Get Mystery Box with random crypto!

ዩኒቨርሲቲዎች ለተለያዩ ግለሰቦች የሚሰጡት የክብር ዶክትሬት በሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ረቂቅ አዋጅ | ATC NEWS

ዩኒቨርሲቲዎች ለተለያዩ ግለሰቦች የሚሰጡት የክብር ዶክትሬት በሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ረቂቅ አዋጅ የማይካተት መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከምክር ቤቱ ለዝርዝር እይታ ለቀረበለት የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ከፍትህ ሚኒስትር ጋር ያዘጋጁት የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ረቂቅ አዋጅ ትውልዱ ለሀገራቸው በጎ ስራ ካበረከቱና ምስጋና ከተሰጣቸው ግለሰቦች ልምድ እንዲቀስምና ለህዝብ ጠቃሚ ነገር ለመስራት ተነሳሽነት እንዲኖረው ያስችላል ተብሏል።

ቋሚ ኮሚቴው ከተቋማቱ ለመጡ ተወካዮች በረቂቅ አዋጁ ላይ ግልፅነት ይጎድላቸዋል ያላቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ውይይት አድርጓል።

ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ዩኒቨርስቲዎች የሚሰጡት የክብር ዶክትሬት ከረቂቅ አዋጁ ጋር ግንኙነት አለው ወይ? የሚለው ይገኝበታል።

የፍትህ ሚኒስቴር የህግ ጥናትና ማርቀቅ ዳይሬክተር አዲስ ጌትነት፤ ዩኒቨርሲቲዎች ለተለያዩ ግለሰቦች የሚሰጡት የክብር ዶክትሬት በራሳቸው አሰራርና መስፈርት የሚተገበር መሆኑን አመልክተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የክብር ዶክትሬት የሚሰጡበት የራሳቸው ግብና አላማ ያላቸው መሆኑን በማንሳት በጉዳዩ ላይ የሚታየውን ወጣ ገባ አካሄድ የሚመለከታቸው ተቋማት ሊያስተካክሉት ይገባል ብለዋል።

በፌዴራልና በክልሎች የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ድግግሞሽ እንዳይኖር ክልሎች በተለያዩ ዘርፎች ዕውቅና የሚሰጧቸው ግለሰቦች በሀገር አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አበርክቶ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የፌዴራል መንግስትም ሊሸልማቸው እንደሚችል በረቂቂ መመላከቱን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የህግ አማካሪው አለምአንተ አግደው ተናግረዋል።

የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በረቂቅ አዋጁ ላይ ከአስረጂዎች በቂ ግብዓት የተገኘ በመሆኑ ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር በመሆን ግብዓት ተጨምሮበት ለምክር ቤቱ ይቀርባል ብለዋል።

ለውይይቱ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ተብለው በደብዳቤ ጥሪ ከተደረገላቸው ከ10 በላይ ተቋማት ውስጥ የተገኙት ሶስቱ ብቻ መሆናቸው እንደተጠቆመ ኢዜአ ዘግቧል።

ለጥቆማ @atc_newsbot
https://t.me/atc_news