?"

"ስለምኑ ነው የምትጠይቀኝ ጎረምሳው?"

‹‹ስድስት ሰዓት ሊሆን ነው...ተስተናጋጇን ልንዘጋ ነው ልበላት እንዴ?"

"አይ አይሆንም...ትልቅ ደንበኛችን ነች ..ቅር እንዲላት አልፈልግም.."

"አይ ለእሷም ቢሆን ይመሽባታል ብዬ እኮ ነው፡፡"

"የእኔ አሳቢ አይመሽባትም... ከተቀመጠችበት ተነስትታ አስር እርምጃ ከተራመደች የተከራየችበት ቤርጎ ትደርሳለች"

"ኦ ረስቼው… ለካ እዚህ ነው አልጋ የያዘችው"

"አዎ ባይሆን ልጇቹ ይግቡ ..ንገራቸው፡፡"

"እሺ ግን ጋሼ እሷ እስክትሄድ ብቻህን ልትሆን ነው?"

"አይ እኔ አይደለሁም ቀርቼ የማስተናግዳት ...አንተነህ.፡፡..በራሷ  ጊዜ በቅቷት ስትሄድ ቆላልፍና ሂድ...እኔ ሚስቴ ትጠብቀኛለች ...አንተ ከአይጥ ጋር ድብብቆሽ ለመጫወት ምን አስቸኮለህ?››

‹‹እንዴ ጋሼ ከጓደኞቼ ጋር የማወራው ነገር ተደብቆ ይሰማል እንዴ...?"ስል በውስጤ አልጎመጎምኩ፡፡ከሶስት ቀን በፊት ነበር ለሴቶቹ አንድ አይጥ አላስተኛ እንዳለቺኝና ልክ ስተኛ ጆሮዬን እየቀረጠፈች፤ ከንፈሬን እየነከሰች  አስቸገረችኝ ብዬ ያወራኋቸው...እነሱ ደግሞ አፍቅራህ ነው እያሉ ሲያሾፍብኝ ነበር..ይሄው አሁን ጋሼም ተቀላቀላቸው...
ጋሼ ሂሳቡን ሰርቶ ጨርሶ ለመሄድ ተነሳ፡፡

"ጋሼ ለመቆየቱ ግን ካሌብ አይሻልም?"

"ጓረምሳው ንብረቴን ለማን አምኜ ጥዬ እንደምሄድ የመወሰኑ መብት የእኔ መሰለኝ?...መልካም አዳር"ብሎኝ ጥሎኝ ወጣ...፡፡እኔም ሌሎቹ እንዲሄዱ ተናግሬ በዛ ውድቅት ለሊት ከአንድ እንስት ተስተናጋጅ ጋር ተፋጥጬ ተቀመጥኩ...፡፡
እኔም እንደሌሎች በዚህ ሰአት ክፍሌ ገብቼ አረፍ ባለማለቴ ከፍቶኛል ..ግን ደግሞ ጋሼ የተናገራት ነገር ልቤ ላይ አሪፍ  ደስታና ኩራትን አርከፋክፋብኛለች "ጓረምሳው ንብረቴን ለማን አምኜ ጥዬ እንደምሄድ የመወሰኑ መብት የእኔ መሰለኝ?ነበር ያለኝ አይደል?፡፡ "በእውነት መታመን ያስደስታል" ለዛውም አንድ አመት ባልበለጠው ጊዜ ውስጥ ይህን መሳይ ክብር ማግኘት ተስፋው ለፈረሰበት ሰውም ቢሆን  በህይወቱ ጥቂት መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡

ጠረጴዛው ተንኳኳ ከነበርኩበት ባንኮኒ ውስጥ ፡ሮጬ ወጣሁና  ወደ ተጠራሁበት ቀርቤ፤ እጇቼን ወደኃላዬ አጣምሬ፤ ከጉልበቴ ሸብረክ ፤ ከአንገቴ ጎንበስ ብዬ"አቤት ምን ጎደለ ? ምን ላምጣ?"አልኩ፡፡

