Get Mystery Box with random crypto!

በተማሪ ምገባ ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ መቻሉን የዋግ | ATC NEWS

በተማሪ ምገባ ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ መቻሉን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገድደዋል።

ይሁን እንጂ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ድርቅ ለተከሰተባቸው አካባቢዎች አልሚ ምግቦች በመላክ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ገልጿል።

ተማሪ ልእልት ብርሃኑ በአበርገሌ ወረዳ ማዓርነት ትምህርት ቤት ተማሪ ናት። በወረዳው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ፍየሎችን ለመጠበቅ ከትምህርት ገበታ ርቃ እንደነበረ ገልጻለች። የተማሪ ምገባ በመጀመሩ ወደ ትምህርቷ እንድትመለስ እንዳገዛት ተናግራለች።

ተማሪ ናትናኤል ሹመት በርካታ ተማሪዎች የዕለት ምግብ በማጣታቸው ምግብ ለመፈለግ ከትምህርት ገበታ ርቀው ነበር ብሏል።

አንድ ክፍል ላይ ከ20 ያልበለጡ ተማሪዎች ይገኙ እንደነበርም ነው ያስረዳው። አሁን ግን በአንድ ክፍል ከ50 በላይ ተማሪዎች ይማራሉ ብሏል። መንግሥት የጀመረውን ድጋፍ እስከ ሰኔ እንዲቀጥል እንደሚፈልጉም አስረድቷል።

የአበርገሌ ወረዳ ኒየረ አቑ ከተማ ነዋሪ እና የትምህርት ቤቱ የወመህ አባል አቶ ወርቁ አየነው "ከችግሮች ሁሉ ክፉው ልጅህን የምታበላው ማጣት ነው፤ አሁን ግን ተመሥገን ልጆቻችን ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለሳቸው ደስተኞች ነን” ብለዋል።

የመዓርነት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ሲሳይ ታደሰ በትምህርት ቤቱ ከሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ጀምሮ ምገባ እንደተጀመረ ገልጸዋል።

የተመዘገቡ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ተመልሰዋል ያሉት ምክትል ርእሰ መምህሩ በምገባ ሥራው ለሦስት ሥራ አጥ ወጣቶችም የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል። የተማሪዎች የመማር ፍላጎትም በእጥፍ ጨምሯል ነው ያሉት።

የአበርገሌ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረሃና ኪሮስ በበኩላቸው በወረዳው በ12 ትምህርት ቤት ምገባው የተጀመረ ሲኾን ከ6ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባው ተጠቃሚ ስለመኾናቸው አብራርተዋል።

በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ያቋረጡ ከአንድ ሺህ 150 በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ተመልሰዋል ነው ያሉት፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍታለሽ ምህረቴ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባደረገው ድጋፍ በዞኑ 64 ትምህርት ቤቶች የምገባ ተጠቃሚ እንደኾኑ ገልጸዋል።

በዚህም ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባው ተጠቃሚ እንደኾኑ የገለጹት ምክትል ኀላፊዋ ምገባው እስከ ትምህርት ዓመቱ መገባደጃ ድረስ የሚቀጥል ነው ብለዋል።

የተማሪ ምገባ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ መከፈቱ ሁለንተናዊ ፋይዳው የጎላ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡ መምሪያ ኀላፊዋ በምገባ ሥራው ከ200 በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

[ዘገባው የአሚኮ ነው]
ለጥቆማ @atc_newsbot
https://t.me/atc_news