"እ ..ምንድነበር..?."በፈጣሪ ሰክራለች መሠለኝ ..?ለምን እንደጠራችኝ እንኳን  አታውቅም፡፡
"አዎ..ሙዚቃውን በጣም ቀንሰው እናም አንድ ብርጭቆ አምጣልኝ"
ወይ ፈጣሪዬ ሴትዬዋ ገና መጠጣት ልትጀምር ነው..ለዛውም በሁለት ብርጭቆ…. እንዳለችኝ የሙዚቃውን ድምፅ  ቀነስኩና ብርጭቆውን አጣጥቤ ይዤላት ሄጄ ጠረጴዛዋ ላይ አስቀመጥኩላትና ልመለስ ስል "ተቀመጥ"አለችኝ...
ተቀመጥ በሚለው ቃሏ ውስጥ ምንም አይነት ትህትናም ሆነ ሀዘኔታ አይነበብም፡፡.

"ምን አልሺኝ እመቤቴ?"

"ቁጭ በል..ንግግሬ አይሰማም እንዴ?"

"ኸረ በደንብ ይሰማል"ብዬ ትዕዛዟን በማክበር ሽኩክ ብዬ ቁጭ አልኩ..ፊቷ የተቀመጠውን  የተጋመሰ ብላክ ሌብል ጠርሙስ አነሳችና አዲስ ያመጣሁት ብርጭቆ ውስጥ አንደቀደቀችው፤ስትጨርስ  ወደፊት ለፊቴ አሽከርክራ አሰጠጋችው።

"ኸረ ይሄ ነገር ለእኔ አይሆንም?"

"ባክህ አትንጠባረር ..ዝም ብለህ ጠጣ "ብላኝ እርፍ...
አሁን ይሄ ግብዠ ነው አስገድዷ ደፈራ፡፡ፈራኋት መሠለኝ አነስሁና አንዴ ጎንጨት አልኩለት...
.፡፡‹‹እራት መቼ ነበር የበላሁት?›› ስል እራሴን ጠየቅኩ፡፡ አዎ 12፡30 አካባቢ....‹‹ምንድ ነበር የበላሁት?›› ዳቦ በሙዝ ...፡፡.ሶስት ሙዝና ሁለት ዶቦ....፡፡‹‹አሁን ከስድስት ሰዓት በኃላ ምን እየጠጣሁ ነው›› ውስኪ፡፡...‹‹ይህቺ ጋባዤ አራት ሰዓት አካባቢ ምንድነበር ያዘዘችው..?››ለማስታወስ ሞከርኩ...አዎ ክትፎ ነበረ ያዘዘችው እናም ግማሹን በልታ ግማሹ እንደተመለሠ አይቼያለሁ....አሁን ኪችን ብገባ ግማሹን ትራፊ አገኝ ይሆን?

"እዚህ ሀገር ለስራ መጥተሽ ነው?"ጥያቄውን መጠየቅ ፈልጌ ሳይሆን ዝም ብሎ መቀመጥ ስለጨነቀኝ ነው የቀባጠርኩት። ቢዝነስ የሚሰሩ ሴት  አስተናጋጆች ግን  እንዴት ብለው ነው ከማያውቁት ሰው ፊት ለፊት ተቀምጠው ዘና ብለው የሚጠጡት...ከዛም አልፎ የሚስቁት፤ የሚጫወቱት?ለዛውም በየቀኑ…፡፡ጥያቄዬን ሰምታ ሲጋራዋን ለኮሰች ...እናም ጭሱን አትጎልጉላ እላዬ ላይ በተነችብኝ ፡፡...ልክ እንደቤተመቅደስ ማዕጠንት ዝም ብዬ በፀጋ ተቀበልኩና ወደውስጤ ማግኩት?

"ምሽቱ ደስ ይላል..."ሌላ የማይረባ አስተያየት ከአንደበቴ ድንገት ሾለከ፡፡

"ምሽቱ አንተን ነው የሚመስለው?"አለችኝ፡፡